የመራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ የ100 ቀናት የስልጣን ጊዜ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2017በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 6 ቀን 2025 ዓመተ ምኅረት ነበር የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፍሪድሪሽ ሜርስን በመራኄ መንግስትነት የመረጠው። ሜርስ ከቀድሞዎቹ የመራኄ መንግስት ምርጫዎች በተለየ ጊዜ በወሰደ ምርጫ ነበር ለዚህ ኃላፊነት የበቁት። የእርሳቸው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ (CDU) 6 አባላት ድምጽ ነፍገዋቸው በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ባይሳካላቸውም ከብዙ ውይይት በኋላ በእለቱ በተካሄደ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ቀንቷቸው ተመርጠዋል ። ሜርስ ኃላፊነቱን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ እና ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ጋር ወደ ዩክሬን ተጉዘው ለዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ አጋርነታቸውን አረጋገጡ። በሰኔ መጀመሪያ ላይ በዋይት ሀውስ ከአሜሪካን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተነጋገሩ። በንግግሩም አንዳንድ መሪዎች ዋይት ሃውስ ሲጋበዙ ያጋጠማቸው ዓይነት ማሳጣት አልደረሰባቸውም። ጥሩ አቀባበልም ነበር የተደረገላቸው። በአውሮጳ ኅብረትና በሰሜን አትላንቲክ የጋራ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጉባኤዎች ላይም እንዲሁ አዎንታዊ አቀባበል እንደተደረገላቸው የዶቼቬለው የንስ ቱራው በዘገባው አስታውሷል።
ጀርመን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር፣ የዩክሬንን በከፍተኛ ደረጃ የምትደግፍ አገር ናት። ምንም እንኳን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው አርብ በአላስካ ዩናይትድ ስቴትስ ባካሄዱት ጉባኤ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪም ሆነ አንድም የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገር ባይጋበዝም ሜርስ አውሮፖች፣ ዩክሬንና ኔቶ የተካፈሉበት ጉባኤ እንዲካሄድ አድርገዋል። ትራምፕም በጉባኤው ላይ በስልክ ተሳትፈዋል። በዚህም «አውሮጳንና ጀርመንን አትርሱ» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ትናንትም ሜርስ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ፣ ከጣልያንዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅዮ ሜሎኒ ከአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን እንዲሁም ከኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ ጋር ዋሽንግተን በመሄድ በዩክሬን ጉዳይ ላይ ዜሌንስኪም ባሉበት መክረዋል።
በዚህ ያላሰለሰ ጥረታቸው ቦታ የተሰጣቸው ሜርስ በሚሰጡት አስተያየት አልፎ አልፎ በቃላት ምርጫቸው መተቸታቸው አልቀረም። እስራኤል ኢራንን ከደበደበች በኋላ ሜርስ የሰጡትን ይህን አስተያየት የዶቼቬለው የንስ ቱራው በምሳሌነት አንስቷል።
«ይህ እስራኤል ለሁላችንም የምታከናውንልን ቆሻሻ ስራ ነው። እኛም በዚህ አገዛዝ ተጽእኖ ደርሶብናል። ይህ የሙላ አገዛዝ ከሂዝቦላና ከሀማስ ጋር በጥቃቶች በግድያ እና በጭፍጨፋ ለዓለም ሞትና ጥፋት ነው ያመጣው። »እስራኤልን እንዲህ ያወደሱት ሜርስ ባልተለመደ ሁኔታ ደግሞ ጦሯ በጋዛ ሰርጥ የሚወስደውን እርምጃ መረዳት አለመቻላቸውን በግልጽ ተችተዋታልም። በዚሁ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሜርስ እስራኤል ለጋዛው ጦርነት የምታውላቸውን የጦር መሣሪያዎች መንግስታቸው ማቅረብ እንደሚያቆም የፓርቲያቸውን አባላትንም ሆነ ተጣምረው መንግሥት የመሰረቱትን አጋሮቻቸው ብዙም ሳያማክሩ መወሰናቸው ግርግር አስከትሎ ነበር።
ሜርስ በ100 ቀናት ውስጥ በውጭ ፖሊሲ ረገድ ያከናወኗቸውን ተግባራት ወደ ኃላ መለስ ብለው የቃኙት የሕግ ባለሞያ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንቅስቃሴያቸውን አዎንታዊ ሲሉ ነው የገመገሙት ። በርሳቸው አስተያየት የሜርስ ግርማ ሞገስ ተሰሚነትም አትርፎላቸዋል።ከሜርስ በፊት ጀርመንን ተጣምረው ሲመሩ የነበሩት የሶሻል ዴሞክራቶች ፣የአረንጓዴዎቹ እና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲዎች አለመስማማት፣ የህዝቡ መከፋፈል እንዲሁም የቀኝ ጽንፈኞች መጠናከር ፣እንደ ቱራው ዘገባ «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው የጀርመን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ በየካቲት ወር በተካሄደው የጀርመን ምርጫ 20.8 በመቶ ድምጽ ለማሸነፍ አስችሎታል። ውጤቱም በቀደመው ምርጫ ፓርቲው ካገኘው ድምጽ በእጥፍ የላቀ ነበር። ፓርቲው ስደተኞች በብዛት ወደጀርመን መግባታቸውን በጽኑ የሚቃወም እና ይህም ሰፊ ድጋፍ ያስገኘለት አቋሙ ነው።
ያኔ ሜርስ የጀርመን ዴሞክራሲን መታደግ የሚችሉ የመጨረሻው እድል ናቸው ሲሉ ታዛቢዎች ይናገሩ ነበር ። የሥልጣን መንበሩን የተቆናጠጡት ሜርስ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ቃል በገቡት መሠረት በጀርመን ድንበሮች በሙሉ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላለፉ ይህ እርምጃ ተግባራዊ የሆነውም ወደ ጀርመን የሚመመጡ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ነው። ሆኖም በዚህ አሰራር ጀርመን በተለይ ተገን እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ስደተኞችን ከድንበር ላይ ማባረሯ ራሱ ሕገ-ወጥና የአውሮፓ ኅብረትን ደንቦች የሚጥስ አሰራር ነው የሚሉ ተቃውሞዎች ከስደተኞች መብት ተሟጋቾችና ከአውሮፓ ኅብረት ጭምር አስነስቶባታል። ጀርመን ግን ይህን ትቃወማለች ። የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንት ለነዚህ ክሶች በሰጡት መልስ «ወደ ሀገራችን ማን እንደሚገባ የምንወስነው እኛ እንጂ ወንጀለኞች ሊሆኑ አይገባም» ብለዋል።
«አውሮጳ ለመላው ዓለም ክፍት የሆነ አህጉር ነው። የአውሮጳ ኅብረት ለመላው ዓለም ክፍት የሆነ አህጉር ነው። እኛም ክፍት የሆንን አገር ሆነን እንቀጥላለን። ሆኖም ወደ እኛ የሚመጣውን ሰው ሕገ-ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች፣ ደላላዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች ፣ እንዲወስኑልን አንፈልግም። እኛ የምንፈልገው ወደአውሮጳ የሚካሄደው ሕጋዊውን ጉዞ ለፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተገዥ እንዲሆን እንጂ በወንጀለኛ ቡድን እጅ እንዲወድቅ አንፈልግም።»
አዲሱ መንግሥት ስልጣን ከመያዙ አስቀድሞ የቀድሞው ምክር ቤት ስራውን ከማቆሙ በፊት የጀርመንን ጥብቅ የብድር ሕግ የሚለውጥ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ተደርጎ ነበር።ይህም መንግስት በመጪዎቹ ዓመታት ተጨማሪ 500 ቢሊዮን ዩሮ የሚያገኝበትን መንገድ አመቻቷል። የጀርመን መከላከያን መልሶ ለማስታጠቅ ፣ ለመሠረተ ልማት እድሳት፣ ለአዳዲስ መንገዶችና እና ለባቡር ሀዲድ እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች ግንባታና ለአካባቢ ጥበቃም ገደብ ያልተቀመጠበት ተጨማሪ 500 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ታስቧል። በምርጫ ዘመቻው ወቅት ወግ አጥባቂዎቹ CDU እና CSU ጥብቅ የብድር ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር ።
በዚህ የአሰራር ለውጥ ላይ አዲሱ የፋይናንስ ሚኒስትር ላርስ ክሊንግባይል ለሀገሪቱ ፓርላማ እንዳስረዱት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጀርመን የበለጠ መዋለ ንዋይ እንድታፈስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን እንዲሁም ቡድን ሰባት ጀርመን የብድር ሕጓን እንድታላላ ሲጠይቁ መቆየታቸውን አንስተዋል። በስተመጨረሻ እነዚህን መሰናክሎች መቀነሳቸውን እና ከመቼውም በላይ ሀገሪቱ ለወደፊቱ ዋስትናዋ ይበልጥ ገንዘብ እያፈሰሰች መሆኑን አስረድተዋል። እዚህም ላይ የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ አስተያየታቸውን አካፍለውናል።
ምንም እንኳን የሜርስ መንግስት ድምጹ ሳይሰማ ፓርላማው የበጋ እረፍት ከመውጣቱ በፊት የሚያካሂደው የመጨረሻው ስብሰባ ላይ ቢደርስም በሕገ መንግስታዊው ፍርድ ቤት እጩ ዳኞች ምርጫ ላይ ገዥዎቹ ፓርቲዎች እንደ ከዚህ ቀደሞቹ መንግሥታት በመቻቻል ማሳካት ሳይችሉ ቀርተው ነበር። አብዛኛዎቹ የወግ አጥባቂዎቹ የCDU እና CSU አባላት የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ያቀረባቸውን እጩ መቃወማቸው ግርግር አስነስቶ ምርጫው ለጊዜው ተሰርዟል። ለውድድር የታጩት ፍራውከ ብሮሲዩስ ጌርስዶርፍም ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል። በዚህ ሰበብም የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አዲስ እጩ ማቅረብ ይኖርበታል። ለአሁኑ ግን ከወግ አጥባቂዎቹ በኩል የተነሳው ተቃውሞ በአንድ መቶ ቀናቱ የመንግስት ቆይታ ላይ ጥላ ማጥላቱ አልቀረም ።
ኂሩት መለሰ
ልደት አበበ