ኢትዮጵያ በናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጨማሪ ሜዳሊያዎች አሸነፈች
ሰኞ፣ መጋቢት 15 2017በቻይና ናንጂንግ ከተማ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በሶስተኛ ቀን ዉሎ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወርቅ እና ብር ሜዳሊያዎች አሸነፈች። በ 1500 ሜትር ዛሬ በተደረገ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች።
አትሌት ድርቤ ወልተጂ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት ለሀገሯ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች። አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ውድድሩን ለማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረ ሲሆን የገባችበት ሰዓትም 3:54: 86 ማይክሮ ሰከንድ ሆኗል። ይህም የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል። በውድድሩ ብሪታንያዊቷ አትሌት ጆርጂያ ሁንተር ቤል ሶስተኛ ሆና ለሀገሯ የነሃስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
ቀጥሎ በተደረገው የ800 ሜትር የሴቶች ውድድር አትሌት ንግሥት ጌታቸው ሁለተኛ በመሆን ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች። በውድድሩ ከፍተኛ ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረው የአምና ሻምፒዮና ጽጌ ዱጉማ ስድስተኛ በመሆን አጠናቃለች። ውድድሩን ደቡብ አፍሪቃዊቷ ፕሩደንስ ሴክጎዲሶ አሸንፋለች ።
የመጋቢት 8 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ኢትዮጵያ ትናንት በተደረጉ የ3000 ሜትር የሴቶች እና የወንዶች ውድድር በአትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ የወርቅ እንዲሁም በአትሌት በሪሁን አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
ውድድሩ ዛሬ ፍጻሜውን ሲያገኝ ኢትዮጵያ በሰበሰበቻቸው ሁለት የወርቅ እና ሶስት የብር ሜዳሊያዎች ከዓለም ሶስተኛ ደረጃ በመሆን አጠናቃለች።
ውድድሩን አሜሪካ በ6 ወርቅ 4 ብር እና 6 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ቀዳሚ ስትሆን ኖርዌይ በ 3 ወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ናት ።
ታምራት ዲንሳ
ልደት አበበ