ኤርትራዊያን ስደተኞች ከእስር ተፈቱ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 2017
ላለፉት 6 ወራት ተኩል በዳባት፣ በደባረቅና ጎንደር ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የነበሩ 5 ኤርትራዊያን ስደተኞች ከእስር መፈታታቸውን ተናገሩ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) 5 ኤርትራውያን ስደተኞች ከእስር መፈታታቸውን አረጋግጧል፡፡
ስደተኞቹ ከ6 ወራት በላይ በእስር ቆይተዋል
የተጠረጠሩበት ወንጀል ሳይነገራቸውና ክስም ሳይመሰረትባቸው፣ ከሚኖሩበት ዳባት “ዓለምዋጪ” የስደተኞች መጠለያ ጣቢያና ከዳባት ከተማ፣ መሰረት ገ/ስላሴ፣ እስማኤል አህመዲን፣ ፍሰሐዬ ኪዳነ፣ መሐሪ አብርሀና ተስፋዓለም ክፍለይ የተባሉ ኤርትራዊያን ስደተኞች ከጥቅምት 8 እስከ ህዳር 26/2017 ዓም ባሉት ቀናት ተይዘው፣ ከታህሳስ 16/2017 በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ፖሊስ ጣቢያ፣ ከታህሳስ 16 እስከ መጋቢት 14/2017 በዚሁ ዞን ደባርቅ ፖሊስ ጣቢያ፣ ከመጋቢት 14 እስከ ግንቦት 5/2017 ደግሞ በጎንደር ከተማ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደነበሩ የታሳሪዎች ጠበቃ አቶ ታሪኩ ወልደማሪያም ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ከሳሽ ያጡት ታሳሪዎች ከሳሽ ሆነው ቀርበዋል
ከስደተኞች መካከል እስማኤል አህመዲን እንደገለጡልን ከሳሽና ጠያቄ ባለማግኝታቸው በጠበቃቸው አማካኝንት ራሳቸው ታሳሪዎች ጉዳያቸው እንዲታይላቸው ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ምድብ ችሎት ክስ ማቅረባቸውንና በችሎት ስለተጠረጠሩበት ሁኔታ የሚያስርዳ አካል ባለመቅረቡ ከፖሊስ ጣቢያ ባለፈው ሳምንት ወጥተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል፡፡
መሠረት ገ/ስላሴ የተባለው ሌላው ሰደተኛ “ፍርድ ቤቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ላመጣን አካል እንድንመለስ ለጎንደር ከተማ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ ግለሰቡ ተረክቦ ባለንበት ጥሎን ሄዷል” ብሏል፡፡
የታሳሪዎች ጠበቃ አቶ ታሪኩ ወልደማሪያም ስደተኞቹን ለጎንደር ከተማ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያስረከባቸው አካል
እንዲረከባቸው ትዕዛዝ በማስተላለፉ፣ በፖሊስ ጣቢያው እንዲቆዩ ያደረገው አካል (ግለሰብ) ፈርሞ ተረክቦ ጥሏቸው በመጥፋቱ ታሳሪዎቹ ወደ መጡበት መመለሳቸውን ከታሳሪዎቹ መረጃ እንደደረሳቸው አመልክተዋል፡፡
“ታሳሪዎቹ በህገወጥ ድርጊት ተጠርጥረው ነበር” UNHCR
ታሳሪዎቹ ስለተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ባይገልፁም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) ቀደም ሲል ለዶይቼ ቬሌ ሰጥቶት በነበረው መረጃ 5ቱ ኤርትራውያን ዳባት በሚገኘው ዓለምዋጪ የስደተኞች ጣቢያና በአካባቢው ህገወጥ ተግባራትን ሲፈፅሙ ነበር በሚል ተጠርጥረው በፀጥታ ኃይሎች መያዛቸውን በወቅቱ አመልክቷል፡፡
ድርጅቱ (UNHCR) ትናንት በጽሁፍ በሰጠን ተጨማሪ መረጃ “5ቱ ኤርትራውያን ስደተኞች ከእስር መፈታታቸውን አረጋግጫለሁ” ብሏል፡፡
ተጨማሪ አስተያየት ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ ለማግኝት ስልክ በመደወልና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ