የሩስያ ሰላዮች አሻጥር በአውሮጳ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 7 2017የሩስያ ሰላዮች እንቅስቃሴ አውሮጳ ውስጥ ከምን ጊዜውም በላይ ከፍ ብሏል ። ሩስያ ወደ ዩክሬን ከመዝመቷ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2021 ቀደም ካለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 2024 አውሮጳ ከ40 በላይ የሩስያ ሰላዮች ትእይንቶችን ያስተናገደችበት ጊዜ ነው ። ግን ከጀርባው ያለው ምንድን ነው? የሞስኮስ ግቦች ምንድንናቸው?
ሩስያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ ባሉት ጥቂት ዓመታት የሩስያ ሰላዮች አሻጥር አውሮጳ ውስጥ ከምን ጊዜውም በላይ ጨምሯል ። ምዕራባውያን ለዩክሬን ጦር መሣሪያዎችን እንዳይልኩ ለማደናቀፍ መፍቀሬ ሩስያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችም ቀጥለዋል፤ አንዳንድ ጊዜም ዘመቻዎቹ ግድያዎችን ያካተቱ ናቸው ይላል የፍራንክ ሆፍማን ዘገባ ።
አውሮጳ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሩስያ ሰላዮች ቁጥርም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው እንደ ዘገባው ። ሩስያ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንደነበረው ሰላዮቿን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያሰማራች መሆኑን የጀርመን ፌዴራል የዜና አገልግሎት (BND)የቀድሞ ወኪል ጌርሃርድ ኮናርድ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል ። የሰላዮቹ ግብንም አብራርተዋል ።
«በእርግጠኝነት ተለይቶ መታየት ያለበት ነገር ነው፤ ለምሳሌ የሕዝብ ግንኙነት የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡን ግራ ለማጋባት ይውላሉ ። መንግሥት ፀጥታን በማረጋገጥ ረገድ ክፍተት እንዳለበት ያሳያሉ ።»
በላይንደር ዩኒቨርሲቲ የሽብር እና የፖለቲካ ነውጥ ጥናት ክፍል ኃላፊ ባርት ሹማን ሩስያ በአውሮጳ «የኢነርጂ እና ቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማት መጠነ ሰፊ ጥቃት» ተጠያቂ ናት ብለዋል ። ጌርሃርድ ኮናርድ ከባርት ሹማን ጋር ይስማማሉ ። በአውሮጳ የተሰማሩት የሩስያ ሰላዮች ግባቸው በዋናነት ወታደራዊ ዒላማዎች ሳይሆኑ የሕዝብ መገናኛ አውታሮች ላይ መሆኑንም ገልጠዋል ።
«ከዚያም ባሻገር፦ የስለላ ተግባራቱ በአጠቃላይ ወታደራዊ ጠቀሜታ በሌላቸው ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ። ያም ማለት፦ ከጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ ጀምሮ እስከ ጀርመን መከላከያ ሥፍራዎች ድረስ ብሎም በፖላንድ አሻግሮ ጀርመን ደርሶ ዩክሬን እስኪመለስ ባሉት የማጓጓዝ መስመሮች ላይ ያነጣጠረ ነው ። መሰል ተግባራትን ለማደናቀፍ ወይም ለመከላከል በማሰብም ይሰለላሉ፣ ይመረመራሉ እናም አስፈላጊ ከሆነ ያወድማሉ አለያም ያሰናክላሉ ።»
የሩስያ በአውሮጳ አገራት ተቋማትን የማደናቀፍ እና የስለላ ተግባር የዩክሬን ጦርነት በተከፈተበት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 የጀመረ አይደለም ። ይልቁንስ ከዚያ ቀደም ብሎ ከ2014 ጀምሮ የነበረ ነው ይላሉ ጌርሃርድ ኮናርድ ።
«በእውነቱ ስለላው ከ2014 ጀምሮ ከፍ እያለ ነበር፤ ከ2022 በኋላ ደግሞ የስለላ ተግባሩ ከሞላ ጎደል የጦርነት ሎጂክን በመከተል ገዘፍ ብሏል ። የስለላ እንቅስቃሴዎችን አንዳንዴም በግልፅ የሚታይ የአሻጥር ተግባሮችን አስተውለናል ። ይህ ከሩስያ ዕይታ አንጻር ምክንያታዊ ነው ። እናም ይኸው ግጭቱ እስከቀጠለ ድረስ ይቀጥላል ።»
ይህ በመሆኑም ይላሉ፦ የጀርመን ፌዴራል የዜና አገልግሎት ወኪል ጌርሃርድ ኮናርድ፥ «የአውሮጳ አባል አገራት በወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን መጠናከር ያለባቸው፤ በስለላውም ግንባር ጭምር ነው ።»
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ፍራንክ ሆፍማን
ኂሩት መለሰ