ከጦርነት የተረፉ ስምንት የትግራይ ተወላጆች ያቀረቡት ክስ
ረቡዕ፣ መጋቢት 17 2017
ክሱን ያቀረቡት ጦርነቱ ሲካሄድ ትግራይ ክልል ውስጥ ገሚሶቹ የረድኤት ድርጅት ሠራተኞች ገሚሶቹ ደግሞ በወቅቱ የነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት እንደነበሩ ተገልጿል። ከጦርነቱ የተረፉት እነዚህ ወገኖች እንደሌሎች በመቶና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጾታዊ ጥቃት ለዘፈቀደ እስር እና ስቃይ፤ እንዲሁም ረሀብ ሰለባና እማኞች መሆናቸውን አቤቱታቸውን ለጀርመን የፌደራል አቃቤ ሕግ ያቀረቡት፤ ተቋማት ናቸው።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ከተለወጠው አቤቱታ አቅራቢያዎች አንዱ የሆኑት አቶ ፀጋ፤ እንደሚሉት በሁለት ዓመቱ ጦርነት ታናሽ ወንድማቸውን እና እናታቸውን አጥተዋል። ሀዘኑ አሁንም አልወጣላቸው። ያ አልበቃ ብሎ ዛሬም የትግራይ ወገኖቻቸው በየቀኑ ለሞት እየተዳረጉ መሆኑንም ነው ይናገራሉ። ይኽ እልባት እንዲያገኝም ለማሰብ የሚከብደው ያሉትን ትግራይ ውስጥ የተፈጸመ ወንጀል ያቀነባበሩ አካላት ባስቸኳይ ለፍርድ መቅረብ እንደሚኖርባቸውም ተማጽነዋል።
ጉዳዩን የያዙት በተለያዩ ሃገራት የጦርና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመመርመር ፍትህ እንዲገኝ የሚሠሩት የሕግ ተቋማት ባለፈው መስከረም ላይ ነው የእነዚህን ወገኖች አቤቱታ ለጀርመን የፌደራል አቃቤ ሕግ ያቀረቡት። ባለፈው ሳምንት ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ ክሶችን አጠናቅረው ማቅረባቸውን ያነጋገርናቸው ኒውዮርክ የሚገኙት ጉዳዩን ከያዙት ዓለም አቀፍ የወንጀል ጉዳዮች የሕግ ባለሙያ ኒክ ለዲ ገልጸውልናል። የቀረበው ክስ ይዘቱ እንዴት ያለ ይሆን? የሕግ ባለሙያው ኒክ ለዲ ያብራራሉ።
« ይህ ጉዳይ ስምንት ከጎርጎሪዮሳዊው ኅዳር 2020 እስከ ኅዳር 2022 ትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ከጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸመ ወንጀል የተረፉ የትግራይ ተወላጆችን ወክሎ የቀረበ ክስ ነው። አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከመካከላቸው አምስቱ ጀርመን ውስጥ ነዋሪ ናቸው፤ እነሱም ግድያና እስራትን ጨምሮ፤ ጾታዊ ጥቃት፤ እርሃብ እና ስቃይ ለመፈጸሙ እማኝ ነን ብለዋል። አቤቱታ አቅራቢ ደንበኞቻችን ፍትህ ይፈልጋሉ። ፍትህ የሚፈልጉትም እኛ እንደምናምነው በኢትዮጵያም በኤርትራም ባለሥልጣናት በኩል ለተፈጸሙ ወንጀሎች ነው።»
እንዲያም ሆኖ ጋዜጣዊ መግለጫውም ሆነ ጉዳዩን ከያዙት የሕግ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ኒክ ላዲ ክስ የቀረበባቸው የ12ቱን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ስም ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ከጦርነቱ የተረፉትን ወገኖች አቤቱታ ለጀርመን የሕግ አካላት ያቀረቡበትን ምክንያት አስመልክተው ግን ከፍትህ ጠያቂዎቹ አምስቱ ጀርመን ሀገር ስለሚኖሩ ነው ያሉት። ለሁለተኛ ጊዜ አቤቱታውን አጠናክረው ያቀረቡትም የጀርመን አቃቤ ሕግ ጉዳዩን እንዲመረምር በሚል ነው።
«አቤቱታውን ለጀርመን ባለሥልጣናት ያቀረብነው ምርመራ እንዲከፍቱ ነው። አሁን ምርመራውን ለመጀመር ሙሉ ውሳኔው የጀርመን አቃቤ ሕግ ነው የሚሆነው። በቂ ማስረጃዎችን ሰጥተናቸዋል፤ ከመቶ ገጽ በላይ አቤቱታንም ከበርካታ አባሪዎች ጋር አቅርበንላቸዋል። የተሟላና ግልጽ ምንጭ ያለው ማስረጃዎችና የእማኞችንም ቃል ይዟል፤ እናም ጀርመኖች ይህን አቤቱታ ተቀብለው እኛ መዋቅራዊ ምርመራ የምንለውን ይጀምራሉ ብለን እናስባለን። እነዚህ መዋቅራዊ ምርመራዎች ደግሞ በዚህ ክስ ተሳትፈዋል የተባሉ መዋቅሮች እና ቡድኖች ላይ የሚደረጉ ይሆናል። በሌሎች ዓለም አቀፍ ሥልጣን የሚጠይቁ ጉዳዮች ለምሳሌ በሶርያ እና ዩክሬን ላይ እንዳካሄዱት ማለት ነው።»
የጀርመን ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም ሶርያ ውስጥ፤ እንዲሁም ጋምቢያ እና ኢራቅ ውስጥ ለተፈጸሙ የጭካኔ ወንጀሎች ዓለም አቀፍ የሕግ ሂደት መርሆዎችን በተሳካ ሁኔታ ተጠቅመው ክስ መመሥረታቸውን የሕግ ተቋማቱ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫም አንስተዋል። አቤታ ያቀረቡት ስምንቱ የትግራይ ተወላጆችም ጉዳያቸው ተመሳሳይ ግምት ተሰጥቶት በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው ነው አሁን የጠየቁት። ኒክ ለዲ የጀርመን አቃቤ ሕግ የቀረበለትን ዝርዝር መረጃ አጢኖ አቤቱታውን ተቀብሎ ምርመራ ያካሂዳል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል፤
«የእኔ ተስፋ የጀርመን ባለሥልጣናት ይህን አቤቱታ ተቀብለው በጭካኔ ወንጀሎቹ ላይ መዋቅራዊ ምርመራ ያደርጋሉ የሚል ነው። አቤቱታዎቹ ትግራይ ውስጥ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከባድ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ይጠቁማሉ። ስለዚህ ለደንበኞቻችን ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን የሚያቀርቡት ሌላ መድረክ የላቸውም። ካሉት ጥቂት የፍትህ መድረኮች አንዱ የጀርመን አቃቤ ሕግ ቢሮ ነው። ይህን ምርመራ በመክፈት የጀርመን ባለሥልጣናት በወንጀሎቹ ማን ዋነኛው ተጠያቂ ነው የሚለውን በመወሰን የእስር ማዘዣ ያወጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ