የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት አርዳታ መቋረጥ በጤና አገልግሎት ላይ ያስከተለዉ ተጽእኖ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2017
በአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት (USAID) ድጋፍ መቋረጥ ፣ የኢትዮጵያን የቤተሰብ ዕቅድ፣ የእናቶች እና የህጻናት ጤናን ማስጠበቅ ሊደናቀፍ እንደምችል ተገለጸ፡፡ድርጅቱ ይሰጣቸው የነበሩ ድጋፎች መቋረጡ ሥራውን በተለመደው መልኩ ለመቀጠል እንደሚያስቸግር ተነግሯል።በአሜሪካው ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል አራት ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ስተገበር የቆየው የጤናማ ባህሪያት ስራዎች የተሰኘ ፕሮጀክት አሁን ላይ በእርዳታ ድርጅቱ ስራውን ማቆም ምክንያት እንቅስቃሴ ላይ አይገኝም፡፡ አቶ አቡ ለገሰ በኦሮሚያ ልማት ማህበር የፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱን ኦሮሚያ ልማት ማህበር ተቀብሎ በክልሉ በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ላይ ገቢራዊ ስያደርግ እንደነበር የገለጹት ባለሙያው፤ “በሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በዳዎ፣ አመያ እና ኢሉ ወረዳዎች ፣ በጅማ ዞን ዴዶ፣ ነዲ ጊቤ እና ኦሞንአዳ እንዲሁም ኢሉባቦር ዞኖ በአልጌ ሳቺ እና ዳሪሙ ወረዳዎች ለአምስት ዓመታት እቅድ ይዞ ይተገበር የነበረ ቢሆንም ስራ እንድታቆሙ በሚል ትዕዛዝ ጥር 20 አከባቢ ፕሮጀክቱ ገና በአንድ ዓመት ከሶስት ወሩ ተገቷል” ነው ያሉት፡፡
የፕሮጀክቱ ትሩፋትና የመቋረጡ ተጽእኖው
በእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎትላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራ የነበረው ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ አሁንም አሳሳቢነቱ ያላበቃው የእናቶች እና ህጻናት ሞት መቀነስን ግቡ አድርጎ ይሰራ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡ እናቶች በእርግዝና ወቅት የቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ክትትላቸው በርካታ ቦታዎች ላይ አሁንም አሳሳቢ በመሆኑ ሰፊ የግንዛቤ ስራዎች እንደሚያስፈልግ የገለጹት ባለሙያው በተጠቀሱት አከባቢዎች ለአንድ ዓመት ግድም በተሰራው ስራ ተስፋ ታይቶም እንደነበር አስረድተዋል፡፡ “እውነት ለመናገር ፕሮጀክቱ ጥሩ ውጤቶችን አምጥቷል” ያሉት ባለሙያው፤ ወላድ እናት በአከባቢዋ በሚገኙ ሰዎች ጭምር ድጋፍ እንዲደረግላት በተፈጠረው ግንዛቤ ከጤና ባለሙያዎች እና የጠየና ተቋማት ጋር እንድትገናኝ ማስቻሉን አመልክተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ገና በጅምሩ መቋረጥስ ምን አሳጥቶ ይሆን የተባሉት ባለሙያው ልሰጥ በታቀደው የግንዛቤ እና ድጋፍ ስራ መጠቀም የነበረባቸው የማህበረሰብ አካላት ሳይጠቀሙ መቅረታቸው ምናልባትም የእናቶች እና ህጻናት ሞትን ለመግታት የሚሰራበትን ፍጥነት እንደሚገታም አስረድተዋል፡፡
ተጠቃሚዎች ምን ይላሉ?
በዚህ በእናቶች እና ህጻናት ጤና ላይ ባጠነጠነውፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆን ጀምረው እንደነበሩ ደግሞ ተጠቃሚዎች ያስረዳሉ፡፡ የጅማ ዞን ነዲ ወረዳ ነዋሪዋ አስተያየት ሰጪ ከተጠቃሚዎች አንዷ ነበሩ፡፡ “አንደኛው ነገር ልጆች፣ ወጣቱ እና እናቶች ከዚህ ቀደም ስልጠና ወስደው ገብተው ነበር፡፡ ከዚያ ጥሩ ግንዛቤ ወስደን ነበር፡፡ የእናቶች እና ህጻናት የጤና አገልግሎትን እንዲሁም የወባ በሽታን በተመለከተ በተሰጠን ግንዛቤ መሰረት በቂ አገልግሎት ስናገኝ ነበር፡፡ ይህን ግንዛቤ ከራሳችን አልፎ ለሌላውም ትምህርት እንሆናለን ብለን ስንጠባበቅ ነው ድንገት ፕሮጀክቱ ተቋረጠ ያሉን፡፡ እናም ተመልሶ ብሰራ የተሻለ ጥቅም እናገኝበታለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ተጠቃሚ የደዶ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ የ35 ዓመት እድሜ የሶስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ “ፕሮጀክቱ ከመቋረጡ በፊት በእናቶች እና ህጻናት ጤና በተለይም የወሊድ አገልግሎት እንዲሁም ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ላይ ጥሩ ግንዛቤ አስጨብጦን ነበር፡፡ በዚሁ አጭር ጊዜ እንኳ የታየው የባህሪ ለውጥም ቀላል አልነበረም፡፡ አሁን ግን ድርጅቱ ስራ አቁሞ ነው ያለው፡፡ በዚህም ከዚህ በፊት በነጻ ይገኙ የነበሩ በርካታ አገልግሎቶች ጥራታቸው እየወረዱ መጥተዋል” ሲሉ የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹን ስያስተባብሩ የነበሩት አቶ አቡ እንዳሉትም የገንዘብ ድጋፉ መቋረጥ የተጀመረውን ግብ ያደናቅፋል፡፡ “አሁን ሙያ እና አውቀት ማስተላለፍ የተቻለ ቢሆንም ባለው የበጀት እጥረት ቤተ ለቤት እየተዞረ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ስለማይቻል ግቡ እንደተፈለገ ይሄዳል የሚል እምነት የለም” ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ባለው ግጭትየምግብ እጥረት እና ርሃብ ከፍ ሊል ይችላል ሲል ከሰሞኑ ያሳወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የህይወት ማዳን ምላሾች በከባዱ አደጋ ውስጥ ገብቷል ሲል ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በተለይም 650,000 እናቶች እና ህጻናትን ያካተተ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊነት የተጋለጡ 3.6 ሚሊየን መለየታቸውንም አስገንዝቧል፡፡
ድርጅቱ በዚህን ወቅት እንዳለውም በግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎች ከቤታቸው የተፈናቀሉትን ሶስት ሚሊየን ዜጎች ጨምሮ በአገሪቱ 10 ሚሊየን የሚሆኑት የምግብ እጥረት ፈተናን ተጋፍጠዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ