ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር «የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባችም» - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ሐሙስ፣ ግንቦት 28 2017ከኤርትራ በኩል «የማይመቹ እና የሚጎረብጡ» ያሏቸው ነገሮች ቢሩም ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት «የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላለመጉዳት» ስትል ጉዳዩን በትዕግስት እያለፈችው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ተናገሩ ። ሚኒስትሩ ዛሬ ሐሙስ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ «ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባችም» ብለዋል ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቴዎስ «ኢትዮጵያ ከጌረቤቶቿ ተነጥላለች» በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፦ ያንን መቀበል እንደሚቸግር፣ ይልቁንም «ቋሚ አድርጋ የምትይዘው ሀገራዊና ብሔራዊ ጥቅሟን ነው» በማለት፣ አንድን ሀገር ላለማስቀየም በሚል ይህንን ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥ ገልፀዋል ።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ተጠይቋል
ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ "ወሳኝ ድክመቶች የታዩበት ነው" የሚለው ቀዳሚው ነበር።
የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት "ወጥነት ማጣት፣ በውስጣዊ አንድነት ችግር ሀገራዊ ተጋላጭነቶች" መኖር የሚሉትም ይገኙበታል። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ የዲፕሎማሲ መገለል እየደረሰባት ነውና ማብራሪያ ይሰጥበት ተብሎ ተጠይቋል። "የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ አሁን ወደ ጦርነት ጅማሮ እየወሰደ ያለ የቃል ጦርነቱ የተጀመረበት ሁኔታ ያለ ይመስላል። እና ሀገራችን ከኤርትራ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት ይገለፃል?" በሚል ተጠይቋል።
ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ዜጎች፣ የሕዝብ ተወካዮች፣ የቀድሞ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የራሳቸውን ምልከታ ያጋራሉ። ልምዳቸውንና ለሀገር ያላቸውን ቀናዒነት ታሳቢ በማድረግ" የሚያስተላልፉት መልዕክት መኖሩንም በማንሳት እንዲያ ያለው መልእክት ጆሮ ሊሰጠው እንደሚገባ፤ ሆኖም እንደ መንግሥት ይፋዊ የሆነው ምላሽ ባለፈው ሳምንት በመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ በኩል የተሰጠው ኢትዮጵያ "ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ተባብሮ መሥራት ላይ ያተኮረ መርህ" እንደምትከተል የተገለፀበት መሆኑን ገልፀዋል።
ምላሹ ሰሞኑን "የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲያስወጣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ሊደረግበት ይገባል" ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተናገሩትን መነሻ ያደረገ ነው። "ከኤርትራ መንግሥት ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባም።"
"የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ከፍ ያለና ጥልቅ ነው"
"የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙኙነት በስፋቱም፣ በደርዙም በጣም ከፍ ያለ፣ ጥልቀትም ያለው ነው" ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህም በ2010 ዓ .ም መታየቱን ገልፀዋል። ያንን ሕጋዊ እና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማስቀጠል የመንግሥት ፍላጎት መሆኑንም ተናግረዋል።
"ኤርትራዊያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ወደ ኢትዮጵያ መጠለያ ፈልገው በተለያየ ምክንያት በሚመጡበት ጊዜ እንደቤታቸው ተሰምቷቸው ለማስተናገድ በሕዝብም በመንግሥትም በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው። በዚህ በኩል ያለውን በጎ ተቀባይነት መንግሥት በሕግ፣ በፖሊስ፣ በአሠራር፣ በተቋም ደግፎ አስቀጥሎታል።"
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከቀጣናዊ ኃይሎች ጋር ያላት ግንኙነት ከጎረቤት ሀገራት ካላት ጋር የተዛመደ መሆኑን በጠቀሱበት ማብራርያቸው "ቋሚ አድርጋ የምትይዘው ሀገራዊና ብሔራዊ ጥቅሟን ነው" ብለዋል።
ከኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ብቻ ሳይሆን የካሳ ኮሚሽን ተሰብሳቢ ገንዘብንም እናስመልሳለን
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤርትራ ያለውን ገንዘብ ለማስመለስ ውጭ ጉዳይ ስለሚያደርገው ጥረት የተጠየቁት ሚኒስትሩ መንግሥት ሌሎች ሀብቶችንም እንደሚያስመልስ ገልፀዋል።
"ንብረታችንን፣ ገንዘባችንን ለማስመለስ የምናደርገውን ጥረት እንቀጥልበታለን። ያለን ሀቅ እና ንብረት ይሄ ብቻ አይደለም። ሌሎችም የሚጠቀሱ ተሰብሳቢ ሂሳቦች አለን። እንደሚታወቀ የካሳ ኮሚሽን ነበር፣ የካሳ ኮሚሽኑ የወሰነልን ገንዘብም አለ። ከዚያም ተሰብሳቢ አለን።" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤትቿ ድንበር ጋር ተያይዞ የሚገጥማት ችግር ሀገሪቱ ከሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በሺዎች በሚቆጠር ኪሎ ሜትር የምትዋሰን ሆኖ ሳለ በአግባቡ የተከለለ እና የተሰመረው ወይም በችካል የተለየው ከሃምሳ በመቶ በታች የሆነው ብቻ በመሆኑ ሚኒስትሩ ይህ "ውዝፍ" ያሉት ሥራ በተደራጀ ሁኔታ በጥናት ሲፈታ ችግሩ ምላሽ ያገኛል ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ