የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ውይይት በሳዑዲ አረቢያ እየተካሔደ ነው
ማክሰኞ፣ መጋቢት 2 2017ሩሲያ በዩክሬን የምታካሒደውን ጦርነት ማብቃት የሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኮረው የአሜሪካ እና የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት በሳዑዲ አረቢያ ተጀምሯል። ውይይቱ የሚካሔደው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሣምንት አሜሪካ የደሕንነት መረጃዎችን ለዩክሬን ማጋራቷን እንድታቆም ካዘዙ በኋላ ነው።
በጅዳ ከተማ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ውይይት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የፕሬዝደንቱ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ ማይክ ዎልትዝ ይሳተፋሉ። ከዩክሬን ወገን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሬ ሲቢያህ፣ የፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ የቅርብ ረዳት አንድሪ ዬርማክ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሩስቴም ኡሜሮቭቶ ተሳታፊ ናቸው።
ጦርነቱን ለማቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በሚደረግበት ወቅት በአውደ ግምባር የዩክሬን ይዞታዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ። በተለይ በሩሲያ ኩርስክ ግዛት የዩክሬን ወታደሮችን ለማስወጣት የሩሲያ ወታደሮች ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተዋል።
ዩክሬን በበኩሏ ለሊቱን በሞስኮ እና በዙሪያው በሚገኙ አካባቢዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ከፍተኛ የተባለ ጥቃት ፈጽማለች። የሩሲያ ባለሥልጣናት 337 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትተው መጣላቸውን አስታውቀዋል። ዩክሬን ከሞስኮ አቅራቢያ የሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ መምታቷን ገልጻለች።
በጅዳ በመካሔድ ላይ የሚገኘው ውይይት የዩክሬን ዜጎች እና አውሮጳውያን በዐይነ ቁራኛ የሚከታተሉት ነው። ከዚህ ንግግር ምን ይጠበቃል? እሸቴ በቀለ በዋሽንግተን ዲሲ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ አበበ ፈለቀን አነጋግሮታል። ቃለ-መጠይቁን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
አበበ ፈለቀ
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ