አዲሱ ተስፋ ሰጪ የወባ መከላከያ መድኃኒት ግኝት
ረቡዕ፣ ጥር 21 2017
የወባ በሽታ አሁንም ድረስ ከፍተኛ የዓለም የጤና ስጋት ሲሆን፤፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት በስፋት ከሚታዩ ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ነው።በኢትዮጵያም ወባ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ወደ 248 ሚሊዮን ሰዎች በ 2023 ዓ/ም ደግሞ ወደ 263 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል።
የአሜሪካ ተመራማሪዎች ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት አዲስ ጥናት የወባ በሽታን በተሻለ ሁኔታ ለማከም የሚስችል አዲስ ፀረ እንግዳ አካላት ተገኝቷል።ሰሞኑን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሳይንስ መፅሄቶች ለህትመት የበቃው ይህ ጥናት፣ ወባን በመዋጋት ረገድ ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል።
በስዊዘርላንድ በአንድ ለትርፍ ያልተቋቋሙ የወባ መድሃኒት ምርምር ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ክርስቲና ዶኒኒ፤ እንደገለፁት በ«ስፖሮዞይት» በሚባሉት የወባ በሽታ አማጪ ተህዋሲያን የህይወት ዑደት ላይ ዒላማ ያደረገው አዲሱ ግኝት፤ አዳዲስ ፀረ ወባ መድሃኒቶችን ለመስራት የሚያግዝ ታላቅ ግኝት ነው።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ልዩ ክሊኒክ የውስጥ ደዌ ሀኪም እና የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ወንደወሰን አሞኘ ግኝቱ ጅምር ላይ ያለ ቢሆንም ወባን ለማከም ተስፋ ሰጭ ነው ሲሉ የክርስቲና ዶኒኒን ሀሳብ ያጠናክራሉ።
አዲስ የወባ ህክምና አስፈላጊነት
የወባ በሽታን ለመግታት ከዚህ ቀደም አዳዲስ መድሃኒቶች ተዘጋጅተዋል።ከነዚህም መካከል በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሃላፊነት በሽታው በተስፋፋባቸው ክልሎች ለህጻናት የሚሰጡ ሁለት የወባ መከላከያዎች መድሃኒቶች ተሰርተዋል። ያም ሆኖ፤ በአሜሪካ ሜሪላንድ በብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች የበሽታ መከላከያ ስርዓት ተመራማሪ የሆኑት ጆሹዋ ታን እነዚህ ክትባቶች ወባን ለመዋጋት ትልቅ እመርታ ቢሆኑም በዘርፉ አሁንም ቢሆን የወባን ጫና ለመቀነስ ተጨማሪ እና አስቸኳይ መፍትሄዎች ያስፈልጋሉ ባይ ናቸው።
ተመራማሪዋ ክርስቲያና ዶኒን እንደሚሉትም አሁን ያሉት የወባ ክትባቶች በጣም ከፍተኛ የሆነ የወባ በሽታ ባለባቸው አካባቢዎች ከ50% ያነሰ የመከላከል አቅም ያላቸው ናቸው።
አሁን ያሉት ፀረ-ወባ ፀረ እንግዳ አካላትም በወባ ክትባቶች ላይ ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉ ናቸው።ይህም የክትባትን ውጤታማነት የበለጠ ሊቀንስ ይችላል።«በሌላ አነጋገር የሞኖክሎናል ፀረ እንግዳ አካላት የበሽታ መከላከያ ምላሾችን ወደ መቀነስ ወይም የክትባት ውጤታማነት ሊያስተጓጉል ይችላል።» ብለዋል ዶኒኒ።
ወባ በተለይ ከስሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በሽታ ነው የሚሉት ዶክተር ወንድ ወሰንም እስካሁን ብቃት ያለው የመከላከያ መንገድ አለመኖሩን ይገልፃሉ።
አዲሱ የወባ ፀረ እንግዳ አካል ተስፋ ሰጪ ይመስላል
በአሜሪካ በብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች የበሽታ መከላከያ ስርዓት ተመራማሪው ጆሹዋ ታን እና ባልደረቦቻቸው ጥናት የተገኘው አዲሱ የወባ ፀረ እንግዳ አካል ግን ተስፋ ሰጪ ይመስላል።የጥናቱ ዓላማ በክትባት ውስጥ ጣልቃ ሳይገባ ወባን ለማከም የሚያስችል አዲስ ፀረ እንግዳ አካላትን ማዘጋጀት ነው።ይህም ፀረ እንግዳ አካላት በሚተሳሰሩበት «ስፖሮዞይት»በሚባለው ተውሳክ ላይ ከዚህ ቀደም ያልተሰራባቸውን አዳዲስ ክፍሎች በመፈለግ የሚከናወን ነው።ይህም ዶክተር ወንደወሰን እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የነበሩ ክትባቶች ኢላማ ከሚያደርጉት የተለዬ ነው።
በዚህም ለተወሰኑ የተውሳኩ ክፍል ምላሽ የሚሰጡ ፀረ እንግዳ አካላትን /mAbs /በመለየት ወባ አማጭ ተውሳክን ወይም «ስፖሮዞይቶችን» ማጥፋት ይችሉ እንደሁ በአይጦች ላይ ሙከራ አድርገዋል።
በዚህ ሙከራ MAD21-101 የተባለው ፀረ እንግዳ አካል /ሞኖክሎን አንቲቦዲ /mAb/ «ፕላዝሞዴየም ፋንሲፈርም»የተባለውን የወባ በሽታ በመከላከል ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህም የወባ አማጭ ተውሳኮች ጉበትን እና የደም ህዋሳትን በመጉዳት በሰዎች ላይ የሚያስከትሉትን በሽታ እና ሞት ያስቀራል ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት /monoclonal antibodies/ (mAbs) ፀረ-ወባ እና ፀረ እንግዳ አካላት በአዋቂዎችም ሆነ በህፃናት ላይ ከፍተኛ ሞት የሚያስከትለውን «ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም» የሚባለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ መፍትሄ ነው።
የፀረ-ወባ ፤ፀረ እንግዳ አካላት የሚሠሩት ከትንኞች ወደ ሰዎች ከሚተላለፉ «ስፖሮዞይት» ከሚባሉ ፕሮቲን መሰል ጥገኛ ተውሳኮች ጋር በመተሳሰር ነው።እነዚህ ፀረ እንግዳ አካላት የሰዎች የበሽታ ተከላካይ ስርዓት ተህዋሲያንን ወዲያውኑ እንዲጠፋ ለማድረግ ያግዛሉ።
ግኝቱ ተጨማሪ ምርምር ይፈልጋል
የመከላከያ ክትባቶች ደግሞ ወደፊት የሚመጡ በሽታዎችን ለመዋጋት በሽታ የመከላከል ስርዓትን በማሰልጠን በተለየ መንገድ ይሰራሉ። ያም ሆኖ ሳይንቲስቶቹ አዲስ ተለይተው የታወቁትን ፀረ እንግዳ አካላት እንቅስቃሴ እና ውጤታማነት ለመፈተሽ ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ምክንያቱም እነዚህ ፀረ እንግዳ አካላት እስካሁን በአይጦች ላይ ብቻ የተሞከሩ በመሆናቸው፤በሰዎች ላይ ይሰሩ እንደሁ ገና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ይህ ፀረ እንግዳ አካል ወደፊት በሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ከሆነ፤ ዶክተር ወንደ ወሰን እንደሚገልፁት በሁለት መንገዶች ሊያገለግል ይችላል ።አንደኛው አዲስ ክትባት ለመስራት ወይም ፀረ እንግዳ አካላቱ በሽታውን ለማከም እንዲውሉ ማድረግ ይቻላል።በዚህ መልኩ አዲሱ ግኝት ውጤታማ ከሆነ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በሽታው ከፍተኛ ጉዳት ለሚያደርስባቸው ሀገራት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ዶክተር ወንድ ወሰን ገልፀዋል።ተመራማሪዋ ዶኒኒ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ያሉት የወባ የመከላከያ መድሃኒቶች በየወሩ መወሰድ ያለባቸው ሲሆኑ፤ነገር ግን አዲሱ ፀረ እንግዳ አካላል በሆነ ወቅት አንድ ጊዜ ወይም አልፎ አልፎ ሊሰጥ ይችላል።በአንድ ጊዜ በሚሰጠው የመድሃኒት መጠንም በፍጥነት የመከላከል አቅምን ይሰጣሉ።, ክትባቶች ግን ሶስት መርፌዎች ያስፈልጋቸዋል ። የበሽታ ተከላካይ ምላሽ እስኪያድግ ድረስም ሶስት ወር ይወስዳል ብለዋል።
እንደ ተመራማሪዎቹ የጥናቱ ግኝቶች ወደፊት ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶች እና አዳዲስ ፀረ እንግዳ አካላት እና የበሽታ መከላከያ ክትባቶች እንዲፈጠሩ ያስችላል።
በዚህ ጥናት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ዘዴም ከወባ በተጨማሪ ሌሎች በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ለመከላከል አዲስ መንገድ እንዲፈጠር ይረዳልም ተብሏል።
በ2030 ወባን ማስወገድ ይቻላልን?
በጎርጎሪያኑ 2015 ፣ የዓለም ጤና ድርጅት በ 2030 ቢያንስ በ 90% የወባ በሽታን እና ሞትን ለመቀነስ ስልት ነድፏል።
ያም ሆኖ እንደ ዶኒኒ ያሉ ባለሙያዎች በበሽታው ላይ ጉልህ መሻሻል ቢታይም ፤አሁን ያለው የወባ በሽታን የማስወገድ አካሄድ በ2030 የሚሳካ አይመስልም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በወባ የሚሞቱ ሰዎች ከ2000-2022 መካከል እየቀነሱ ቢሄዱም አሁንም ድረስ በዓመት ወደ 250 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው ይጠቃሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት መድሀኒት እና ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን የተላመዱ እና መቋቋም የሚችሉ የወባ ትንኝ ዝርያዎች መስፋፋት፣ ጥሩ ያልሆነ የጤና ስርዓት እና የአየር ንብረት ለውጥ ለቀጣይ እንቅፋት ናቸው።
ወባን ለማጥፋት ከተፈለገ አዳዲስ ህክምናዎች ርካሽ እና ለአወሳሰድ ቀላል መሆን አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ መድሃኒቶቹ በተለይ እርጉዝ ሴቶች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ሊወስዷቸው የሚችሉ እና የወባ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ሊቋቋሟቸው የማይችሉ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ