"ኢትዮጵያ አትበታተንም፤ ኤርትራ በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም" ጠ/ሚ ዐቢይ
ሐሙስ፣ ሰኔ 26 2017"ኢትዮጵያ አትበታተንም፤ ኤርትራ በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
"ኢትዮጵያ አትበታተንም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ። "ኢትዮጵያን ለመበተን የሚያስችል ኃይል የለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ "ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት" በማለት ከጎረቤት ሀገራት ሊቃጣ የሚችል ጥቃት ቢኖር እንደምትመክት ገልፀዋል። በኤርትራ በኩል ዉጊያ እንደሚነሳ እንደሚወራ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በእኛ በኩል አንድም ጥይት አይተኮስም" ሲሉም አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ ዳግም ጦርነት እንዲጀመር ፍላጎት እንደሌለው ግን አዝማሚያ መኖሩን በመጥቀስ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች እና ኤምባሲዎች በፍጥነት ይህንን እንቅስቃሴ እንዲያስቆሙ እና ንግግር እንዲጀመር ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
"ኢትዮጵያ አትበታተንም። ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት። ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች። ለመበልጸግ የሚያበቃ በቂ አቅም አላት"
ይህ ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመቱ የመጨረሻ መደበኛ ጉባኤ ላይ የሰጡትን ማብራሪያ የደመደሙበት ንግግር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምና ፀጥታን በተመለከተው ማብራሪያቸው በትግራይ ክልል ጦርነት እንዳይጀመር ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለባለሃብቶችና ለሌሎችም ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። በክልሉ ያሉ ኃይላት "በፍጥነት ወደ ውይይት መግባት እንዳለባቸው" ይሰማኛልም ብለዋል። በክልሉ ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ "መንግሥት ተወጥሯል" ፣ የሚያግዙን ሀገራት አሉ" በሚሉ ምክንያቶች ጦርነት የመቀስቀስ አዝማሚያ መኖሩን በመግለጽ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ገልፀዋል። የህወሓት ክፍፍል ያመጣዉ የታጣቂዎች መከፈል ወደ ግጭት እንዳያመራ አስግቷል መባሉ
"በእኛ በኩል በትግራይ ምድር አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም"።
የሀገሪቱ የፀጥታ ችግር ምክንያቶችን የዘረዘሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሳሳተ የፖለቲካ አረዳድና የኃይል አማራጭ፣ ስንፍና፣ ድህነት፣ "ጥግ የሌለው'" ኋላቀርነት፣ ሥር የሰደደ ያሉት ዘረኝነት እንዲሁም የውጭ ጣልቃገብነት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የታሠሩ ፖለቲከኞችን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠየቀው ምህረት ከሆነ "ችግር እንደሌለው" በመግለጽ "ጥፋት የላቸውም" ከሚል መነሻ ከሆነ ግን ፍርድ ቤት ይዳኘው ብለዋል። "በዝቋላ ገዳም አንድ አባት ተገድለዋል" ሲሉ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ማን እንደገደላቸው እየተጣራ ነው" ብለዋል። ሆኖም የሃይማኖት ተቋማት የታጣቂዎች መሸሸጊያ ከሆኑ እንደዚህ አይነት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ካሉ በኋላ መልሰው "ፈተና አትፈተን ብለው፣ ማዳበሪያ አትውሰዱ ብለው የሚገድሉ መኖራቸውን በመጥቀስ ይጣራል ያሉት ወንጀል ገዳዩ ማን እንደሆን ለመግለጽ ሞክረዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እንደሚወያዩ ገለፁ
"ኢትዮጵያ የሚገባት ሰላም አላት? የላትም። አንጻራዊ ሰላም አለ"።
የቀይ ባሕር ጉዳይ በንግግር የሚታይ ሆኖ ውጤቱም በረጅም ጊዜ የሚጠበቅ መሆኑንም በማብራሪያቸው አመልክተዋል። ይሁንና "በግጭት፣ በኃይል አናደርግም" ብለዋል። ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነት እንደምታከብረው ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋን ማክበር እንዳለባቸው ግን በዚሁ ጊዜ አስገንዝበዋል።
"ኤርትራ ሉዓላዊ ሀገር ናት። በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም"።
በኤርትራ በኩል ዉጊያ እንደሚነሳ ሥጋት እንዳለ እንደሚወራ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በእኛ በኩል አንድም ጥይት አይተኮስም" ብለዋል። ከሁሉም ጎረቤት ሀገር ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዳለ፣ ትብብር፣ ውይይት ብቻ እንደሚፈለግ እና ያንን ማስቀጠል የትኩረት አቅጣጫ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። "በእኛ በኩል አንድ ጥይት አይተኮስም። በሰላም የማያኖር ጉዳይ ካለስ? ራሳችን እንከላከላለን"። የኢትዮጵያና የኤርትራ አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ሕዝብ ግንኙነት
ኢኮኖሚን በሚመለከት የሰጡት ማብራሪያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ዓመት "ታላላቅ ድሎች እና አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት" ነው ብለዋል። መንግሥታቸው የ8.4 በመቶ ዕድገት እንዲመዘገብ ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ከተረጂነት እንዲላቀቁ መደረጉን፣ አሁን ያለው የምግብ ተረጂ ሕዝብ ቁጥር 4 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል። ምንም እንኳን ሰሞኑን የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ39 ሀገራት ከፍተኛ ድህነት እና አስከፊ ረሃብ በፍጥነት እያደገ መሆኑን የጠቀሰ ቢሄንም።
"በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው ያልታወቁ ድሎች የተመዘገቡበት" ዓመት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በቀጣዩ ዓመት መባቻ ሶማሌ ክልል ውስጥ ተገንብቷል ያሉት የጋዝ ፋብሪካ ተመርቆ ምርት ለገበያ እንደሚያቀርብ አብስረዋል። "ድንቅ ሪፎርም ነው ያለው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታይቷል ያሉትን ዕድገት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፎች ዘርዝረው ጠቅሰዋል። በአመቱ አጠቃላይ 32 ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ምንጬች መገኘቱን፣ ከመንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለዓመታት የነበረ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሽግሽግ መደረጉን፣ እንዲያም ሆኖ 46 ሺህ የግብር ተመዝጋቢዎች ግብር እንደማይከፍሉ፣ በዚህም ምክንያት በዓመቱ የተሰበሰበው ግብር 900 ቢሊዮን ብር ሆኖ ሳለ የመንግሥት ጠቅላላ አጪ 1.2 ትሪሊየን ብር መሆኑን እና አለመጣጣሙን ገልፀዋል። አክለውም "የተቀናጀ ሌብነት፣ መንግሥታዊ ሙስና የለም" ሲሉ ተደምጠዋል። "የሕዳሴ ግድብ አልቋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ክረምቱ ሲያልቅ እንደመረቅም ተናግረዋል። "ግድቡ እንዳይመረቅ የሚያደርግ ነገር የለም" በማለት የታችኛው ተፋስስ ሀገራት በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዱገኙም በአደባባይ ግብዣ አቅርበዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ