የሰዎችን ደም ለትንኞች መርዛማ የሚያደርገው አዲሱ የወባ መድኃኒት
ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017ሰሞኑን የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው የወባ በሽታን ለማከም የሚያስችል አዲስ መድኃኒት ተገኝቷል። «ኒቲሲኖን»በመባል የሚጠራው ይህ መድሃኒት፤ በሽታውን የሚያክመው የሰዎችን ደም ለወባ ትንኝ መርዛማ በማድረግ መሆኑን ተመራማሪዎቹ አረጋግጠዋል።ይህም ገዳይ የሆኑ ነፍሳትን ቁጥር ለመቀነስ ተጨማሪ የቁጥጥር መንገድ ሊሆን ይችላል ተብሏል።ኒቲሲኖን ፤ ምንም እንኳን ፕላዝሞዲየም የሚባለውን የወባ ትንኝ ስርጭትን ባይከላከልም በሽታውን ሊያስተላልፉ የሚችሉ ትንኞችን ቁጥር ለመቀነስ አሁን ለተጨማሪ የመስክ ሙከራዎች ታሳቢ እየተደረገ ነው።
ሳይንስ ትራንዚሽናል ሜዲሲን» የተሰኘ የሳይንስ መፅሄት ጥናቱን በተመለከተ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ፤ ኒቲሲኖን በአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር /FDA/ ማረጋገጫ ያገኘ መድሀኒት ሲሆን፤ አልፎ አልፎ በዘር የሚተላለፉ የታይሮሲን መዛባት በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግል ነው።በአዲሱ ምርምር ግን ይህ መድሃኒት «አኖፌሌስ» በመባል የምትታወቀውን የወባ በሽታ አማጭ ትንኝ ለገድል እንደሚችል ፍንጭ ተገኝቷል።ተመራማሪዎቹ «ኒቲሲኖን» ትንኞች ከደም የሚያገኙትን ምግብ ለመፍጨት በሚያስፈልጋቸው ወሳኝ ኢንዛይም ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልፀዋል።
ትንኝ የሚገድለው መድሃኒት ምንድን ነው?
ተመራማሪዎቹ በቤተ ሙከራ ባደረጉት ምርምር ሴቷ የወባ ትንኝ «ኒቲሲኖን» በውስጡ የያዘ ደም በምትመገብበት ወቅት መድኃኒቱ ገዳይ መሆኑ ታይቷል። አዲሱ መድሃኒት ፀረ ተባይ መድሐኒቶችን የሚቋቋሙ ትንኞችን ጭምር በመግደል ከዚህ ቀደም ከነበረው «ከአይቨርሜክቲን»ከተሰኘው የወባ ትንኝ መድኃኒት የተሻለ ነው ተብሏል። በአሜሪካ የኖትር ዳመ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ እና የጥናቱ የጋራ ተቆጣጣሪ የሆኑት አልቫሮ አኮስታ-ሴራኖ እንደሚገልፁት፤ሌላው ጠቃሚ ነገር አዲሱ መድሃኒት ኬሚካሎችን የመቋቋም ባህሪ ባዳበሩ ሌሎች የትንኝ ዝርያዎች ላይ ውጤታማ መሆኑ ነው።
«ፀረ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ትንኞችን ይገድላል። ለብዙ አሥርተ ዓመታት በመስክ ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ ጥቂት ፀረ ተባይ መድኃኒቶች አሉ [ነገር ግን] መድሃኒቱን የሚቋቋሙ [ትንኞች] አሉ። እነዚያን መድሃኒት የሚቋቋሙትን በ«ኒቲሲኖን» ሞክረናቸዋል። እናም በቀላሉ በመድሃኒቱ ሊጠቁ ከሚችሉት ትንኞች ጋር እኩል ይጋለጣሉ።እናም ከ«አይቨርሜክቲን»የተሻለ የሚሰራ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጥቅሞችንም ያስገኛል።» በማለት አብራርተዋል።
ይህ መድሃኒት /ኒቲሲኖን/ በየቀኑ ዝቅተኛ መጠን ያለው 2 ሚሊ ግራም ኒቲሲኖን ቢወሰድ እንኳ ትንኞችን የሚገድል መሆኑ ታይቷል።እነዚህ ግኝቶች «ኒቲሲኖን» ለወባ አማጭ ትንኞች ቁጥጥር እና የወባ ስርጭትን ለመከላከል ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ መንገድ ጠርገዋል።
በቤተሙከራ የተደረጉ ምርምሮች እንዳረጋገጡት ትንኟ «ኒቲሲኖን»ን የወሰደ ሰው በምትነክስበት ጊዜ የመድኃኒቱ መኖር ነፍሳቱ ከደም የወሰዱትን ምግብ መፍጨት እንዳይችሉ ያደርጋል። ከ 24 ሰዓታት በኋላም ነፍሳቱ እንዲሞቱ ያደርጋል። ኒቲሲኖን ለሰው ልጆች ሳይሆን መርዛማነቱ ለትንኞች ብቻ ነው። ይህም «ኢቨርሜክቲን» ከሚባለው የወባ ትንኝን ከሚከላከል ሌላ መድሃኒት ጋር ሲነጻጸር «ኒቲሲኖን»በደም ውስጥ የበለጠ ለረጅም ጊዜ ይቆያል። እንዲሁም በእንፋሎት እና በፈሳሽ መልክ ሊረጭ የሚችል እና እንደ ፀረ-ተባይ ሊያገለግል የሚችል በመሆኑ ሁለገብ ነው።
በደም ውስጥ ፀረ-ተባይ መድሃኒት?
መድኃኒቱ ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ውጤታማ መሆኑን ለማረጋገጥ ተጨማሪ የመስክ ሙከራዎች ቢያስፈልገውም፣ የመጀመሪያዎቹ ግኝቶች እንደሚጠቁሙት የወባ ትንኝ ቁጥሮችን ለመቆጣጠር ርካሽ እና ውጤታማ በመሆን ተስፋ ሰጪ ነው።
በለንደን የንጽህና እና የትሮፒካል ህክምና ትምህርት ቤት በተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አና ላስት፤ ምንም እንኳ በጥናቱ ያልተሳተፉት ቢሆንም፤ ግኝቱ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።በተለይ በአፍሪካ ተጋላጭ በሆኑ ማህበረሰቦች ውስጥ በቅርቡ በተደረገው የኢቨርሜክቲን የመስክ ምርመራ የተገኘው ውጤት ላስት እንዳሉት በጣም ጠቃሚ የሆነ ስራ ነው።« በጣም ጠቃሚ የሆነ ስራ ነው።እኔ እንደማስበው መስክ ላይ ባሰብነው እና በጠበቅነው መንገድ እንዳልተከናወነ ከታየው፤ ከአብዛኛው የኢቨርሜክቲን የመስክ ሙከራዎች እና ከተገኙት ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ ውጤቶች አንፃር የተሻለ ነው።»በማለት ገልፀዋል።
የወባ በሽታን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ2023 ዓ/ም 263 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን ፤በዚህም ምክንያት 597,000 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።ያምሆኖ እንደ ወባ ያሉ በትንኞች የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመዋጋት በርካታ ሕክምናዎች እና ቴክኖሎጂዎች አሉ።
በእነዚህ ሕክምናዎችም ከ 2000 ዓ/ም ጀምሮ 2.2 ቢሊዮን የጤና ችግሮችን እና 12.7 ሚሊዮን ሞትን መከላከል ተችሏል ተብሎ ይታመናል ።
ለምሳሌ እንደ ሞሶኪሪክስ /Mosquirix/ በሚል ለገበያ የቀረበው የ RTS,S የተባለው ክትባት ከ5-18 ወር እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ህጻናት ላይ ከባድ የጤና ችግሮችን ለመከላከል 30% ውጤታማ ሲሆን ለዚህም አራት የክትባት መጠን ያስፈልገዋል።
በዚህ ሁኔታ የወባ በሽታ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የአሁኑን አዲስ መድሃኒት ጨምሮ ሌሎች ክትባቶችና መድሃኒቶችን ለመስራት ምርምሮች ቀጥለዋል። መድሃኒት ለማግኘት ከሚደረገው ምርምር በተጨማሪ፤በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የጤና አካላት በሰፊው የሚሰራጩ፤ ፀረ-ነፍሳት ኬሚካል የተረጩ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበሮችም ጠቃሚ መሳሪያዎች ናቸው።
በግሎባል ፈንድ የኤድስ፣ የሳንባ ነቀርሳ እና የወባ መከላከያ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ኢስትሬላ ላስሪ እንዳሉት እንደ ክትባት እና መድሃኒቶች ሁሉ ፀረ ትንኝ መድሃኒት የተረጩ አጎበሮችም በሽታውን ለመከላከል “30% ውጤታማ ናቸው” ብለዋል።
የግሎባል ፈንድ መረጃ እንደሚያሳየው በታንዛኒያ እና ቤኒን በተደረጉ ሙከራዎች ከስድስት ወር እስከ 10 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሕፃናት ላይ «ፒሪትሮይድ» እና «ክሎሮፔናፒር» በተባሉ በሁለት ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች የተረጩ አጎበሮችን በመጠቀም የወባ በሽታን በግማሽ መቀነስ ተችሏል።ይህንንም ላሰሪ እንዳሉት፤ በተቻለ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ለወባ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ለማዳረስ እየተሞከረ ነው።
ነገር ግን ልክ በአጎበሮች ላይ ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን እንደ መጠቀም ሁሉ በሽታውን ለመቆጣጠር ለሚሞክሩ ቡድኖች የነፍሳት ቁጥጥር አስፈላጊ ሆኖ ይቆያል። ይህም የትንኞቹን እጭ መቆጣጠርን እና የወባ ትንኞች ከመራባታቸው በፊት ማጥፋትን ያጠቃልላል።
በዚህ ሁኔታ ወባ በደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ እና እስያ በሚገኑ በርካታ ሀገሮች ተወግዷል።ነገር ግን ይህን የሚሰሩ ቡድኖች አገልግሎቱን መስጠት ካልቻሉ፤የወባ አማጭ ተንኞችን ለማጥፋት የሚደረጉት ርምጃዎች ሊቆሙ የሚችሉበት አደጋ አለ።የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የትራምፕ አስተዳደር በዩኤስ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሚደረገውን ሰፊ የድጋፍ መርሃግብር በማቋረጥ እንደ ወባ ላሉ የጤና ምርምሮች የሚሰጠውን ገንዘብ ሊቀንስ ይችላል።
ለጤና ምርምሮች የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ
ከዚህ አንፃር አሜሪካ፤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚደረጉ የሕክምና ምርምሮች የምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ሊቀንስ ይችላል የሚል ስጋትም አለ።ነገር ግን ፕሮፌሰር ላስት ድጋፉ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ።
«በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው።እኔ እንደማስበው በጤና ስርዓቶች እና መርሃግብሮች ላይ በእርግጠኝነት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገሮች ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላል። ነገር ግን እንደ «ኒቲሲኖን» ባሉ አዳዲስ ሞሎኪዮሎች ልማት አውድ ውስጥ ከዚያ የበለጠ ተደራሽ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።ባለፉት አስርተ ዓመታት ወይም ከዚያ በላይ ከፍተኛ ትርፍ ያስገኙ አሁን ያሉን ምርጥ መሳሪያዎችን መጠበቅ እና ማቆየት ላይ ብዙ ትኩረት መደረግ አለበት።»ሲሉ ተናግረዋል።
የወባ ትንኞች በዓለም ላይበሽታን ለሰው ልጆች በማሰራጨት በጣም ገዳይ ተውሳኮች ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን፤ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ገዳይ በሆኑ በሽታዎች እንዲያዙ ያደርጋሉ።የወባ በሽታ በተለይ ከስሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በሽታ ነው።ከዚህ አንፃር በዓለም አቀፉ የሳምባ ነቀርሳ እና የኤች አይቪ ኤድስ ፈንድ ከፍተኛ የወባ አማካሪ የሆኑት እስቴርላ ላስሪ ይህንን በሽታ ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት የገንዘብ ድጋፍ ከሌለው ስራው የተገደበ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።
«ለዚያ የሚቀርበው ምክረ ሃሳብ ጣቢያዎቹ ጥቂት ሲሆኑ፣ ተስተካክለው እና ተደራሽ ሊሆኑ በሚችሉበት ጊዜ መሰራት እንዳለበት ነው። ይህ መሆን አልነበረበትም። ነገር ግን በትንኝ አማካኝነት በከተማ በሚከሰት የወባ በሽታ አሁን የበለጠ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።» ብለዋል።ይህም የወባ በሽታ ስርጭት እንዲጨምር ያደርጋል የሚል ስጋትም አላቸው። «እንጨነቃለን።ፔዳሉ ከእግር እየወለቀ በመምጣቱ እና የጉዳዩን መጨመር ማየት በመቻላችን።እና እንደሱ ነው። በወባ ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፤ ለምንሠራባቸው ሀገሮች ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም የጤና ደኅንነት ጉዳይ ነው። ማህበረሰቦችን ወደ ጤናማነት እና ጠንካራነት ይለውጣል። እንዲሁም በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ እይታ የበለጠ ጠንካራ ያደርጋል።»
በመሆኑም በአሜሪካ የሚደረገው የአዲሱ የወባ በሽታ መድሃኒት የ«ኒቲሲኖን»ቀጣይ ምርምሮችም በዚሁ የገንዘብ ድጋፍ ቅነሳ እክል እንዳይገጠመው ስጋት አለ።
ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ