ኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች አዲስ አበባ ውስጥ መወያየታቸው ተገለፀ
ማክሰኞ፣ ጥር 20 2017የኤርትራ መንግሥትን ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ያዘጋጁት የተባለ ውይይት ትናንት ሰኞ ጥር 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መደረጉን ከተሳታፊ ድርጅቶች አንዱ ለዶቼ ቬለ ዐሳወቀ ። እስከ «ሁለት ሺህ እና ከዚያም በላይ» የሚሆኑ ኤርትራዊያን በዚህ «ውይይት» መሳተፋቸው ተገልጧል ። የተደረገውን ውይይት በተመለከ፦ «የኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ሳይኖረው አልሆነም» ሲሉ የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ (EANC) ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ የሱፍ አብደላ ተናግረዋል ። ይህንን ውይይት አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ እድሉን እንዴት እንዳግፕኙ የተጠየቁት አቶ የሱፍ አብደላ ይህንን ለማድረግ "እድል ተገኝቷል፣ ያንን እድል ተጠቅመን ውይይቱን አድርገናል" የሚል ምላሽ ከመስጠት በዘለለ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል ።
የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ አስተያየት
የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ (EANC) የተባለውና የኤርትራን መንግሥት ለመለወጥ የሚንቀሳቀስ መሆኑን የሚገልፀው ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ የሱፍ አብደላ የፖለቲካ ትግላቸው ማጠንጠኛ የኤርትራ መንግሥት ኤርትራ ውስጥ በሚገኙ አፋሮች ላይ የሚፈጽመው ያሉትን "በደል" እና "ግፍ" ማስቀረት ነው። ለዚህም ሲባል የኤርትራ መንግሥትን ከሌሎች የኤርትራ "ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ለመቀየር" ከኤርትራ ውጪ እንደሚንቀሳቀስ እና በትግል ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልፀዋል።
"ኤርትራ ውስጥ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ የራስን መብት ራስህ የምትወስንበት ኹኔታ ለማመቻቸት የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት ነው።" ይህንን ለማድረግ የትጥቅ ወይስ ሰላማዊ ትግል ነው የምታደርጉት? የትግል ሜዳችሁስ የት ነው ? የሚለውን ጠይቀናቸዋል።
አማርኛ የሚናገሩት አቶ የሱፍ ድርጅታቸው "ከተለያየ" የዓለም ክፍል ላይ ያለ እና የተደራጀ መሆኑን ገልፀዋል። ይህንን እንቅስቃሴውንም ኤርትራ ውስጥ "ለነፃነት ከሚታገሉ" ካሏቸው ሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚከውን መሆኑን በስልክ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። አዲስ አበባ ውስጥ ምን መሳይ ውይይት ነው ያደረጋችሁት? ለሚለውም ምላሽ ሰጥተዋል።
"ለውጥ ማምጣት እንዳለብን [ኤርትራ ውስጥ] ሕዝባችን ተሰቃየ፣ ሀገራችን ወድሟል። ግን ይህንን መንግሥት [የኤርትራን] በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት እና ለሁሉም የኤርትራ ብሔር ብሔረሰቦች የሚስማማ ያልተማከለ መንግሥት ለመመሥረት የሚል ሴሚናር ነበር።"
ለኤርትራ ሕዝብ የሚታገል እንቅስቃሴ ያሉት "ሰማያዊ ማዕበል" የሚባለው ንቅናቄ ያዘጋጀው በተባለው በዚህ "ሴሚናር" ወይም ውይይት ላይ ከተለያየ የዓለም ክፍል የተውጣጡ ኤርትራዊያን የተሳተፉበት መሆኑን እኒሁ ሰው ገልፀዋል። ውይይቱ አዲስ አበባ ውስጥ ሲደረግ ምን ያህል ሰው ተሳትፏል? የሚለውም ሌላኛው ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነው።
"ተሳታፊው ብዙ ነበር። እስከ ሁለት ሺህ እና ከዚያ በላይ የሚሆን ወጣቶች እና እንግዶች ተሳትፈዋ።"
እንዴት ይህንን ፈቃድ ወይም እድል አገኛችሁ?
"መቼም የኤርትራ መንግሥት ጓደኛ የለውም" ሲሉ የከሰሱት የኤርትራን መንግሥት የሚቃወመው የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ ሥራ አሥፈፃሚ አባል አቶ የሱፍ አብደላ፤ የኢሳያስ አፈወርቂን አስተዳደር "ዓለም ላይ ለጎረቤት ሀገሮች ችግር ነው፣ ለራሱ ሕዝብ ችግር የሆነ በአንድ ቡድን የሚመራ መንግሥት ስለሆነ ዛሬ ይህ እድል ተገኝቷል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ውይይት ላይ የነበረው እውቅና ምን ድን ነው ? የሚለውንም ለአቶ የሱፍ አቅርበንላቸዋል። "ይህን ያህል ሴሚናር እዚህ ዋና ከተማ ውስጥ ሲደረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ሳይኖረው አይሆንም" ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በእጅጉ ተለውጦ ሁለንተናዊ ግንኙነት ተጀምሮ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታው የተለወጠ ይመስላል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስመራ በረራም ተቋርጧል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት ለቀረበለት ተደጋጋሚ ጥያቄ አሁንም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት መኖረን ደጋግሞ አስታውቋል።
አዲስ አበባ ውስጥ ተደረገ ስለተባለው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ውይይት የኢትዮጵያን መንግሥት ሀሳብ ለማካተት ወደ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ ብንደውልም ልናገኘቸው አልቻልንም።
የኤርትራ መንግሥትም እስካሁን በይፋ የወጣ ያለው ነገር ስለመኖሩ የወጣ መረጃ የለም።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ