የብር የምንዛሪ ዋጋ በሕጋዊ እና በትይዩ ገበያ ያለው ልዩነት
ረቡዕ፣ ሰኔ 25 2017
ኢትዮ ፎሬክስ የተባለ የግል የምንዛሪ ተቋም ደግሞ አንዱን ዶላር በ155 ብር ከ90 ሳንቲም ይሸጣል። ትይዩ በሚባለውና ከሕጋዊ የምንዛሪ ሥርዓት ውጪ ያለው ግብይት ደግሞ አንዱን ዶላር እስከ 160 ብር እንደሚያገበያይ ያሰባሰብነው መረጃ ያሳያል። የኢትኢትዮጵያዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አተዳደር ሥርዓት ለውጡን ተከትሎ የትይዩ ግበያው «ከነበረበት መሠረታዊ በሚባል መልኩ» መውረዱን ሰሞኑን አስታውቋል። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ፤ ልዩነቱ ቢቻል ከአምስት በመቶ በታች መውረድ እንዳለበት ጠቅሰው ያንን ለማድረግ ግን የወጪ ንግድ ላይ ብርቱ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፈው ዓመት ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ. ም. ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ ሲወስን በሕጋዊ የምንዛሪ ሥርዓቱ እና «ጥቁር» በሚባለው የትይዩ ገበያ መካከል የ100 ፐርሰንት ልዩነት ነበረው። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምሕረቱ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳስታወቁት ባለፉት 11 ወራት ውስጥ ይህ ልዩነት እስከ አምስት በመቶ ወርዶ የነበረበት ጊዜ ተመዝግቧል።
ይህንን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ልዩነት እዚህ ግባ የማይባል ደረጃ ለማድረስ ተከታታይ ሥራዎች ያስፈልጋሉ የሚሉት አቶ ማሞ «መጠኑ ካልሆነ በስተቀር» ትይዩ ገበያ መኖሩ እንደማይቀር ገልፀዋል። የካፒታል ሒሳብ አለመከፈቱንም በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
«ተገማችነት ያለው የብር የምንዛሪ ዋጋ ለምን አልተፈጠረም?» ይልቁንም የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ መጠን ተዳክሟል የሚለው ተጠቅሶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ነው አቶ ማሞ ይህንን ያሉት።
«ዕቃ የሚያስመጡ ሰዎች ሕጋዊ የሆነ ክፍያ ለመፈፀም ወደ ባንክ በሚሄዱበት ጊዜ አንዳንድ ሕጋዊ የሆኑ ክፍያዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል አሠራር አለመኖሩ ወደ ትይዩ ገበያ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል»
የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ ከውጭ የምናስገባውን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን መቀነስ እንጂ የአንድ ዓመት ውጤቱ የዘላቂ ሥራው አመልካች ላይሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
«በአንድ ዓመት ውስጥ ይህንን ነገር በደፈናው ትልቅ ስኬት ተደርጓል ብለን የምንዘጋው ነገር አይደለም»
የብሔራዊ ባንክ ገዢው እንደሚሉት ከዚህ በፊት በነበረውአሠራር ሲጠቀሙ የነበሩ ሰዎች «ያንን ለማቀጠል ሥራ መሥራታቸው የማይቀር ነው» ሲሉ ሕገወጥነቱን የሚከተሉ መኖራቸውንም ለሁኔታው አለመጥበብ ሌላ ምክንያት አድርገው አቅርበዋል።
«አንዳንድ በሃዋላ ሥራ ላይ የሚሠማሩ ድርጅቶች ሕጋዊውን መንገድም ሕገወጥ መንገድንም አጣርሰው የመሄድ ሁኔታ አይተናል»።
«ሀብት ለማሸሽ ግብር ለመሠወር» ይደረጋል በተባለ ጥረት አንዳንድ ሰዎች ከሕገ ወጥ የምንዛሪ አሠራሩ የውጭ ምንዛሪን በከፍተኛ መጠን የሚሰበስቡ መኖራቸው ይነገራል። ይህም በፖሊሲ ሳይሆን በክትትል እና በሕጋዊ ርምጃ የሚፈታ መሆኑን መንግሥት ያምናል። የወጪ ንግድን ማሳደግ ቁልፉ ጉዳይ መሆኑን ግን አቶ ዳዊት ገልፀዋል።
«የዶላር እጥረት ሲኖር ባንኮች ለተጠቃሚው የሚያቀርቡት የዶላር እጥረት ሲኖርባቸው የተለያዩ መሰናክሎች ይፈጠራሉ። እጥረቱን ግን በዘላቂነት የምናሳካው [የምንቀርፈው] የወጪ ንግዳችን በመጠን፣ በጥራት፣ በብዛት ማደግ አለበት። ያንን ስናሳድግ የዶላር አቅርቦታችን እየጨመር ይመጣል»።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም አንዱን የአሜሪካ ዶላር በ134፣ ዩሮን በ152 ብር ይሸጣል። ኢትዮ ፎሬክስ የተባለው የግል የምንዛሪ ተቋም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ155.9፣ ዩሮን በ170 ብር ይሸጣል። የትይዩ ገበያው ደግሞ አንዱን የአሜሪካ ዶላር በ160 ብር እየሸጠ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ