ሀዋሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ሻረ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ሻረ ፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ምርጫ ቦርድ በከሳሽ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ከሥልጣን ገደቡ ውጪ የሆነ ፣ ሕጉን እና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የሚጻረር ሆኖ በመገኘቱ ነው ብሏል ፡፡ ፍርድ ቤቱ ለተከራካሪ ወገኖች በሰጠው የፍርድ ውሳኔ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተራ ቁጥር 1 ተከሳሽነት ተጠቅሷል ፡፡ ቦርዱ የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት ፣ የአገሪቱን ሕጎች እና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ በመጣስ ጣልቃ ገብ ውሳኔዎችን አሳልፏል በሚል አቤቱታ እንደቀረበበት በፍርድ ቤቱ የውሳኔ መዝገብ ላይ መጠቀሱን ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሀዋሳ ዘግቧል።
ዶቼ ቬለ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስመልከቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ሆኖም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት በአንደኛው የፓርቲ ወገን ውስጥ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገነነ ሀሰና ውሳኔውን “ ተገቢ “ ብለውታል ፡፡
“ መጀመሪያም ህጉን ተከትለን ነው የሄድነው ምርጫ ቦርድም ጣልቃ እንዳይገባብን በተደጋጋሚ ሰንጠይቅ ነበር “ ያሉት አቶ ገነነ “ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ክስ ለመሄድ ተገደናል ፡፡ ውሳኔውም ተገቢ እና የጠበቅነው ነው ፡፡ በቀጣይ ቦርዱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚ ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን “
በሌላኛው ወገን የሚገኙት የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የቀረቡ ማስረጃዎችን ከግምት ያላስገባ ነው ሲሉ በመቃወም ለሚቀጥለው የፍትህ አካል ይግባኝ እንላለን “ ብለዋል ፡፡ዝርዝሩ በዜና መጽሔት ዝግጅታችን ይቀርባል።
ኬፕታውን የነዳጅ ዋጋ ንረት ባስነሳው ተቃውሞ 22 ሰዎች ተገደሉ
የአንጎላ መንግሥት የነዳጅ ዘይት ዋጋ ለመጨመር መወሰኑ ባስነሳው ተቃውሞ ቢያንስ 22 ሰዎች በዚህ ሳምንት መገደላቸውን አሳወቀ ።የአንጎላ ፕሬዝዳንት ቢሮ ትናንትባወጣው መግለጫ ከሰኞ አንስቶ ለሁለት ቀናት በዘለቀው በዚሁ ተቃውሞ197 ሰዎችም መቁሰላቸውን፣ ከ1,200 በላይ ደግሞ መታሰራቸውን ገልጿል። የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጃኦ ላውሬንሶ ቢሮ እንዳለው በተቃውሞው ወቅት በተካሄዱ አመጾች በርካታ ሱቆች ተዘርፈዋል፤መኪናዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ስርዓት ለማስከበርም ጦር ሠራዊቱ ተሰማርቶ እንደነበርም ቢሮው ባወጣው መግለጫ ተጠቅሷል። ሰዎቹ እንዴት እንደተገደሉ ግን ያለው ነገር የለም። በነዳጅ ዘይት በበለጸገችው በደቡብ አፍሪቃዊቷ አገር አንጎላ፣ የተከሰተው ተቃውሞ ከዋና ከተማዋ ከሉዋንዳ ተነስቶ ስድስት ሌሎች ግዛቶችንም አዳርሷል። አንድ የመብት ተቆርቋሪ የችግሩ መንስኤ መጥፎ ያሏቸው መንግስት የሚከተላቸው ፖሊሲዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ዓመታት መጥፎ ፖሊሲዎች እና እንደ አሁኑ ዓይነት መዘዛቸው ስለ ውድቀቱ እና ስለ ድኅነቱ ስንናገር ነበር። እናም ይህ በማንኛውም ከድኅነት ወለል በታች የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት ማኅበረሰብ የሚሆን ነገር ። »
የተቃውሞው መነሻ በሐምሌ መጨረሻ ላይ መንግስት ለናፍጣ ያደርግ የነበረው ድጎማና እንደሚያነሳና ዋጋውንም ከ30 በመቶ በላይ እንደሚጨምር ማሳወቁ ነው። ይህም አንጎላውያን በብዛት የሚጠቀሙበት የሚኒባስ ታክሲዎች ዋጋ በ50 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል።ተቃውሞው መጀመሪያ የተቀሰቀሰው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ።ያኔም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩመን ራይትስ ዋች ፖሊስ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል ሲል ከሶ ነበር።
ፓሪስ የተመድ የኮንጎው አማፂ M23 በርካታ ገበሬዎች ገደለ
የተመድ የኮንጎው አማፂ M23 በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በርካታ ገበሬዎችን ገደሏል ሲል አስታወቀ። ድርጅቱ ባወጣው ዘገባ መሠረት M23 በዚህ ወቅት በምስራቅ ኮንጎ በገበሪዎችና በሌሎች ሲቭሎች ላይ በፈጸመው ጥቃት169 ሰዎች ተገድለዋል ። የM23 መሪ ቤርትራንድ ቢሲምዋ ግን ድርጅቱ ቡድናቸው ፈጽሟል ያለውን ግድያ እንደሚያጠራ ገልጸው ሆኖም ዘገባው የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊሆን ይችላልም ብለዋል። ሮይተርስ ግድያውን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ባይችልም አንድ ስሙን ያልጠቀሰው የአካባቢው የመብት ተቆርቋሪ የM23 ተዋጊዎች በሽጉጥና በገጀራዎች በርካታ ሲቭሎችን ገድለዋል ሲል የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ መናገሩን ዘግቧል።
ግለሰቡ አማጺው M23 ከ100 በላይ ሲቭሎችን በተለይም የሁቱ ገበሬዎችን ገድሏል ብሏል። ገበሬዎቹ M23 ይዞታውን ሲያሰፋ አካባቢያቸውን ለቀው ሄደው ነበር ሆኖም ቡድኑ ለደኅንነታቸው ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ወደ አካባቢው ተመልሰው ነበር። ያነጣጠረውም መቀመጫውን ኮንጎ ያደረገው እና በጎርጎሮሳዊው 1994 የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል የሚባሉትን የቀድሞ የሩዋንዳ ጦር አባላትንና ሚሊሽያዎችን ያካተተው ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ለሩዋንዳ ነጻነት በእንግሊዘኛው ምህጻር FDLR የተባለው ቡድን አባላትነት በተጠረጠሩት ላይ ነበር። የተገደሉትም M23 እና የኮንጎ መንግስት በአካባቢው ሰላም ለማውረድ ቃል ገብተው ነበር ። M23 በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገደሉበትና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በተፈናቀሉበት በዚህ ዓመት ባካሄደው ውጊያ ከከዚህ ቀደሙ በተለየ ተጨማሪ ግዛቶችን ይዟል። የተመድ ዘገባ እንደሚለው የገበሬዎቹ ግድያ የተጀመረው በጊርጎሮሳዊው ሐምሌ 9 በሰሜን ኪቩ ግዛት ሩትሹሩ በተባለው አካባቢ ነው።
በርሊን እስራኤል በፍልስጤም ጉዳይ እየተገለለች ነው ስትል ጀርመን አስታወቀች
በጋዛው ሰብዓዊ ቀውስ እና አንዳንድ ሀገራትም ለፍልስጤም መንግስት እውቅና ለመስጠት በሚያደርጉት ግፊት እስራኤል የሚደርስባት ዲፕሎማሲዊ መገለል እየጨመረ ነው ስትል ጀርመን አስታወቀች። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሀን ቫደፉል ዛሬ ወደ እስራኤል ከመሄዳቸው በፊት በሰጡት መግለጫ የእስራኤልና የፍልስጤማውያን ግጭትን ለመግታት የሁለት መንግሥታት መፍትሄ ላይ የሚነጋገረው የተመድ ጉባኤ እስራኤል ይበልጥ ራሷን ከአናሳዎች ጎራ ውስጥ የምታገኝበት መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።በመጪዉ መስከረም ኒዮርክ ላይ የሚሰየመዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ሥለ ሁለት መንግሥታት በሚነጋገርበት ወቅት እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ እንደማይካፈሉ አስታዉቀዋል።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐገራቸዉ ለፍልስጤም የመንግሥትነት ዕዉቅና መሰጠት ያለበት የሁለት መንግስታት መፍትሔ ድርድር ሲያበቃ ነው ብላ ታምናለች።ይሁንና እስራኤል በኃይል የያዘችዉን የፍልስጥም ግዛት ለመጠቅላል የእስራኤል ሁለት ሚንስትሮች ያሰሙት ዛቻ ጀርመን የተናጥል የዕዉቅና እርምጃ እንድትወስድ ሊያደርጋት እንደሚችል ሚንስትሩ ጠቁመዋል።
ቫደፉል በእስራኤል ቆይታቸው ከእስራኤል አቻቸው ጌድዮን ሳርና ከእስራኤል ፕሬዝዳንት ኢሳክ ሄርዞግ እንዱህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ወደ ዌስትባንክ በመጓዝም ከፍልስጤማውያን አስተዳደር ባለሥልጣን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋርም ይነጋገራሉ ተብሏል።
ኪቭ በሩስያ የአየር ድብደባ በኪቭ ቢያንስ 8 ሰዎች ተገደሉ
ሩስያ ዛሬ ኪቭ ላይ በፈጸመችው የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምነት ሰዎች ተገደሉ። የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ዛሬ ሲነጋጋ በደረሰው በዚህ ጥቃት ከሞቱት መካከል አንድ የስድስት ዓመት ልጅ ይገኝበታል። ሌሎች 88 ሰዎችም ቆስለዋል። ከነዚህ ውስጥ ዘጠኙ ህጻናት ናቸው።የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በዋና ከተማይቱ ጠዋት ከተፈጸመው ከዚህ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ሲፈልጉ ነበር። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ሩስያ በዛሬው ጥቃት ከ300 በላይ ድሮኖችን ስትጠቀም 8 ሚሳይሎችንም አስወንጭፋለች። ዜሌንስኪ በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክት ከአሜሪካና ከአውሮጳ ጋር ለምናሳየው የሰላም ፍላጎት ሩስያ የሰጠችውን ምላሽ ዓለም ዛሬ እንደገና አይቷል ስለዚህ ሰላም ያለ ጥንካሬ ሊመጣ አይችልም ሲሉ ጽፈዋል።የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የዛሬው ጥቃት ዒላማ የዩክሬን ወታደራዊ የአየር ጥቃት ይዞታዎች እና የጦር መሣሪዎች መጋዘኖች እንዲሁም ከክየቭ የወታደራዊ ኢንዱስትሪ ማዕከላት ጋር የተያያዙ ያለቻቸው ንግዶች ጭምር ናቸው። ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አላደርግም የምትለው ሩስያ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከውጊያው ግንባር ራቅ ያሉ የዩክሬን ከተሞች ላይ የአየር ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች ። የዩክሬን ባለስልጣናት እንደሚሉት ግን ዛሬ በ27 ስፍራዎች በተካሄደው ድብደባ ጉዳት ከደረሰባቸው ህንጻዎች መካከል ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ይገኙበታል።
ሞስኮ ከዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ዳግም የመሬት መንቀጥቀጥ ቀጥሏል
የሩስያውን የካምቻትካ ልሳነ ምድር ካራደው የመሬት መንቀጥቀጥ አንድ ቀን በኋላ ዛሬ ፣ሌሎች ዳግም የመሬት መንቀጥቀጦች ቀጥለዋል። የሩስያ መንግስት ዜና አገልግሎት ታስ እንደዘገበው ፓራሙሽር በተባለው ደሴት ላይ በሚገኘው ስቬሮ ኩርሊስክ በተባለው ከተማ በሬክተር ስኬል መለኪያ 6 እና 5.6 የተመዘገቡ ሁለት የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰዋል። የስቬሮ ኩርሊስክ ከተማ ትናንት ካማቻትካን የመታው በሬክተር መለኪያ 8.8 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ባስከተለው የሱናሚ ወጀብ በተደጋጋሚ ተመቶ ነበር ። በአካባቢው የተከሰተው የትናንቱ መሬት መንቀጥቀጥ ፓስፊክ ውቅያኖስን ከሚያዋስኑት ከጃፓን ቻይና እና፣ ፊሊፒንስ አንስቶ እስከ ሀዋይ ምዕራባዊ የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ዳርቻ እንዲሁም ሜክሲኮና ኤኳዶርን ከመሳሰሉ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ድረስ ለሚገኙ ነዋሪዎች የሱናሚ ማስጠንቀቂያ አሰጥቶ ነበር። ሩቅ ምሥራቅ ሩስያን የመታው የትናንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ስላደረሰው ጉዳት እስከዛሬ ከሰዓት በኋላ ድረስ የተባለ ነገር እንደሌለ የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር