የቀጠለው የሐኪሞች ሥራ ማቆም አድማ
ሰኞ፣ ግንቦት 11 2017
ከደመወዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ዝቅተኛነት ጋር በተያያዘ የጤና ባልሙያዎች እንዲመለሱላቸው 12 ጥያቄዎችን ለመንግሥት ማቅረባቸውን ይናገራሉ። እንዲያም ሆኖ ጥያቄዎቹ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ባለማግኘታቸው ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ከፊል የሥራ ማቆም ማድረግ ጀምረዋል። ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ሙሉ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ ባለሙያዎቹ አስጠንቅቀው ነበር።
አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሆስፒታሎች በአንዱ የሚሠሩት የንቅናቄው አስተባባሪ እንደሆኑ የነገሩን ሐኪም ዛሬ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚሠሩ ባለሙያዎች በአብዛኛው ወደ ሥራ አልገቡም ይላሉ።
ባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙት ሆስፒታሎች መካከል በጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ዛሬ ምንም ዓይነት ሥራ እንደሌለ አንድ የሆስፒታሉ ባለሙያ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል በአካል እንዳየነው በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የድንገተኛ ክፍል አገልገሎት እየሰጠ አልነበረም። አንድ ቀጠሮ የነበራቸው ታካሚም የሚከታተላቸው ሐኪም ወደ ሥራ ባለመግባቱ ሳይታከሙ መመለሳቸውን ነግረውናል።
ቀደም ሲል በፅኑ ህሙማን ክፍል የነበሩ ሰዎችን የሚከታተሉየጤና ባለሙያዎች ህሙማንን ጥለው መውጣት እንዳልቻሉም አንድ የሆስፒታሉ ሐኪም ገልጸዋል። የደብረታቦር ሆስፒታል አንድ ሠራተኛ በበኩላቸው በጥቂት የሥራ ክፍሎች የተወሰነ ሥራ መኖሩን ጠቁመው ሆኖም ሥራ ያልገቡ ሠራተኛች ስም ዝርዝር በሰው ኃይል እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
የደንበጫ ሆስፒታል አንድ ሐኪም በበኩላቸው እርሳቸውን ጨምሮ በሥራ ላይ ቢሆኑም የአንድ ሐኪምን በፀጥታ ኃይሎች መወሰድን ተከትሎ ድባቡ መልካም እንዳልሆነ ገልጠዋል። ሌላ የንቅናቄው አስተባባሪ አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን ፖልቲካዊ ይዘት ለመስጠት እየሞከሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህ ስህተት እንደሆነ ተናግረዋል። «እኛን ተገን በማድረግ በእኛ ለመጠቀም የሚፈልግ አካል ከእኛ መራቅ የገባዋል፣ መንግሥትም የተለያየ ምክንያት እየሰጠ የንቅናቄውን ዓላማ ሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ የሚያደርገውን ሙከራም ያቁም» ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል (EHRDC) ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ 75 የጤና ባለሙያዎች መታሰራቸውን ትናንት ባወጣው መግለጫ አመልከቷል። ከማዕከሉ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ብንሞክርም ዳይሬክተሩ ከአገር ውጪ ናቸው በመባሉ አልተሳካም።ጉዳዩን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ተጨማሪ አስተያየት ለማካትተ የተደረገው ጥረትም አልተሳካም። ሆኖም ቀደም ባሉት ዘገባዎቻችን የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግኙነት ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ የባለሙያዎቹ ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛና በርጅም ጊዜ እቅድ እንደሚመለሱ ተናግረው ነበር።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ