4 ፓርቲዎች ኦነግና ኦፌኮ በኦሮምያ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ያቀረቡትን ጥያቄ ተቃወሙ
ሐሙስ፣ የካቲት 27 2017እናት፣ ኢሕአፓ፣ መኢአድ እና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፤ ኦነግ እና ኦፌኮ ከሳምንታት በፊት በኦሮሚያ ክልል የጋራ "ሽግግር መንግሥት" እንዲመሠረት ከተለያዩ አካላት አደራ መቀበላቸውን በሚመለከት ያራመዱትን አቋም ተቃወሙ። አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ "የሽግግር መንግሥት በተናጠል በክልል ደረጃ ሊመሠረት አይችልም" ብለዋል። የሁለቱን ፓርቲዎች አቋም ክልሎችን ከክልሎች የሚያጋጭ እና ለኢትዮጵያ አደጋ የሚያስከትል ነው ያሉት አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ኹኔታው "እሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ የሚቆጠር ነው" ሲሉ ነቅፈዋል። አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የታሰበው "የሽግግር መንግሥት" ጥያቄ ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ መፍትሔ የሚያመጣ እንዳልሆነም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አዲስ አበባ ውስጥ ከተለያዩ የክልሉ ኹኔታ ይመለከተናል ካሉ ተወካዮች ጋር ከተወያዩ በኋላ አወጡት በተባለው መግለጫ፤ በክልሉ የሽግግር መንግሥት ይመስረት የሚለውን ጨምሮ ተወያዮቹ የይገባኛል ጥያቄዎች ያነሱባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ጭምር ስለመኖራቸው መረጃ እንዳላቸው መኢአድ፣ እናት፣ ኢሕአፓ እና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ጠቅሰዋል። የኦነግና ኦፌኮ «የሽግግር መንግሥት» ምስረታ ምክረሃሳብ
የኦሮሚያ ክልል ጉዳይ ሌሎች ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚመለከት መሆኑን የጠቀሱት አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ይህንን አቋም ነቅፈው ተችተዋል። አካሄዱንም "ፍትሕ አልባ፣ ኢ- ሕገ መንግሥታዊ" ነው ብለውታል። የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሃይማኖት አብርሃም ይህንን የሁለቱን ፓርቲዎች አቋም ሀገር የሚያጠፋ ነው ብለውታል።
አዲስ አበባን የአንድ ክልል አድርጎ ማሰብ እና መጠየቅ "ከቀን ቅዠት" ተለይቶ አይታይም ያሉት እናት፣ መኢአድ፣ ኢሕአፓ እና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ሌሎች አካባቢዎችንም ወደ ኦሮሚያ ክልል "ለማጠቃለል መሻት" በክልሎች ላይ "ወረራ ከመፈፀም ተለይቶ የማይታይ" ነው ብለዋል። የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው "እነዚህ የይገባኛል ጥያቄዎች ከምን ሊመነጩ እንደቻሉ ግራ ያጋባል" በማለት የክልል ዳር ድንበር የሚል አገላለጽም አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል። የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው ይህ ኹኔታ የሀገርንም የክልሉንም ችግር ይፈታል ብለን አናምንም ብለዋል። አራቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ የሁለቱ ፓርቲዎች አቋም ኢትዮጵያን "ለበርካታ አሥርት ዓመታት ወደኋላ የሚመልሳት" ስለሆነ ይልቁንም ተረባርበን ሀገርን ወደማሳደግና ከችግር ወደማውጣት ልናተኩር ይገባል ይላል።ኦፌኮ እና ኦነግ “የሰላም መፍትሄ” ለምን አወዛገበ?
ኦነግ እና ኦፌኮ ከሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ከኦሮሞ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ወጣ የተባለው አቋም በክልሉ ላለው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ የሚያበጅ አቅጣጫ ስለመሆኑ ተነግሯል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ገለታ