የትግራይ ኃይሎች ጥቃት ደረሰብን አሉ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 12 2014የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ በትግራይ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈፅሟል ሲሉ ትናንት የትግራይ ኃይሎች ዐስታወቁ። የትግራይ ሰራዊት ወታደራዊ ኮማንድ የተባለው የትግራይ ኃይሎች አመራር ባሰራጨው መግለጫ እንዳስታወቀው፦ በሦስተኛ ወገን በኩል ተደረሰ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነትን በመጣስ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ኃይሎች ላይ ባለፈው ነሐሴ 9 ቀን፣ 2014 ዓመተ ምህረት ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጧል። ጥቃቱ የተፈጸመውም «በደደቢት አቅጣጫ በተለመደው የመከላከል ተግባሩ ላይ ባለው የትግራይ ሰራዊት ኃይል ላይ» ነው ብለዋል በመግለጫቸው። ተፈጸመ የተባለው ጥቃት፦ «ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ገደማ የቆየ የከባድ ብረትና ታንክ ድብደባ» መሆኑንም አክለው ገልጠዋል።
በጉዳዩ ዙርያ ማብራሪያ የሰጡን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራር ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ነሐሴ 9 የተፈፀመው ጥቃት የቶክስ አቁም ውሳኔው የሚያፈርስ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ዝግጁ አለመሆኑ የሚያሳይ ብለውታል።
የትግራይ ኃሎች በመግለጫቸው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኩል ተፈፀመ ላሉት ጥቃት በዕለቱ የሰጡት የአፃፋ ምላሽ እንደሌለ ጠቁመዋል። ኾኖም «ሀገር ወደ ጠቅላላ ውድመት የሚመራት ጦርነት ዳግም እንዲሎከስ በማድረግ ተግባር» ብቸኛው ተጠያቂ የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።
የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራር ፕሮፌሰር ክንደያ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የተጀመረ አልያም የቀጠለ ጦርነት የሌለ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድርጊት ግን ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከረዥምና ደም አፋሳሽ ጦርነት በኃላ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕወሓት መሩ የትግራይ ክልል መንግስት ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ የቶኩስ አቁም ውሳኔ ላይ መድረሳቸው በየፊናቸው ዐስታውቀው ነበር። ከመጋቢት ወር በኋላ ወታደራዊ ጥቃት በመሰንዘር አንዱ ሌላውን ሲከስ ይህ የትናንቱ በትግራይ በኩል የወጣ መግለጫ የመጀመርያ ነው። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት ግጭቱ በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸው በቅርቡ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ በትግራይ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈፅሟል ሲሉ ትናንት የትግራይ ኃይሎች ያወጡትን መግለጫ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ወቀሳውን አጣጥሏል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የፕረስ ሴክረተሪ ቢልለኔ ሥዩም ዛሬ ለውጭ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት ያም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተደጋጋሚ ጥረቶችን ዐሳይቷል። ሰብዓዊ ርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስበትንም መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል ብለዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ