የምርጫ ቦርድ በህወሓት ላይ የወሰደው እርምጃ እና የሰላም ስምምነቱ
ቅዳሜ፣ የካቲት 8 2017የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህወሓት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ፥ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር ስጋቶች አሉ። ያነጋገርናቸው ምሁራን የሰላም ስምምነቱ ፈራሚ አካላት ችግሮች በፖለቲካዊ ውይይት መፍታት አለባቸው ይላሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ሁለት ቡድኖች በማሸማገል ላይ እንደቆዩ የገለፁት በትግራይ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች፥ ፖለቲከኞች ልዩነታቸው በውይይት ለመፍታት መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተሰጥቶት የነበረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ይጠበቁበት የነበሩ ግዴታዎች ባለመፈፀሙ ምክንያት 'በምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሳተፍ' ማገዱ እና በሶስት ወራት ውስጥ 'የእርምት እርምጃ' ካልወሰደ ደግሞ፥ ፓርቲው በቀጥታ እንደሚሰረዝ መግለፁ ይታወቃል።
የትግራዩ ጦርነት ተከትሎ በ2013 ዓመተምህረት ጥር ወር በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ የተሰረዘው ህወሓት፥ ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኃላ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ሲጠይቅ ቆይቷል። ይሁንና ባለፈው ነሓሴ 3 ቀን 2016 ዓመተምህረት በምርጫ ቦርድ ተሰጠው የተባለ 'በልዩ ሁኔታ የምዝገባ እና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት' እንደማይቀበል ህወሓት በወቅቱ ገልጿ ነበር።
ይህ በህወሓት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አልያም የፌደራሉ መንግስት መካከል ያለ ልዩነት፥ በበርካቶች ዘንድ ስጋት የፈጠረ ሆንዋል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ አስተያየታቸው ያጋሩን የሕግ ምሁሩ አቶ ዳዊት ገብረሚካኤል፥ ህወሓት የፕሪቶርያ ውል ፈራሚ እንደሆነ አካል በምርጫ ቦርድ ከተሰጠው ምስክር ወረቀት በፊትም በሰላም ስምምነቱ መሰረት እውቅና አግኝቶ የቆየ ነው በማለት ሐሳባቸው ያስቀምጣሉ።
የፕሪቶርያ ውል ፈራሚ የሆኑት አካላት ቅድሚያ ለሰላም ይስጡ የሚሉት የሕግ ምሁሩ አቶ ዳዊት ገብረሚካኤል ግጭት ሊፈጥሩ ከሚችሉ አካሄዶች መቆጠብም ያስፈልጋል ሲሉ ያክላሉ።
"ካልቻሉ አሁን ከስልጣን መልቀቅ አለባቸው" ተቃዋሚዎች
የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት ለማክበር ዝግጅት ላይ ያለው ህወሓት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና አቶ ጌታቸው ረዳ በሚመሯቸው በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ይገኛል። በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ ባለፈው ነሓሴ ወር 2016 ዓመተምህረት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጉ ይታወሳል። ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ነሓሴ 3 ቀን 2016 ዓመተምህረት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ 'በልዩ ሁኔታ' ተብሎ የተሰጠ የሕጋዊነት ምስክር ወረቀት እንደማይቀበሉት በተለያየ ግዜ አስታውቀው ነበር።
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህወሓትን ከሰሱ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ሁለት ቡድኖች የተፈጠረ መካረር ወደለየለት ግጭት እንዳያመራ በመስጋት የማሸማገል ጥረት ላይ እንደቆዩ የገለፁ በትግራይ የሚገኙ የተለያዩ አብያተ እምነት መሪዎች ፥ ፖለቲከኞቹ ችግራቸው በውይይት እንዲፈቱ እና ከግጭት እንዲቆጠቡ የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ገልፀዋል። በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩ ሁለት ቡድኖች በሃይማኖት መሪዎቹ አሸማጋይነት የፈረሙት ይህ ውል ፖለቲከኞቹ እና ደጋፊዎቻቸው የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ወደሐይል እርምጃ እንዳይገቡ፣ ከጥላቻ እንግሮች እንዲቆጠቡ፣ ፖለቲካዊ ልዩነታቸው በውይይት እንዲፈቱ የሚያስገድድ ነው። ይህ ስምምነት የተፈረመው ባለፈው ጥር 12 ቀን መሆኑ ሰነዱ ያመለክታል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ