የሰሜን ወሎ ሕዝብ ዝናብ እንዲጥል ፈጣሪዉን ሲማፀን ዝናብና ነፋስ ሰዉ ጎዳ ንብረት አጠፋም
ሐሙስ፣ ነሐሴ 1 2017በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞንባለፈዉ ዕሁድ የጣለዉ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ጃራ የሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያና አንድ ትምሕርት ቤት አወደመ።ኃይለኛዉ ዝናብና ነፋስ በ28 ተፈናቃዮች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱም ተዘግቧል።አብዛኞቹ መጠለያ ቤቶች በመፈራረሳቸዉና የተረፉትም ለአደጋ በመጋለጣቸዉ ተፈናቃዮች ሜዳ ላይ መቅረታቸዉን አስታዉቀዋል። የመጠለያ ጣቢያው ኗሪ የሆኑት ወ/ሮ ማሬ በላይ ፡
‹‹ዝናብ ጋር ንፋስ ነው የመጣው፤ ቤቱ የተጎዳ ነው ከላይ ሸራ ተደርጎበታል እንጂ ቤቱ እንጨቱ ከስር የለቀቀ በመሆኑ ወደቀ፤ ብዙ ቤት ወድቋል፡፡ ትንሽ ቆይቶ በነበር አደጋው ይከፋ ነበር፡፡›› ብለዋል።
አደጋው በተከሰተበት ወቅት በቤቶቹ ውስጥ የነበሩ 28ሰዎች ነፋስ በሚጥለው ቆርቆሮ እና ሚስማር ተመተው ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ መሆኑን የገለፁት ተፈናቃዮች አሁን ቀሪ ያልወደቁ መጠለያ ቤቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ በመሆናቸው በቀጣይ ሊወድቁ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹ቤቱ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ነው ቤቱ የወደቀው ውስጥ ላይ ያሉ ሰዎች ቆርቆሮ እየቀደዳቸው፣ሚስማር እየወጋቸው ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል፤ ወደ ሆስፒታል ሄደዋል አሁን የቀረው ቤት ንፋስ ሲመጣ ውጭ እያደርን ነው፡፡››
አደጋው ሲከሰት በአካባቢው የነበረውየኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ በወደቁ ቤቶች ፍርስራሽ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በማውጣት አግዘውናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ በህፃናት እና ነብሰጡር እናቶች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሆኗል ይላሉ፡፡
‹‹የወደቀው ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎችን መከላከያዎቹ አውጥተው አትርፈውልናል፤ የእኛም ወጣቶች ብዙ ተሯሩጠው ነፍሰጡር እናቶች እና ህፃናት አውጥተውልናል፡፡ የሞተና የጠፋ ሰው የለም እንጂ ጎርፉም ህፃናትን ሲወስድ፣ ጠንካራ ሰዎች ናቸው ያወጧቸው፡፡››
በመጠለያ ጣቢያዉ ዉስጥ ያለ ትምህርት ቤት ፈርሶል
አሁን ላይ የቀሩት የመጠለያ ቤቶች ለአደጋ የተጋለጡ በመሆናቸው ዝናብ ሲመጣና ሌሊቱን ከቤት ውጭ እያሳለፍን ነው የሚሉት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ስጋት ላይ ነን ብለዋል፡፡
‹‹አሁን ሌላውም ቤት እየተነቃነቀ ዝናብ ሲዘንብ ውጭ ላይ ነን››
በሰሜን ወሎ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት በበኩሉ በጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያለ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት እና የመጠለያ ቤቶች በአደጋው መጎዳታቸውን የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ አለሙ ይመር ይገልፃሉ፡፡
‹‹ግቢው ውስጥ ያለ የህፃናት ት/ቤት ወድሟል፣ የወደሙም መኖሪያ ቤቶች አሉ፤ አውሎነፋሱ በጣም ከባድ ነበር፤ ክረምቱ ከገባ ጀምሮ ብዙ ቤቶች ናቸው አደጋ የደረሰባቸው፡፡››
የደረሰውን የጉዳት መጠን ለአማራ ክልል እና ለኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በማሳወቅ የመጠለያ ድንኳኖች እና የባለሙያ ቡድን ወደ አካባቢው መንቀሳቀሱን አቶ አለሙ ይመር ተናግረዋል፡፡
‹‹ክልሉንም ሆነ ፌደራሉን በመጠየቅ ዛሬ ማቴሪያል እየተጓጓዘ ነው፡፡ ከክልልም ከፌዴራልም ባለሙያም ተመድቦልናል፤ ዛሬ እየገቡ ነው፤ ድንኳን ነው የተጫነው ከፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር፤ያንን በየወደመበት የማስቀመጥ ሥራ ይሰራል፡፡››
በሰሜን ወሎ ዞን 30,000 በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሲኖሩ በዞኑ ያሉ 4 የመጠለያ ጣቢያዎችም ለኑሮ ምቹ ያልሆኑና አስፈላጊውን የመሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኢሳያስ ገላዉ
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ