"አዲስ አበባ የከፈትነው ቢሮ የአብዮታችን ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ነው" - ብርጌድ ንሓመዶ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 22 2017"አዲስ አበባ የከፈትነው ቢሮ የአብዮታችን ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ነው" - የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚው ብርጌድ ንሓመዶየእንቅስቃሴየ የመጨረሻ ግብ "የኢሳይያስ አፈወርቂን ሥርዓት ማስወገድ ነው" የሚለው የኤርትራ መንግሥት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ብርጌድ ንሓመዶ ለዚህ አላማው "ወደ ኤርትራ መቅረብ የግድ ስለሚል" ቢሮውን አዲስ አበባ ውስጥ መክፈቱን አስታውቋል። አዲስ አበባ ውስጥ ይህንን እድል እንዴት ሊያገኙ እንደቻሉ የተጠየቁት የእንቅስቃሴው አስተባባሪ አቶ ኪሮስ አስፍሓ "ይህ ሥርዓት በአካባቢያችን ያሉ መንግሥታት እንዲወገድ እንደሚፈልጉ እርግጠኞች ነን" ብለዋል።
ይህ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ መከፈቱን እንደሚያውቅ ሌላኛው የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ አረጋግጦልናል።
ይሁንና ይህ ምን ያህል ተጨባጭ ዕውነት ነው የሚለውን ከኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም።
በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የሚያደርጓቸውን የድጋፍ እንቅስቃሴዎች በመቃወምና በማወክ የተጀመረው ብርጌድ ንሓመዶ የተባለው እንቅስቃሴ ከወራት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ እስከማድረግ ደርሷል። አሁን ደግሞ "የአብዮታችን ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ነው" ያሉትን ቢሮ እዚህ መክፈታቸውን የንቅናቄው አስተባባሪ አቶ ኪሮስ አስፍሓ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
"አዲስ አበባ የከፈትነው ቢሮ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት - የአብዮታችን ወይም የእንቅስቃሴያችን ነው። ብርጌድ ንሓመዶ በየ ሀገሩ ነው የሚንቀሳቀሰው እና ለሁሉም እንዲያገለግል ተብሎ ነው የተከፈተው"።
አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ የመክፈቱ ዕድል እንዴት ተገኘ?
ኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች አዲስ አበባ ውስጥ መወያየታቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ "90 ሺህ ያህል ኤርትራዊያን ይኖራሉ" ያሉት አቶ ኪሮስ ይህንን ርምጃ ለመውሰድ የውሳኔያቸው መነሻ የሆነውንም ጠቅሰዋል።
"ኢትዮጵያ ያለው ኹኔታም ሊፈቅድልን ይችላል ብለን ስለተገነዘብን መቅረብ ነበረብን። በተለይ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ እሱን ማስተባበር አለብን በሚል ሀሳብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተን ስብሰባ አደረግን፤ ከወጣቱ ጋር ተነጋገርን ዝግጁ መሆኑንም ገለጸልን" ብለዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት ካለ እንዲገልፁ ለቀረበላቸው ጥያቄም "የግድ ከመንግሥት ጋር መገናኘት አለብህ ማለት አይደለም" ሲሉ መልሰዋል። "አዲስ አበባ መጥተን ከተለያዩ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎች ጋር ተነጋግረናል፣ እውቅና እንዲሰጡን፣ እንዲደግፉን እየነገርናቸው ነው" ያሉት አቶ ኪሮስ ይህንን ዕድል ካለ ኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ሊያገኙት እንደማይችሉ ተጠይቀዋል። ለዚህ በሰጡት ምላሽ ስብሰባ "ሁሌም ስናደርግ ኖረናል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ባለፉት ሃያ ዓመታት መሰል ስብሰባ ማድረጋቸውንና ይህንንም እድል እንዴት እንዳገኙት ሲገልፁ "የስደተኛ መብትህን ተጠቅመህ ስብሰባ ማድረግ፣ መወያየት፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ትችላለህ" ብለዋል።
የኤርትራ መንግሥት ደጋፊና ተቃዋሚዎች በእስራኤል ተጋጭተው ሁለት ሰዎች ተገደሉ
የእንቅስቃሴያቸው የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው?
የብርጌድ ንሓመዶ አስተባባሪ አቶ ኪሮስ የእንቅስቃሴያቸው የመጨረሻ ግብ የኤርትራው ፕሬዝዳንት "ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚመሩትን መንግሥት ማስወገድ" መሆኑን በመጥቀስ ይህንን በሩቅ ሆኖ ማድረግ ስለማይቻል "ወደ ኤርትራ መቅረብ የግድ ይላል" ብለዋል።
"ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ ነው ወደዚህ እየመጣን ያለነው። [ይህም] ምን ያህል ይህ ሥርዓት [የኤርትራ መንግሥት] መወገድ እንዳለበት እንዳመንን እሱ በቂ [ማሳያ] ነው"።
ብርጌድ ንሓመዶ አዲስ አበባ ላይ ቢሮ ስለመክፈቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ማረጋገጥ አልቻልንም
ሌላኛው የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ ይህ የብርጌድ ንሓመዶ ቢሮ አዲስ አበባ ውስጥ መከፈቱን አረጋግጧል። የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ የሱፍ አብደላ ሀገራቸው ባለፉት 32 ዓመታት እንደ መንግሥት ብዙ ጉዳዮች የጎደሏት መሆኑን ለDW ገልፀዋል።
እረብሻ ያደፈረሰው የደን ሃጉ የኤርትራውያን ፌስቲቫል
"ሕዝበ ውሳኔ ተደረገ እንጂ ከዚያ በኋላ ሕጋዊ የሆነ መንግሥት የለውም። በእኛ እምነት ኤርትራ ውስጥ ሕጋዊ የሆነ መንግሥት የለም"።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በበጎ ተለውጦ አለም አቀፍ እውቅና ተችሮት የነበረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ቀስ በቀስ መሻከሩ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል።
ይህ የኤርትራው መንግሥት ተቃዋሚ ብርጌድ ንሓመዶ አዲስ አበባ ላይ ቢሮ ስለመክፈቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ማረጋገጥ አልቻልንም።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ጸሐይ ጫኔ