የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣ ኢትዮ-ኤርትራ፣ የኢትዮጵያ ሠላም፣ የዩክሬን ጥቃት
ሐሙስ፣ ግንቦት 28 2017በኢትዮጵያና የኤርትራ መካከል እየናረ የመጣዉ ዉጥረት፣ የኢትዮጵያ የሠላም ሚንስትር መግለጫና የሐገሪቱ ሠላም፣ ዩክሬን በሩሲያ ላይ የከፈተችዉ ድንገተኛ ጥቃት ሳምንቱን የብዙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን አስተያየት ከሳቡ ርዕሶች የጎሉት ናቸዉ።ከተሰጡት አስተያየቶች ስድብና ዘለፋዉን ነቅሰን ጥለን ጥቂቱን እናሰማችኋለን። አብራችሁኝ ቆዩ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ዉጥረት
የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቅ ባለፈዉ ግንቦት 16 ኢትዮጵያ፣ በጣሙን ገዢ ፓርtቲዋን ብልፅግናን «የዉጪ ኃይላት ወኪል፣ ወይም ተገዢ» ና «ጦር መሳሪያ የሚያከማች» እያሉ በይፋ ከወነጀሉ ወዲሕ ከዓመት ከመንፈቅ በላይ ዉስጥ ዉስጡን ሲትመከመክ የነበረዉ የሁለቱ መንግሥታት ጠብ እየናረ መጥቷል።የሁለቱ ሐገራት ባለሥልጣናትና ደጋፊዎቻቸዉ የገጠሙት የቃላት-ጦርነትም በያዝነዉ ሳምንት እየተባባሰ ነዉ።
ብዙወርቅ ማሩ በፌስ ቡክ በእንግሊዝኛ ባሠፈረዉ መልዕክት ዉጥረቱን በዲፕሎማሲ መንገድ እንዲረግብ ይመክራል።«የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ከኤርትራ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለመፈለግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግ ጥሩ ነዉ» ብዙወርቅ ማሩ ነዉ-ይሕን ባዩ።አሕመድ ሙስጠፋ እሱም በፌስ ቡክ ይጠይቃል፤ «ኢሱ ጭሱ ብላቹህ አስጨፋራቹህን ነበር። አሁን ኢሱ ገልቱ ብላቹህ ልታጫርሱን ነዉ!! » ጥያቄዉን በሁለት ቃለ አጋኖ አሳረገ።ባርክልኝ ጫኔ አድነዉ «አዬ ጉድ ሌላ ጦርነት» እንደ መሥጋትም፣ እንደ መገረምም--- እና ቀጠለ ጥያቄ አዘል ትዝብቱን-«ኢትዮጵያ መቼ ልማት ትናፍቅ ይሆን??» ኪ ፍቅር ሚቶ ምክር ብጤ አለዉ «ዜጋን የማፋጄት አጀንዳ ባታራምዱ መልካም ነው።»
አዲሱ አበበ «በጦርነትም በኑሮ ውድነትም የሚወድመው የድሃ ልጅ እንጂ አቀጣጣዮች አይደሉም» አለ በፌስ ቡክ።ቀጠለም።«እረፉ ደሃ ነቅቷል።» ብሎ።ሐብታሙ አራጋዉም ተመሳሳይ አስተያየት አለዉ «ለህዝቦች አስቡ። መሪዎች በጦርነቱ ወቅት አይገኙም።» ብሎ።መርሻ ዋዋ «በምንም ምክንያቶች ጦርነት አንፈልግም።» ይላል።ላሚቲ ኮ የሚል የፌስ ቡክ ሥም ያላት ወይም ያለዉ «ጦርነት አንፈልግም» አለች ወይም አለ በእንግሊዝኛ።ጌታሁን ታደሰ «ሁለቱም.....» ብሎ በነጠብጣብ አንጠልጥሎ ተወዉ።
የኢትዮጵያ የሰላም ሚንስትር መግለጫ
ሁለተኛዉ ርዕሥ የኢትዮጵያ የሠላም ሚንስትር ሰጡት የተባለዉ መግለጫ ነዉ።ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚወግኑ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የሠላም ሚንስትር መሐመድ ኢድሪስ «ኢትዮጵያ ዉስጥ በሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን «ዉጤማ» ያሉት ተግባር ተከናዉኗል።በዘገባዉ መሠረት ሚንስትሩ የፕሪቶሪያ ሥምምነት ከተፈረመ ወዲሕ ትግራይ ክልል የመማር-ማስተማርን ጨምሮ መደበኛ የሰዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል።«አማራ ክልልም «ከሁለት ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ የተሻለ የሰላም አየር መኖሩን» የሠላም ሚንስትሩ ተናግረዋል-እንደ ዘገባዉ።
ትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ዉጥረት፣ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የተፈናቃዮች ወደየቀያቸዉ አለመመለስ ችግር፣ ምናልባት ሌላ ጦርነት በሚያሰጋበት፣ በአማራና በኦሮሚያ የመንግሥት ኃይላትና በየክልሉ የሚገኙ ታጣቂዎች የገጠሙት ግጭት ባየለበት፣ርዕሠ ከተማ አዲስ አበባን ጭምሮ ሰዎች መታገት፣መዘረፍ ሲከፋም መገደላቸዉ በሚነገርበት መሐል የሠላም ሚንስትሩ «ሠላም ሠፍኗል» አሉ መባሉ ለብዙዎች አጠያያቂ እንቆቅልሽም ብጤ ሆኗል።
ብርሐኑ ሐለፎም «ተምታታ» ይላል።«ዜናው ሰላም ሆኗል ይላል፣ ከዛ ቀጥሎ በሚልዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት መኣድ ለቀዋል እና ተፈናቀሉ ይላል ተምታታ እኮ» የብርሐኑ ሐለፎም አስተያየት ነዉ።እሸቱ ጉዲሳ በፌስ ቡክ ጥያቄ ብጤ አለዉ «ኧረ እንዲያዉ ምን ይሻላቸዋል» የሚል ጥያቄ። በዚሕ አላበቃም «ሰው በየመንገዱ እየተገደለና እየታገተ እያዩ ሰላም ነው ማለት ምን ማለት ነው?» እንደገና ጠየቀ።ራሱ መለሰም «ፍርዱን ለእግዚአብሔር እንተወው።» ብሎ።
ዉቤ ዉብ አዲስ በበኩሉ «ሠላም ሰፈነ የምትሉት ለሠላም ምን አስተዋጾ አደረጋችሁና ነው ?? ያጠናችሁት ውሸት ነው እንዴ ??» ዉቤ ዉብ አዲስ ነዉ ጠያቂዉ።
ዑመር ፈድሉም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል-ያዉ በፌስ ቡክ።«ሰላም ለማስፈን ምንም አይነት ውጤታም ስራ አልተሰራም» የዑመር ፈድሉ አስተያየት ነዉ።አበባዉ መኳንንት የማታ ደግሞ «የሰላም ሚኒሰቴር ያላት ሀገር » ይላል ኢትዮጵያን «ግን አንድም ቀን ሰላም አግኝታ ያላደረች ሀገር» አበቃ።አብዱ ሰዒድ አጭር አስተያየት አለዉ «ሠላም እንኳ እርቆናል» የምትል።ኢስማኤል ጋሹ ገረመኝ ባይ ነዉ።እና «ማን ይታመን» ጠየቀ ኢስማኤል ጋሹ።
ዩክሬን የሩሲያ የጦር ሠፈሮችን መደብደቧና ሰስጊዉ አፀፋ
3ተኛዉ ርዕሥ ዩክሬን ባለፈዉ ዕሁድ ሩሲያ ላይ ድንገት የከፈተችዉን የሰዉ አልባ (ድሮን) ጥቃትን የሚመለከት ነዉ።የዩክሬን የሥለላ ድርጅት ባለፈዉ ዕሁድ ያዘመታቸዉ በርካታ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች አራት የሩሲያ የጦር ሠፈሮችን ደብድበዋል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳሉት ጥቃቱን ለማድረስ የሐገሪቱ የሥለላ፣ የጦርና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ከአንድ-ዓመት ከመንፈቅ በላይ ጥናት፣ዝግጅትና ሥልቱን ሲያቀለጣጥፉት ነበር።
ከዩክሬን ድንበር 4300 ኪሎ ሜትር ድረስ በሚርቁ የሩሲያ የጦር ሠፈሮች ላይ በተሰነዘረዉ ጥቃት የሩሲያ ኑክሌር ተሸካሚዎችን ጨምሮ 41 የረጅም ርቀት ተጓዥ ሥልታዊ ተዋጊ ጄቶች ተመትተዋል።ከ41ዱ 13 ሙሉ በሙሉ መጋየታቸዉን ዩክሬን አስታዉቃለች።ሩሲያ ለብቀላ እየዛተች ነዉ።
ፀሐይ ብራቅ «አልፎ አልፎም ቢሆን ጥጋበኛችን እንዲህ ማስተንፈስ ጥሩ ነው» ትለለች ወይም ይላል።ሥዩም መኮንን ግን በፌስ ቡክ «አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች!!» እያለ ቀጠለ፣ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልዶሜር « ዜለንስክይ የዉሸት እርዳታ ተማምኖ አንበሳውን (የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር )ፑቲን ነካክቶ ዋጋውን እያገኘ ነው!!!» ሥዩም መኮንን ነዉ-ይሕን ባዩ። አንተነሕ አንተነሕ «አፀፋዉ እጅግ ይከፋል።ምናልባትም ኔቶን ጭምር ወደ ጦርነቱ ጎትቶ የሚያስገባ ነው።» አለ።ገብረ ሺፍቴ የዩክሬንን ርምጃ «የልጅ ሩጫ» በማለት ተሳልቆበታል።
ተሾመ ወልዴ በፌስ ቡክ «የሩሲያን አፀፋ ሳስበው ይሰቀጥጣል» ይላል «ፀሎቴ ጓድ ፑቲን ኒዩክሌር እንዳይጠቀም ነው።»መለሰ ሙዜ ሆራንሶም ተመሳሳይ ሥጋት አለዉ።«ምላሹ አፈር ድሜ የሚያበላ ሊሆን ይችላል፡፡ አባባሰች በሉት» መለሰ ሙዜ ሆራንሶ ነዉ-ይሕን ባዩ።ሰዓዳ ቼማ መሐመድ ሁሉ-በፌስ ቡክ እንደፃፈችዉ ለሁሉም ማረጋገጪያ ትጠይቃለች።«ወላሒ በሉ እስቲ» አለች ሰዓዳ።የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት-የዛሬዉ አበቃ።።ኢድ ሙባረክ።
ነጋሽ መሐመድ ነኝ
ሸዋዬ ለገሰ