የብሪታንያ ምርጫ እና ዉጤቱ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3 2012ብሪታንያ ዉስጥ ታኅሳስ 2 ፣ 2012 ሃሙስ በተደረገዉ ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወግ አጥባቂ ፓርቲ ማሸነፍ ሀገሪቱ ከአውሮጳ ሕብረት ለመውጣት የጀመረችውን እርምጃ እንደሚያፋጥን ተገለፀ። የዚህ ምርቻ ዉጤት ለገዥዉ ፓርቲ አብላጫ ድምፅን ያስገኘ ነዉ ተብሎአል። በምርጫዉ ወግ አጥባቂዎቹ የምክር ቤቱን አብዛኛ መቀመጫ ማሸነፋቸው ዛሬ ይፋ ሆኗል። ተቃዋሚዎቹ ሌበር እና ነፃ ዴሞክራቶቹ አልቀናቸውም። ውጤቱ ይፋ እንደሆነም ጆንሰን ብሬግዚትን በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ወር በ 31 ኛው ቀን እውን እንደሚያደርጉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል። ተፎካካሪያቸው የሌበር ፓርቲው ጀርሚ ኮርቢን በበኩላቸው በውጤቱ ማዘናቸውን ቢገልፁም በመርጫ ዘመቻው ወቅት ለሀገሪቱ የሚበጅ ተስፋ ትኩረት እንዲያገኝ አድርገናል ይላሉ። የብሪታንያ የምርጫ ውጤት ይፋ እንደሆነም የአውሮጳ ሕብረት መሪዎች ብሬግዚት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ጀምረዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ለቦሪስ ጆንሰን የእንኳን ደስ ያልዎት መልእክታቸውን በማስቀደም የቁርጡ ቀን በመድረሱ የብሪታኒያ ምክር ቤት የብሬግዚትን ውል መርምሮ እንዲያፀድቅ አሳስበዋል። የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ከተመሳሳይ የደስታ መግለጫ ጋር አያይዘው «ሙሉ ኃላፊነት ያለው መሪ መገኘቱ» ሥራውን ለማከናወን እንደሚረዳ አመልክተዋል።
ገበያዉ ንጉሤ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ