የሐምሌ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሐምሌ 7 2017የቡድኖች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ቸልሲ ፓሪ ሳንጃርሞን ትናንት በአስደናቂ ሁኔታ 3 ለ0 አሸንፎ 40 ሚሊዮን ዶላር ተቀብሏል፥ ተሸናፊው ፓሪ ሳንጃርሞም 30 ሚሊዮን ዶላር ደርሶታል ። እጅግ ትርፋማ ከነበረው አጠቃላይ ውድድር 2 ቢሊዮን ዶላር መሰብሰቡ ተዘግቧል ። ለመሆኑ ፓሪ ሳንጃርሞን ምን ነካው? የፓሪስ ነዋሪዎችስ ምን አሉ? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። እድሜያቸው ከ20 እና 18 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ለአፍሪቃ አትሌቲክስ ፉክክር ወደ ናይጄሪያ አቅንቷል ። ተጨማሪ ዘገባዎችንም አካተናል ።
አትሌቲክስ
ከረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን፣ 2017 ዓ.ም እስከ እሁድ ሐምሌ 13 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ድረስ በናይጄሪያ አቡከታ እድሜያቸው ከ20 እና 18 ዓመት በታች የአፍሪቃ አትሌቲክስ ፉክክር ይከናወናል ። ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የመጀመሪያው ተጓዥ ዛሬ ማለዳ ወደ ናይጄሪያ አቡኩታ ማምራቱ ተዘግቧል ። የኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የወጣቶች አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን ዛሬ እኩለ ሌሊትም ወደ ናይጄሪያ እንደሚጓዝ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጧል ።
የዘንድሮ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የፈረንሣይ ሊግ፤ የፈረንሳይ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች ዋንጫ አሸናፊ ነበር፤ ፓሪ ሳንጃርሞ ። ኢንተር ሚላንን 5 ለ0 አደባይቶ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳው ቡድን ፒኤስጂ ግን ትናንት በቸልሲ ጉድ ሁኗል ። በቡድኖች የዓለም ዋንጫ በቸልሲ እጅግ ተበልጦ 3 ለ0 ተሸንፏል ። ቸልሲ ዘንድሮ በኮንፈረንስ ሊግ ሪያል ቤቲስን 4 ለ1 ድል አድርጎ ዋንጫ ያነሳ ቡድን ነው ።
ቸልሲ የቡድኖች የዓለም ዋንጫን ወሰደ
የቡድኖች የዓለም ዋንጫ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፊፋ ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር በመሆን ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሜዳሊያዎችን እና ዋንጫዎችን ለተጨዋቾች ሸልመዋል ።
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና ዶናልድ ትራምፕ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሜዳሊያዎችን እና ዋንጫዎችን ለተጨዋቾች ሸልመዋል ። የቡድኖች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ፓሪ ሳንጃርሞን ትናንት በአስደናቂ ሁኔታ 3 ለ0 አሸንፎ የወሰደው ቸልሲ 40 ሚሊዮን ዶላር ተቀብሏል፥ ተሸናፊው ፓሪ ሳንጃርሞም 30 ሚሊዮን ዶላር ደርሶታል ። እጅግ ትርፋማ ከነበረው አጠቃላይ ውድድር 2 ቢሊዮን ዶላር መሰብሰቡ ተዘግቧል ።
የሜዳ ቴኒስ
በሐምቡርግ የአውሮጳ የቴኒስ መክፈቻ የሜዳ ቴኒስ ዛሬ ተከናውኗል ። በሴቶች ውድድር፦ የፈረንሳዩዋ ዲያነ ፓሪ የክሮሺያዋን ታራ ቩርዝ 7 ለ6 እባ 11 ለ9 አሸንፋለች ። በወንዶች የማጣሪያ ፉክክር ደግሞ የኦስትሪያው ፊሊፕ ሚሶሊች የስዊድኑ ዖሌ ዋሊንን 7 ለ6 እና 6 ለ2 ድል አድርጓል ። የብራዚሉ ቲያጎ ሞንቴሪዮ ደግሞ የሉታኒያውን ቪሊዩስ ጋውቡስን 6 ለ2 እና 6 ለ3 ድል አድርጓል ። የሰኔ 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ስለ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ ከሃይማኖት ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ መጠይቅ በድምፅ ማድመጥ ይቻላል
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሃይማኖት ጥሩነህ