የተፈናቃዮች የአቤቱታ ሰልፍ በመቐለ
ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017
በመቐለ ሰልፍ እያደረጉ ያሉት ተፈናቃዮች የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ግቢን ጥሰው መግባታቸው ተሰማ። በጦርነቱ ምክንያት ከምዕራብ ትግራይ እና ሌሎች የኤርትራ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ዛሬ በመቐለ ሰልፍ አካሂደዋል። ተፈናቃዮቹ «በተደጋጋሚ መንግሥት ወደቀዬአችን እንዲመልሰን ብንጠይቅም ምላሽ አጥተናል» ሲሉ ምሬታቸው ገልፀዋል።
ኑሯቸው በመቐለ የተለያዩ መጠለያዎች የሆነው በጦርነቱ ምክንያት በ2013 ዓ.ም.ከትግራይ የተለያዩ ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ባደረጉት ሰልፍ በርካታ መፈክሮች ተሰምተዋል። «መንግሥት ረስቶናል» «ይበቃል፣» «ወደቀዬአችን መልሱን፣» «የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ አንሆንም» የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችን ያሰሙት እነዚህ ተፈናቃዮች፥ ለሰዓታት በትግራይ ርእሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በራፍ ድምፃቸውን ያሰሙ ሲሆን፥ ረፋዱ ላይ ደግሞ ወደ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ግቢ ጥሰው ገብተዋል። «ምላሽ የማይሰጠን ከሆነ፥ ከዚህ አንወጣም» የሚሉት እነዚህ ዛሬ በመቐለ ሰልፍ ያደረጉ ተፈናቃዮች በተደጋጋሚ ከሚገባላቸው ቃል የዘለለ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
የፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤቱን ግቢ ጥሰው ሲገቡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በጽሕፈት ቤታቸው እንዳልነበሩ ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጠናል። ሰልፈኞቹ ወደ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ግቢ ከገቡ በኋላ ሁኔታውን ለመቆጣጠር እዛው ከነበሩ ፖሊሶችና ታጣቂዎች በተጨማሪ በርከት ያሉ የፖሊስ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ተሰማርተዋል። ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ቁርጥ ያለ ምላሽ ከመንግሥት እንጠብቃለን ሲሉ ተደምጠዋል።
ዛሬ ከቀትር በኋላ በነበረው ሁነት፥ ከሰልፈኞቹ መካከል የተወሰኑ ከፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ውይይቱ ለመገናኛ ብዙኀን ዝግ ተደርጓል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ