ውዝግብ የበዛበት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 23 2017
«ሁሉም፤ ሁሉም፤ የበለጠ መሥራት አለበት። ከፍተኛ ብክለት የሚያስከትሉት የቡድን 20 ሃገራት እዚህ ጋ መጥተው የየራሳቸውን ድርሻ መጫወት ይኖርባቸዋል።» የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተረሽ የምድራችን የሙቀት መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን የሚያመላክቱ ተፈጥሯዊ ክስተቶች እየተደጋገሙ ነው። ይህ ያሳሰባቸው ወገኖች የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ገደብ እንዲበጅለት የሚያደርገውን እርምጃ በጋራ መውሰድ ይገባል ይላሉ።
የፓሪሱ የአየር ንብረት ውል
በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ከተካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP 21 ማጠቃለያ የምድራችን ሙቀት ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ የሚያደርግ እርምጃን የተመለከተ ስምምነት ተፈረመ። ይህን ስምምነት የፈረሙት 196 ሃገራት የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ቃል በመግባት በተለይ በኢንዱስትሪ ያደጉት የበለጠና ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተው ነበር። ከምድራችን ግንባር ቀደም ከባቢ አየር በካይ ሃገራት ከቻይና ቀጥላ የምትጠቀሰው ዩናይትድ ስቴትስ ምንም እንኳን የውሉ ፈራሚ ሀገር ብትሆንም የአየር ንብረት ለውጥ ተረት ተረት ነው ብለው የማይቀበሉት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ፕሬዝደንትነት ሥልጣኑ ሲመጡ ዋሽንግተንን ከዚህ ስምምነት በይፋ አስወጥተዋል። እርምጃቸው የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመቀልበስ የሚያደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳደረገው እየተገለጸ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ይዞት የመጣው ፖሊሲ ካስከተለው መልክአ ምድራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ስጋት በተጨማሪ የአየር ንብረትን የሚመለከተው አካሄዱ ሌሎች ሃገራት በአንድ መድረክ ተሰባስበው እንዲመክሩ ግድ ብሏል።
የበርሊኑ የአየር ንብረት ውይይት መድረክ
ባለፈው ሳምንት በርሊን ላይ 40 ሃገራት የተሳተፉበት በአየር ንብረት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱ በመጪዉ ዓመት ኅዳር ወር ብራዚል ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP 30 አጀንዳዎችን ማስተካከሉ ነው የተነገረው። ጉባኤውን ያስተናገዱት ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ የተሻለ ጥረት የሚደረግባት ጀርመን ባለሥልጣናት የአየር ንብረት ለውጥን መካድ ነባራዊ እውነታውን አይለውጠውም እያሉ ነው። ተሰናባቹ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ፤
«ዩናይትድ ስቴትስ ከስምምነቱ መውጣት በመፈለጓ በጣም አዝናለሁ። ሆኖም ግን አንድ ነገር ግልፅ ነው፤ እውነታውን መካድ እናችላ ማለት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን መዘዝ ወይም ዩናይትድ ስቴትስ በከፍተኛ የበካይ ጋዞች ልቀት ያለባትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲጠፋ አያደርገውም።»
ሾልስ አክለውም፤ «ሰው ሠራሽ የአየር ንብረት ለውጥን መዋጋት የሁሉም አስፈላጊ የደህንነት ፖሊሲ ከሆኑ ጉዳዮች ነው ወዲፊትም እንዲሁ እንደሆነ ይኖራል ብለዋል። ይህ ደግሞ በአየር ንብረት ተሟጋቾች ብቻ ሳይሆን በስለላ ተቋማት ሁሉ የተረጋገጠመሆኑን አመልክተዋል። በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት ስለደኅንነት የሚያስብ ሁሉ ስለ አየር ንብረት ሁኔታም እንደሚያስብ ማመላከቱንም ጠቁመዋል።
የትራምፕ ውሳኔ ተጽዕኖ
ከፓሪሱ የበካይ ጋዞች ልቀት መጠን ቅነሳ ታሪካዊ ስምምነት በኋላ ሃገራት በትብብር ተግባራዊ ለማድረግ ያደርጉት የነበረው የጋራ እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት መሻሻይ እያሳየ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ። በመካከሉ ወደ ዋሽንግተን የሥልጣን መንበር ብቅ ያሉት ትራምፕ በመጀመሪያው የምርጫ ዘመናቸውም ተመሳሳይ አወዛጋቢ እርምጃ ለመውሰድ ቢወስኑም የአራት ዓመት የሥራ ጊዜያቸው ሲያበቃ ዳግም አሜሪካ አብራ ለመሥራት መጥታ ነበር። አሁን ለሁለተኛ ጊዜ የወሰኑት ውሳኔ እንደገና ጥረቱን ወደማደናቀፉ ተመልሷል።
በጀርመን የግሪን ፒስ ዋና ዳይሬክተር ማርቲን ካይዘር፤ የትራምፕ ድጋሚ መመረጥ እና የወሰዷቸው እርምጃዎች ለአየር ንብረት የሚደረገውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ጥልቅ ቀውስ ውስጥ ከቶታል ይላሉ። ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የተፈጥሮ ተቆርቋሪው በዓለማችን የትልቁ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነች ሀገር በበርሊኑ የውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ አለመሳተፍንም ትልቅ ውድቀት ብለውታል።
ትራምፕ ለወሰዱት እርምጃ በግንባር ቀደም ምክንያትነት ያቀረቡት አሜሪካንን ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል ነው። ጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው የሚሉ ወገኖችን ክፉኛ ነው የተቹት። እሳቸውና የፖለቲካ ጓዶቻቸው በጀርመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡንደስታኽ በዚህ ረገድ ያደረጉትን ጥረት እንዲህ ገልጸዋል።
«እንደ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች በጋራ በምክር ቤት/ቡንደስታኽ/ ለአየር ንብረት ጥበቃ ተጨማሪ 100 ቢሊየን ዩሮ እንዲመደብ መንገዱን አመቻችተናል። ሆኖም ግን ወደ ፊት ወደ ጽዱ ኤኮኖሚ የሚደረገው ሽግግር ለሁላችንም ትልቅ ሥራ ሆኖ ይቆያል፤ ምክንያቱም ገንዘብ ማውጣት ብቻ አይደለምና። እነዚያ ለአየር ንብረት ጥበቃ የሚደረጉ የገንዘብ ፍሰቶች ለሁሉም ጠቃሚ መሆናቸው ግልጽ መሆን አለባቸው።»
እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሃገራት ከስምምነቱ መውጣታቸው፤ የራሳቸው ውሳኔ ነው፤ ነው ያሉት ቤርቦክ። ሆኖም ግን ጀርመንም ሆነች ሌሎች ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ሃገራት ጽዱ ኤኮኖሚ ላይ አተኩረው ለሚሠሩት ሥራ ተባባሪ ኩባንያዎችን በአውሮጳም ሆነ ላቲን አሜሪካ እንዲሁም አፍሪቃ ውስጥ ለመጠቀም እንደሚፈልጉ ግልጽ አድርገዋል።
የአየር ንብረትን የመጠበቅ እርምጃ
የተመ የልማት መርኀግብር UNDP እና የኤኮኖሚ ትብብር ድርጅት OECD በጋራ ይፋ ያደረጉት ጥናት የአየር ንብረት ፖሊሲዎች እና ጽዱ የኃይል ምንጭ ላይ ትኩረት ያደረገ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፤ ምርታማነትን እና ፈጠራን በማበረታታት የበካይ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ያስችላል ነው ያለው።
የአየር ንብረትን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ መቀዛቀዝ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ መዋዕለ ንዋይ ፍሰቶችን በማጓተት፤ ዘላቂ ኤኮኖሚን በማዳከም ከባቢ አየር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እንደሚጨምር አመልክቷል።
ወቅቱን ባልጠበቀ ኃይለኛ ዝናብ እና ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ የሚቸገሩ ሃገራት ዋና መንስኤ ነው የሚሉትን የበካይ ጋዞች ልቀት ውጤት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች ለመቋቋም አቅም እንዳነሳቸው በየመድረኩ ከመግለጽ አላቋረጡም።
ጥናቱ እንዳመለከተው ማንኛውም እድገት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ አስተዋጽኦዎች የሚወሰን ነው። በጎርጎሪዮሳዊው 2035 ዓ,ም ከታሰበው ግብ ለመድረስ ደግሞ ቢያንስ ከመጪው ኅዳር ወር በፊት እያንዳንዱ ሀገር የሚጠበቅበትን የየበኩሉን እቅድ ናቅረብ ይኖርበታል። እስካሁን ይህን ማድረግ የቻሉ በጣም ጥቂት ሃገራት ናቸው። የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም በትብብር መሥራት ወሳኝ መሆኑ ነው የተናገሩት።
«የተከበራችሁ፤ እነዚህን ግቦች ማሳካት የምንችለው ከመንግሥታት፤ ከኅብረተሰቡ እና ከየዘርፎቹ ጋር መተባበር ከቻልን ብቻ ነው። ወደ ኋላ የሚቀሩት ቁርጠኝነታችንን ከፍ አድርገን ወደፊት ለመራመድ እንጂ ተስፋ እንድንቆርጥ ምክንያት ሊሆኑን አይገባም።»
ለከባቢ አየር የጋራ ጥረት
የካርቦን ዳይኦክሳይድ ቅነሳ መጠንን በተመለከተ አሁን ቀሪዎቹ ሃገራት የአውሮጳ ኅብረትና ቻይናን እየጠበቁ ነው የተባለው። ብራዚል ከወዲሁ እንዶቿን ለመቀበል ዝግጅት ጀምራለች። ይህን ሀላፊነት የተቀበሉት ጉባው የሚካሄድባት የቤሊም ከተማ ከንቲባ ተሰብሳቢዎቹ ቅንጡ ሆቴልና ሪዞርት ከፈለጉ በአውሮጳ ከተሞች ይፈልጉ እኛ እዚህ ከተፈጥሮ ጋር እናገናኛቸዋለን ብለዋል። ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ አማዞን ውስጥ ሲካሄድ የመጀመሪያ ነው የሚሆነው። በርካቶች ጉባኤው ጥቅጥቅ ደን ባለበት ስፍራ መካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚኖረውን ቁልፍ ሚና በተምሳሌትነት ለማመላከት ነው ባይ ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖው በየቦታው የሚታይ ከሆነ ውሎ አድሯል። ሆኖም በጋራ ጥረት ካልተደረገ በቀር ማንም ለብቻው መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል የብራዚሉ መጪው ጉባኤ ፕሬዝደንት ከወዲሁ አሳስበዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ