ኢትዮጵያዉያን ባለሐብቶች ጅቡቲ ዉስጥ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሳተፉ የጅቡቲ ባለሥልጣን ጠየቁ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 30 2017የኢትዮጵያ ወሳኝ የወደብ አገልግሎት ሰጪ የሆነችው ጅቡቲ ለሁለተኛ ጊዜ እያደረገችው ባለው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ቢሰማሩ ደስተኛ መሆኗን አስታውቃለች።የጅቡቲ ሉዓላዊ ሐብት የበላይ ኃላፊ "የጅቡቲ ስኬት የኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያም ስኬት የጅቡቲ ስኬት ነው" በማለት የሁለቱ ሀገራት ትብብር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጅቡቲ በኢትዮጵያ የፀጥታ፣ የደኅንነት፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላት በጎ ሚና እያደገ ስለመሄዱ ይታመናል።ሀገሪቱ የምትገኝበት ወሳኝ አቀማመጥ ሀያላኑ ሀገራት የጦር መንደር ገንብተው ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁባት፣ ኢትዮጵያን የመሰሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ደግሞ የወጪ እና ገቢ ንግድና እንቅስቃሴያቸው በዚህችው ሀገር ላይ እንዲመሰረት አድርጓል።
የጅቡቲ ሉዓላዊ የሀብት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ስሊም ፌሪያኒ ጅቡቲ በወደብ አገልግሎት ረገድ ለኢትዮጵያ የያዘችው የቀጣይ እቅድ ካለ ጠይቀናቸው፣ ኢትዮጵያዊያን ከወደብ አገልግሎቱ ባለፈ በኢንቨስትመንትም ቢሰማሩ እንፈልጋለን ብለዋል።"ኢትዮጵያ አንደኛ አጋራችን ናት። ኢትዮጵያ ወንድምም፣ ጎረቤትም ሀገር ነች [ለጅቡቲ]። ከዚህ ባለፈ ግን በታሪካዊ ግንኙነትም ቀዳሚ ሀጋር ናት። ስለዚህ የጅቡቲ ስኬት የኢትዮጵያ ስኬት ነው። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ስኬት የጅቡቲ ስኬት ነው። ስለዚህ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት አለብን፣ እና በከፍተኛ ደረጃ ከዚህ የተሻለ ግንኙነት ሊኖር አይችልም።
የኢትዮጵያ ባለሀብቶችም እዚህ ቢመጡ ደስ ይለኛል።"
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ወደ ሶማሊላንድ በማማተር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል። በዚህ ወቅት ጅቡቲዎች "ተደናግጠው ነበር" ያሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ የጅቡቲ ደሴቶች የለሙ ባለመሆናቸው በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ እና በዚህ ምክንያት ብዙ አልሚዎች ወደዚያ ሆዶ የመሥራት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብ ጥገኛ የመሆኗን ያህል ጅቡቲም ከኢትዮጵያ በእጅጉ የምትጠቀም መሆኗንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ የባሕር በሮችን ለማግኘትየምታደርገው ጥረት ምን ያህል ተገቢ እንደሆነ ሲያስረዱም ተከታዩን ብለዋል።"ለኢትዮጵያ ጅቡቲ ብቻ መሆኗ [የወደብ አገልግሎት በር ሰጪ] ጅቡቲ ያለው መንግሥት ቀውስ ውስጥ ከገባ ወደቡ ሊስተጓጎል ይችላል። ሁለተኛ የየመኖቹ ሁቲዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጅቡቲን ካጠቁ ለእኛ [ለኢትዮጵያ] አደገኛ ይሆናል"። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ይህንንም በማሳያ ጭምር አስረድተዋል።
"የጅቡቲ ብቻ በቂ አይደለም። በተለይ የአፈር ማዳበሪያ፣ የእርዳታ እህል ወይም ደግሞ ወደ ውስጥ የምናስገባው ነገር በሚመጣበት ጊዜ ሁል ጊዜ መጨናነቅ ነው"።ትናንትና ዛሬ ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤዋን ያደረገችው ጅቡቲ የምጣኔ ሐብት አማራጯን ከወደብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ግልጽ ፍላጎት እንዳላት አሳይታለች።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ