ኮቪድ-19ን የሚከላከው አዲሱ መተግበሪያ
ረቡዕ፣ ግንቦት 5 2012የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ ሀገራት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎችንና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን ጥቅም ላይ እያዋሉ ይገኛሉ።«ለህዝባችን ተጠቃሚነት ዓለምን እናስሳለን»በሚል መሪ ቃል የተለያዩ የሳይንስና የቴክኖሎጅ ስራዎችን ሲሰራ የቆየው የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተቋምም የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የተለያዩ ምርምሮችን ሲያደርግ ቆይቷል። ምርምርሩ ፍሬ አፍርቶም ከሰሞኑ በኮሮና ተዋህሲ የተያዙትንም ሆነ ተይዘው ይሆናል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን መረጃ የሚሰበስብ አዲስ መተግበሪያ ሰርቷል። የተቋሙ ዳይሬክተር ዶክተር ሶሎሞን በላይ እንደገለፁት ይህ መተግበሪያ በተንቀሳቃሽ ስልክና በድረ-ገፅ የሚጫን ሲሆን ፤ማንኛዉም የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ መተግበሪያውን ስልኩ ላይ በመጫን ብቻ የግለሰቡን የሰዎች ንክኪ፣ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለተዋህሲው ያለውን ተጋላጭነት መረጃ መሰብሰብ ይቻላል።ዳይሬክተሩ ከተጠቃሚው የሚጠበቀው ነገር መተግበሪያውን ስልክ ላይ መጫን ብቻ ነው።
አንድ ሰው በኮሮና ተዋህሲ ከተያዘም ሆነ ከተጠረጠረ ወይም ለይቶ ማቆያ ከነበረና ከማቆያው በሚወጣበት ጊዜ ከማን ጋር እንደተገናኘና የት እንደሄደ መረጃ የሚሰበስበው ይህ መተግበሪያ፤ ከዋና ማዕከሉ የመረጃ ቋት ጋር የየተያያዘ በመሆኑ የተሰበሰበውን መረጃ የጤና ባለሙያዎች በቀላሉ ማግኜት ይችላሉ።ይህም የወረርሽኙን ስርጭት በጊዜ ለመከላከልና የተያዙ ሰዎችም በጊዜ ህክምና እንዲያገኙ ያግዛል።በሁለተኛ ደረጃ በድረ-ገፅ የሚጫነው መተግበሪያ ደግሞ የጋራ መረጃን በማሰባሰብ የተለዬ አገልግሎት አለው። በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ የሚጫነው ይህ መተግበሪያ ምንም አይነት የኢንተርኔት ግንኙነት የማያስፈልገውና ከቦታና ከአቅጣጫ ጋር ብቻ የተገናኘ ነው ።መተግበሪያው ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል እንዲሆንም ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ሀገር በቀል ቋንቋዎችም የተዘጋጀ ነው።ስለሆነም ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት ቋንቋ መርጠው መጠቀም ይችላሉ። መተግበሪያውንም ከተቋሙ ድረ-ገፅ ማግኘት የሚቻል ሲሆን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ አጠቃቀሙን በተመለከተ ባለሙያዎች በተቋሙ ድረ-ገጽ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ይህ መተግበሪያ በግለሰቦች የግል መረጃና ማንነትን ላይ ያላነጣጠረ እንዲሁም በግለሰቦች በጎ ፈቃደኝነትና የመረጃ ልገሳ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ለተወሰነና ለታወቀ ዓላማ ማለትም በሽታውን በመከላከል የግለሰብንና የማህበረሰብን ጤና ለመጠበቅ ብቻ የሚዉል ነው።ይህንን በመገንዘብ በተቻለ መጠን ህብረተሰቡ መተግበሪያውን በተንቀሳቃሽ ስልክም ይሁን በድረ-ገፅ በመጫን የበሽታዉን ስርጭት ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት አጋዥ እንዲሆን ዶክተር ሶሎሞን አስገንዝበዋል።
ይህ መሰሉ መተግበሪያ ከዚህ ቀደም በተላያዩ ሀገራት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ፤በቻይና ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ይከሰታል በሚል ስጋት ሰዎች ስልኮቻቸው ላይ ስካን የሚያደርጉት ኮድ በመጫን ስለጤንነታቸውና ስለጉዞዎቻቸው መረጃ ይሰጣሉ።በአውስትራሊያም ብሉቱዝና «ኮቪድ ሴፍ» የተባለ መተግበሪያ በመጠቀም የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ነው።በህንድም በ11 ቋንቋዎች የሚሰራ የአንሮይድ መተግበሪያ በመጠቀም 75 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።በአጠቃላይ በጀርመን ፣በጣሊያን፣ በደቡብ ኮርያና በተላያዩ ሀገሮች የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎችንና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም የኮሮና ወረርሽኝን ለከላከል ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።ወረርሽኙን በፈጠራ ስራ ለመከላከል የሚደረገው ይህ መሰሉ ጥረት እንደ ዶክተር ሶሎሞን በላይ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ ትምህርት የሰጠና ወደ ፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።
በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን ለመግታት በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች እየሰሩ መሆናቸውን ተመራማሪው ጠቅሰው ምንም እንኳ የገንዘብ አቅም ችግር ቢኖርም ተስፋ ሳይቆርጡ ተበረታተው እንዲቀጥሉም መክረዋል። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተቋም ከዚህ መተግበሪያ በተጨማሪ ፅኑ ህሙማንን የሚረዳ የመተንፈሻ መሳሪያ አሻሽሎ መስራቱንም ተመራማሪው ዶክተር ሶሎሞን በላይ ጨምረው ገልፀዋል። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ