ትግራይ ክልል የፖለቲካ አለመረጋጋትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 17 2017በትግራይ ክልል ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዳያገግም እንቅፋት መሆኑን የዘርፉ ተዋንያን ዐሳወቁ ። በተለያዩ ሀገራት የሚወጡ የጉዞ ማሳሰቢያዎች አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ ስለመሆናቸውም የትግራይ ቱሪዝም ጽ/ቤት ገልጿል ።
በትግራይ ክልል ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የፀጥታ ሥጋት የቱሪዝም ዘርፉ እየጎዳ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ ። በትግራይ ክልል ተዳክሞ የነበረ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በተለይም ጦርነቱ ካስቆመ የሰላም ስምምነት በኋላ በተወሰነ መልክ መነቃቃት አሳይቶ እንደነበረ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይገልፃሉ። ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም የቱሪስቶች መዳረሻ ከሚባሉ ቦታዎች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንዳሉን ወደ ትግራይ ክልል የሚመጡ የውጭ ይሁን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ቀንሷል ይላሉ ። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የፈጠረው የጉዞ ማሳሰብያ መሆኑ በርካቶች ይገልፃሉ።
የትግራይ ክልል ቱሪዝም ቢሮ በትግራይ ስላለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ በሰጠው መግለጫ በተለያዩ ሀገራት የሚሰጡ የጉዞ ማሳሰብያዎች የቱሪስቶች እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩ ያነሳል።
የትግራይ ክልል ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር አፅበሃ ገብረእግዚአብሔር "የትግራይ ምስል በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽቷል። የትግራይ ካርታ ከሙሉ ቀይ ወደ ደበዘዘ ቀይ ማለትም በአንፃራዊነት የተሻለ ተቀይሮ ነበረ። ከዛ ቀጥሎ በተለይም ከመጋቢት ወር በኃላ ባለው ግን፥ 23 ሀገራት በጋራ ካወጡት የጉዞ ማሳሰብያ መግለጫ በኃላ ተመልሶ ወደቀይ ገብቷል። እሱን ተከትሎ የቱሪስቶች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል" ይላሉ።
በትግራይ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝ ገቢ የበርካቶች መተዳደርያ ሲሆን በክልሉ ኢኮኖሚም ከፍተኛ ድርሻ አለው። የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ እንደሚለው ካለፉት ጊዜያት እና ወቅቶች ሲነፃፀር ዝቅተኛ ቢሆንም እንዲሁም የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም፥ አሁንም በተወሰነ መጠን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ እየመጡ ነው። የትግራይ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃይላይ በየነ "ባለፉት ሦስት ወራት የውጭ ሀገራት ዜጎች የሆኑ 1354 ቱሪስቶች ወደ ትግራይ መጥተው የተለያዩ መስህቦች ጎብኝተዋል።
ለሃይማኖታዊ ተግባራት፣ ለጉብኝት እንዲሁም ለሌሎች ዓላማዎች ወደ ትግራይ የመጡ አልያም በትግራይ የተንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር ደግሞ የተጣራ 50 ሺህ ነው። ይህ ከገቢ አንፃር ስንመለከተው በአጠቃላይ 200 ሚሊዮን ብር አካባቢ ገቢ ተገኝቷል" ሲሉ ገልፀዋል።
ፖለቲካዊው ሁኔታ ተከትሎ በትግራይ ክልል ከቱሪዝም በተጨማሪ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍም ከፍተኛ የእንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ይስተዋላል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ