የትግራይ የንግድ ማሕበረሰብ አባላት የብድር ስረዛ ጥያቄ
ሰኞ፣ መጋቢት 1 2017የትግራይ የንግድ ማሕበረሰብ አባላት የብድር ስረዛ ጥያቄ
በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት እና ኪሳራ እንደደረሰባቸው የሚያነሱት በትግራይ የሚገኙ ነጋዴዎች እና ሌሎች ባለሀብቶች፥ የተከማቸ ብድር፣ ወለድና ቅጣት ደግሞ ወደከፋ ቀውስ እየመራቸው መሆኑ የክልሉ የንግድና የዘርፍ ማሕበራት ይገልፃል። በጦርነቱ በደረሰባቸው ከፍተኛ ኪሳራ ምክንያት ወደቀድሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመመለስ መቸገራቸው የሚያነሱት እነዚህ በትግራይ የሚገኙ የቢዝነስ አንቀሳቃሾች፥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከጦርነቱ በፊት ከባንኮች የወሰዱት ብድር፣ የብድሩ ወለድ እና ቅጣት እንዲሰርዝ ጥያቄ አቅርበዋል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ የትግራይ ንግድ እና ዘርፍ ማሕበራት ባለፈው ቅዳሜ በርካታ የክልሉ ባለሀብቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን፥ የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ የቢዝነስ አንቀሳቃሾች መፍትሔ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል። ለወሰዱት ብድር የጦርነቱን ጊዜ ጨምሮ ወለድ ክፈሉ የተባሉ የትግራይ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች አቤቱታ
የንግድ ማሕበረሰቡ አቋም ያቀረቡት ዲበኩሉ አለም ብርሃነ "የትግራይ ፋይናንሳዊ እንቅስቃሴ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በልዩ ፖለቲካዊ መመርያ በመዘጋቱ፥ ከጦርነቱ በፊት የተሰጠ ብድር፣ ወለዱና ቅጣቱ ሙሉበሙሉ እንዲሰረዝ፥ የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲሰጥበት ደግመን ደጋግመን እንጠይቃለን" ብለዋል።
የትግራይ የንግድ እና የዘርፍ ማሕበራት እንደሚለው በትግራይ ያሉት የንግድ ማሕበረሰቡ ችግሮች ለመፍታት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የፌደራል ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተጨባጭ መፍትሔ እንዳልተሰጠ አንስቷል።
የንግድ ማሕበረሰቡ አቋም ያቀረቡት ዲበኩሉ አለም "ከጦርነቱ በፊት የተወሰደ ብድር፣ ወለድና ቅጣት እንዲነሳ፥ ኪሳራ የሚያካክስ ካሳ እንዲሰጥ በማለት መጋቢት ወር 2016 ዓመተምህረት ወደ አዲስአበባ በመሄድ ለጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ተጠይቆ፥ ከትግራይ ንግድ ማሕበረሰብ፣ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፣ ከንግድ እና ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከብሔራዊ ባንክ ተውጣጥቶ የተቋቋመው ኮሚቴ ተጨባጭ መፍትሔ ሳይሰጥ አንድ ዓመት ሞልቶታል። በንግድ ማሕበረሰቡ የተጫነው ዕዳ፣ ወለድና ቅጣት ደግሞ ተከማችቶ ከ80 ቢልዮን ብር በላይ ደርሷል" ሲሉ አክለው ገልፀዋል። የትግራይ የኢኮኖሚ ኪሳራና የስምምነቱ ተስፋ
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ የሚገኙ የንግዱ ዘርፍ አንቀሳቃሾች በክልሉ የቀጠለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በስራቸው ላይ እንቅፋት ሆኖ እንዳለም ያነሳሉ። አስተያየታቸው የሰጡት ባለሀብት አቶ ዘርኡ ገብረሊባኖስ "ልንክሳችሁ በተገባ ይሁንና ዳግመኛ የማይወድምበት ዋስትና የሚሰጠን አካል ማን ነው ተብለናል። ለዚህ ምላሽ የሰጠ የለም" ሲሉ ተናግረዋል።
በትግራይ የሚገኙ የንግዱ ዘርፍ ማሕበረሰብ ያለው ችግር አስመለክቶ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ጋር መነጋገር እንደሚሹ ያነሱ ሲሆን አስቸኳይ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነም ሌሎች እርምጃዎች እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ