አደገኛዉ የአዲስ አበባ-ሰላሌ-ጎጃም መንገድ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1 2017
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰላም ብርቱ ችግር ውስጥ ገብቶ የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ከተፈተነባቸው ዞንና አካባቢዎች ሰሜን ሸዋ ዞን (ሰላሌ) አንዱና ቀዳሚው ነው ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል። በዚህ ዞን በበረታው አለመረጋጋት ተደጋጋሚ የነዋሪዎች እገታ እና የጸጥታው መደፍረስ አስከፊ ውጤቶች ተደጋግሞ ስለመከሰቱም በተደጋጋሚ ተዘግቧል። ከሌሎች የክልሉ ዞኖች በተሻለ ለመዲናዋ አዲስ አበባ እጅግ ቅርብ ስፍራ ላይ የምትገኘው ይህቺ ዞን እንደ ቅርበቷ ሳይሆን እንደሩቅ ግዛት በከፍተኛ የፀጥታ ችግር መፈተን ከተለመደም አምስት ዓመታት ሊደፍን ነው።
በፀጥታ ችግሩም ምክንያት አሰቃቂ ክስተቶች ተደጋግመው መሰማታቸው በገሃድ የሚታወቅ ነው። የአርሶ አደሮች ቤቶች በዚህ ዞን በተደጋጋሚ ሲነድ፣ «የሚሊሻ ወይም የታጣቂ ዘመድ አለህ» በሚል ብዙ ሰላማዊ ዜጎች እየታፈሱ ሲታሰሩና ታግተው ከአቅማቸውም በላይ የሆነ ገንዘብ ሲጠየቁም በተደጋጋሚ ሰምተናል።
ከሁሉም በላይ ግን ዞኑን በሚያቋርጠው ትልቁ የፌዴራል መንገድ ላይ በተደጋጋሚየተሰማው የተሳፋሪዎች እገታ በርካቶች በዚህ መንገድ ለመጓዝ ሲያስቡ ፍርሃት እንዲወራቸው እያስገደደ ነው። በቅርቡ እንኳ ሙሉ አውቶብስ ተሳፋሪዎች ታግተው መወሰዳቸው በተዘገበበት በዚህ አውራ ጎዳና መጓዝ ሥራቸው ለሆነው ሾፌሮች እና ቤተሰብ ለሚጠይቅ መንገደኛም ጭምር ሀሳብ ሆኖባቸዋል።
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የዞኑ ያያ ጉለሌ ወረዳ ነዋሪ በዋናው መንገዱ የመጓዝ ስጋት ቢኖረውም ከሌላው የውስጥ ለውስጥ ወረዳዎች አገናኝ መስመር ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ይላሉ። «ከዚህ ከአዲስ አበባ ስንሄድ የጫንጮ ኬላ ጠዋት ከ2 ሰዓት በፊት አይለቀቅም። አንዳንዴ ነው በአንድ ሰዓት መንገዱን ክፍት የሚያደርገው። በተቃራኒው ከዚያ ከኩዩ ወደ አዲስ አበባም ከሁለት ሰዓት በፊት መንገዱ አይለቀቅም። ከሰዓትም ቢሆን አንዳንዴ 11 ሰዓት አንዳንዴ ደግሞ ከ10 ሰዓት በኋላ ኬላው ይዘጋል። ከዚህ ባለፈ ሰው በየትኛውም ሰዓት በራሱ ላይ ወስኖ ነው ይህን መንገድ የሚጓዘው» ሲሉ ስጋታቸውን አስረድተዋል።
በዚህ አውራ መንገድ ላይ የሚፈጸመው የተሳፋሪዎች እና አሽከርካሪዎች እገታ ደግሞ ሌላው የትራንስፖርት ስርዓቱን ያወከው ጉዳይ ሆኗል። ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር ወረታ እየተመላለሱ ሸቀጥ በመጫን ወደ ተለያዩ ከተሞች ማድረስን የሰርክ ተግባራቸው ያደረጉት አንድ ለደኅንነታቸውሲባል ስማቸውን ያልገለጹት አሽከርካሪ በዚሁ ስጋት ሰፍኖበታል ባሉት ጎዳና በሚያሳልፉት ሰቀቀን መማረራቸውን ይናገራሉ። «እዚህ ስትመጣ ኬላ በዚያ ወደ ኦሮሚያ ስትመጣ እገታ ፈርተህ በቃ መሮናል በቃ» በማለትም በዚህ መንገድ ላይ ተደጋግሞ ስለሚገጥማቸው ብርቱ ፈተና ገልጸዋል።
በዚህ ላይ ዶይቼ ቬለ ከሰሜን ሸዋ ዞን ወና አስተዳዳሪ አቶ ከፋለ አደሬ ጋር በመደወል አስተያየታቸውን በዘገባው ለማካተት ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልሰመረም። በሰሜን ሸዋ ዞን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የመንግሥት ፀጥታ አካላት ውጊያ ከጀመሩ አምስት ዓመታት ወዲህ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ በርካቶች የሕይወት ዋጋም ጭምር ከፍለዋል።
በዚህ በያዝነው ዓመት እንኳ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ከ10 ያላነሱ የዞንና ወረዳ አመራሮች በታጣቂዎች ሕይወታቸው መቀጠፉን ዶይቼ ቬለ በተደጋጋሚ ዘግቧል። በኅዳር ወር መጀመሪያ በወጫሌ ወረዳ በታጣቂዎች ከ45 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ እንዲሁም የሱሉልታ ወረዳ እና በያያ ጉሌሌ ወረዳ የተፈጸመ የአመራሮች ግድያም ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ