ወደ ዩክሬን የሰላም አስከባሪ ጦር የመላክ ሀሳብ በጀርመን ውዝግብ አስነሳ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 2017በዩክሬን ያለው የሩስያ ጥቃት ሊያበቃ እንደሚችል ምንም አይነት ምልክት ባይኖርም፤ ጀርመን ግን ቡንደስዌር እየተባለ የሚጠራውን የጀርመን ጦር በሠላም አስከባሪ ሀይል ውስጥ የመሳተፍ ሀሳብ ከወዲሁ እያወዛገበ ነው።የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በቅርቡ ስብሰባ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።ሁለቱ ሀገራት ጦርነቱን ለማቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በትክክል ከተስማሙ የጀርመን ሚና ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው በጀርመን ፖለቲከኞች ዘንድ እያከራከረ ነው።
ፖለቲከኞች በተለይ ጀርመን ለሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደር ልትልክ ትችል እንደሆነ ሲከራከሩ ቆይተዋል - ጦርነቱ እንደገና እንዳይቀጥል ዓለም አቀፋዊ ኃይል በሀገሪቱ ውስጥ ይሰፍራል የሚል ሀሳብ በብዙዎች ዘንድ እየተነሳ ነው።በተለይ መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርዝጀርመን በአለም አቀፍ ግጭቶችን ለመፍታት ጠንካራ ድምጽ እንዳላት ከተናገሩ ወዲህ ፤ ጀርመን በእንደዚህ አይነቱ ሃይል የማሰማራት ስራ ላይ ልትገኝ እንደምትችል ብዙዎች ይናገራሉ። ነገር ግን እንደ ሜርዝ ገለጻ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላም ቢሆን ቀዳሚው ጉዳይ ሩሲያ አዳዲስ ጥቃቶችን እንዳትፈጽም የዩክሬንን ጦር በከፍተኛ ሁኔታ የማጠናከር ቁልፍ ጉዳይ ላይ ጀርመን ትኩረት ማድረግ አለባት።ይህም የሜርዝ ሀሳብ የዩኤስ አሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በፎክስ ኒውስ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ አውሮፓ ሊመጣ ከሚችል ማንኛውም የደህንነት ዋስትና «የአንበሳውን ድርሻ» መውሰድ አለባት ከሚለው ጋር የሚስማማ ነው።ይሁን እንጂ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የአውሮፓ ጦር በዩክሬን ማሰማራቱን «ፍፁም ተቀባይነት የሌለው» ሲሉ ገልፀውታል።
የህዝብ ድጋፍ ብዙ አይለም
በጀርመንም ቢሆን ለእንደዚህ አይነቱ ጉዳይ ይሁንታ ለማግኘት ለመራሄ መንግስት ሜርዝ ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ይመስላል። በመራሄ መንግስት ሜርዝ የጥምር መንግስቱ ትንሹ አጋር የሆነው የመሀል ግራው ሶሻል ዴሞክራቶች (ኤስፒዲ) ርምጃው የችኮላ ነው ሲል እያስጠነቀቀ ነው።የ ግራው ሶሻል ዴሞክራቶች በጀርመንኛው ምህፃሩ /SPD /መሪ ላርስ ክሊንግባይቶልድ ሳት አንድ (Sat-1) ለተባለው ቴሌቪዥን እንድገለፁት አሁን ጠንከር ያሉ ንግግሮች ቢደረጉ መልካም ነው ።በእርግጥ ዩክሬን ዳግም ጥቃት እንደማይደርስባት ስለደህንነት ሁኔታዋ ማወቅ ትፈልጋለች። ሲሉ ክሊንግቤይል ተናግረዋል። አያይዘውም ይህ «በመጀመሪያ ደረጃ ጠንካራ የዩክሬን ጦር ይፈልጋል። ከዚያ ውጭ ምን ማድረግ እንደሚቻል እናያለን። ነገር ግን የጀርመን ወታደሮች መሳተፍ መቻል እና አለመቻላቸው በአሁኑ ጊዜ ጥያቄ አይደለም።» በማለት ገልፀዋል።
የጀርመን መራጮች፣ በተወሰነ መልኩ ይስማማሉ። አንድ የጀርመን የጥናት ድርጅት ፤ዌብ ዲኢ (web.de) የተባለውን የጀርመን የበይነመረብ ፖርታል ወክሎ ባደረገው ጥናት፣ 51% የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች በዩክሬን የሰላም ተልዕኮ ላይ የጀርመን ተሳትፎን ተቃውመዋል። 36% ብቻ ጉዳዩ ትክክል ነው ብለው እንዳሰቡ ተናግረዋል ።
የሜርዝ የመሀል ቀኝ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት (ሲዲዩ) አባል የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሃን ዋዴፑል በበኩላቸው ጥንቃቄን እንዲደረግ አሳስበዋል።ዋዴፑል በዩክሬን የሚካሄደው ተልእኮ ጀርመንን “ምናልባት ሊያጨናንቃት” ይችላል ሲሉ ቴብል ሚዲያ ለተባለው የመገናኛ ዘዴ ተናግረዋል። በሊትዌኒያ የቡንደስዌህር ተዋጊ ብርጌድ ማቋቋም በጀርመን ወታደሮች ላይ ከወዲሁ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው ብለዋል።ዋዴፑል ከDW ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሰላም ንግግሮች ሊደረጉ ይችላሉ በሚለው ላይ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል፡ «አሁን ሁሉም ሰው ቭላድሚር ፑቲን ይህን ጦርነት ለማቆም እውነተኛ ንግግሮችን እንደሚያደርግ እየጠበቀ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ በጦር ሜዳ ያለው ሁኔታ አሁንም ፍጹም የተለየ ይመስላል።»ብለዋል።
የመራሄ መንግስት ሜርዝ አቋም
በጎርጎሪያኑ ነሐሴ 18 በትራምፕ ፣ ዘለንስኪ እናየአውሮፓ መሪዎችመካከል በዋሽንግተን የተደረገውን ስብሰባ ተከትሎ፤ መራሄ መንግስት ሜርዝ “እኛ እንደ ጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፤ ከፍተኛ የመሳተፍ ፍላጎት እና ትልቅ ሀላፊነት አለን” በማለት በሁለቱ ሀገራት ሊኖር የሚችለውን የሰላም ሂደት በተመለከተ የጀርመንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሀሳብ ሰንዝረዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ፖለቲከኞች ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የማሰማራት ሀሳብ ላይ በየቀኑ በመነጋገር ላይ ናቸው። አብዛኛዎቹ ጉዳዩን በጥርጣሬ የሚያዩ ወይም የሚቃወሙ ናቸው።ሁሉም በሚባል ደረጃ በዚህ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውሳኔ አሁንም ጊዜው አለመሆኑን እና በጣም ሩቅ እንደሆነ ያምናሉ።
በተለይ የምስራቅ ጀርመን ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች እቅዱን በመቃወም ላይ ናቸው። በዚህ ሃሳብ የጀርመን የግራ እና የቀኝ ክንፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም አላቸው።ለምሳሌ ተቃዋሚዎቹ ሶሻሊስት ግራ ፓርቲ እና ቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን (አፍዲ) ይህንን ሃሳብ ውድቅ በማድረግ ላይ ናቸው።
የተቃዋሚዎች አቋም ምንድን ነው?
አረንጓዴው ፓርቲ በዋሽንግተን በተካሄደው የዩክሬን ስብሰባ ውጤት ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ገልጿል። የግሪን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባለሙያ ኦሚድ ኑሪፑር ማክሰኞ RTL እና nTV ከሚባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አውሮፓ የራሷን የጥበቃ ሃይሎች በማቋቋም ዩኤስን ሳያካትት እንኳን ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና እንድትሰጥ አሳስበዋል።
የግራ ፓርቲ መሪ ጃን ቫን አኬን ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና እንዲሆን ከ30,000 እስከ 40,000 የሚደርሱ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርበዋል። «የሩሲያ ወታደሮች በቻይና ወታደሮች ላይ ስለማይተኩሱ» የቻይና መሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። ሆኖም የጀርመን ወታደሮች ተሳትፎ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ጦር ሩሲያን በወረረበት ወቅት የተከሰቱትን ክስተቶች የሚያስታውስ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅዋል። የአማራጭ ለጀርመን (አኤፍዲ) መሪ አሊስ ዋይዴል ጀርመን እራሷ ኢላማ ልትሆን እንደምትችል አስጠንቅቀው “ጀርመን ከሩሲያ ጋር የማያቋርጥ ግጭት ከመፍጠር ይልቅ እርቅ ያስፈልጋታል” ሲሉ ጠይቀዋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ የሙኒክ የፀጥታ ኮንፈረንስ የረዥም ጊዜ ኃላፊ ቮልፍጋንግ ኢቺንገር በ X ገፃቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡- «ፕሬዚዳንት ፑቲን በአሁኑ ጊዜ ይህን ጦርነት ለማቆም መዘጋጀታቸውን የሚያሳይ አንድም ምልክት የለም። በጀርመን ያሉ ብዙ ታዛቢዎች በዚህ ይስማማሉ። ይህ የሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ ሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ዩክሬን የማሰማራቱ እና ያለማሰማራቱ ጉዳይ ከይስሙላ ክርክር ያለፈ አይደለም።»ብለዋል።
ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ