አንድ ለአንድ፤ ከአንጋፋው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ መሐሪ አብርሃም
ዓርብ፣ ሐምሌ 25 2017እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1969 በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ተወለደ፤ እዛው አደገ። የያኔው ብላቴና የአሁኑ አንጋፋ ጋዜጠኛ መሐሪ አብርሐም። የአቶ ኢሳያስ አፍወርቂ መንግስት ሕገ መንግስት ባይኖረውምየፕረስ ነጻነት አዋጅ በተናጥል አውጆ እንደነበር ያስታውሳል። ይህን ዕድል በመጠቀምም በእንግሊዝኛ «ዘ ሚረር ኢንፎርሜሽን ኢንተርፕራይዝ» የሚል የመገናኛ ብዙሃን ተቋም በመመስረት በስሩ በትግርኛ «መስተያት» በእንግሊዝኛ ደግሞ «ዘ ሚረር» የሚሉ ጋዜጦች ማሳተም መጀመሩን አጫውቶናል። በተለያዩ ጊዚያት ስለ የመጀመሪያው የኤርትራ የግል የሕትመት መገናኛ ብዙሃን ሲወራ መስራቾች ሌሎች ተደርጎ እንደሚገለጽ ቅሬታውን የገለጸው አንጋፋው ጋዜጠኛ መሐሪ አብርሐም ይሁንና በኤርትራ የፕረስ ነጻነት ሲታወጅ የመጀመሪያው የግል የሕትመት ጋዜጣ መስራች እራሱ እንደነበር ይገልጻል።
በመሰረተው ጋዜጣም የፕረስ ነጻነት መታወጁን በበጎ ቢወሰድም «ሕገመንግስታዊ ዋስትና ሊሰጠው ይገባል» የሚል ትችት በጋዜጣው በመጻፉ በመንግስት የጸጥታ ሰራተኞች ጥርስ እንዲነከስበት እንዳደረገው ይገልጻል።
በመቀጠልም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረውን መሻከር በመተንተን ወደ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል የሚተነብይ ጽሑፍ በጋዜጣው በማሳተሙ ሌላ ተጨማሪ ቂም በመንግስት የፀጥታ አካላት እንደተቋጠረበት አጫውቶናል። ሌሎች የኤርትራ መንግስትን የሚተቹ ፅሑፎችም በድፍረት ያሳትም እንደነበረ ያጫወተን ጋዜጠኛ መሐሪ ጫናው እየበረታ ሲሄድ ያጋጠመውን የውጭ ዕድል በመጠቀም መጀመሪያ ወደ እስራኤል ከዚያም ወደ ስዊድን መሰደዱን ይገልጻል።
በአሁኑ ጊዜ ስዊድን አገር በሚታተመው «ኤክስፕረሰን» እና ሌሎች ሚድያዎች በውጭ የዜና ክትትል በፍሪላንሰርነት፤ እንዲሁም በቲቪ ዘተ በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በዋና አዘጋጅነት፤ በሐርመኒ ሚድያ ደግሞ በዋና ፕሮግራም ዳይሬክተርነት እና የቦርድ አባል በመሆን እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ በስዊድን አገር በምግብ ዝግጅትና አመጋገብ ሙያ ተምሮ በዚሁ መስክም በተደራቢ እያገለገለ እንደሚገኝ አጫውቶናል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ መሐሪ አብርሃ በኤርትራ ያለው የፕረስ ነጻነት ሁኔታ፤ ለሙያው የከፈለው መስዋዕትነትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠንን ቃለ ምልልስ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንድታዳምጡት በአክብሮት እንጋብዛለን።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ