ትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ የመሠረተ ልማት ዳግም ግንባታ አለመኖር ዳፋው
ሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2017ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ይጠበቅ የነበረው የዳግም ግንባታ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ አለመሆኑ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ችግሮች እያስከተለ መሆኑ ተገለጠ ። የኢኮኖሚ ማነቃቅያ ድጋፎች ከጦርነቱ በኋላ አለመተግበራቸው በክልሉ ችግሩን እንዳባባሰው ተጠቅሷል ። ውድመት የደረሰባቸው የትምህርት፣ ጤና እና ውኃ ተቋማት ዳግም ግንባታ ሊደረግላቸው እእንደሚገባ ንዲሁም ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ ርምጃዎችም ሊወሰዱ እንደሚገባ ነዋሪዎች በመጠየቅ ላይ ናቸው ።
በ2013 እስከ 2015 ዓመተ ምህረት ለሁለት ዓመት በትግራይ የተካሄደው ጦርነት፥ ከሰብአዊ ኪሳራው በተጨማሪ በመሰረት ልማት እና ኢኮኖሚ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ነው። በጦርነቱ ምክንያት የበርካታ ሕዝብ መገልገያ የነበሩ መንገዶች ውድመዋል፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት አንዲሁም የውኃ እና ሌሎች ማእከላት በተለያየ መጠን የሚገለፅ ውድመት ደርሶባቸዋል።
በ2013 ዓመተ ምህረት ለረዥም ወራት ተከታታይ ጦርነት በተደተረገባ በትግራይ ክልል ማእከላዊ ዞን የምትገኘው ጭላ ወረዳ፥ በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና መንገዶች ፈርሰዋል። የወረዳዋ አስተዳደር አቶ ሰይፈ አርአያ፥ የተወሰኑ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ቢሮሩም አሁንም ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ትምህርት ቤቶች በወረዳዋ መኖራቸውን ያመለክታሉ።
በመሰረተ ልማት የደረሰ ውድመት ከመጠገን በተጨማሪ ኢኮኖሚው የሚያነቃቁ ርምጃዎች በክልሉ እንዲወሰዱ ነዋሪዎች ይጠብቃሉ። ከአገላዕ ያነጋገርናቸው ነዋሪ አቶ ሃይላይ ስባጋድስ "ነዳጅ አቅርቦት አሁንም ችግር አለ። ኢኮኖሚው አልተመለሰም። የሚስተዋሉ ነገሮች ተከትሎ መረጋጋት አይታይም። በዚህም ምክንያት ስራ አጥነት አለ። ከጦርነቱ መቆም በርካታ ግዜም ቢሆን በርካታ ችግሮች ናቸው የቀጠሉት" ይላሉ።
በትግራይ ክልል የቀጠለው ፖለቲካዊ ውጥረት እንዲሁም ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ያለው ውዝግብ ክልል ከጦርነቱ በኋላም ጭምር በአስቸጋሪ ሁኔታ እንዲቀጥል እንዳደረገው በበርካቶች ይገለፃል። በሚጠበቀው መጠን እንኳን ባይሆንም ከዓለም አቀፉ ለጋሾች በሚገኝ ድጋፍ በትግራይ ክልል የመልሶ ግንባታ ተግባራት እየተከወኑ መሆኑንም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይገልፃል።
የትግራይ ክልል ዳግም ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪ ኢንጅነር ቴድሮስ ገብረእግዚአብሔር በክልሉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው መሰረተ ልማቶች ከዓለም ባንክ እና ሌሎች ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ መልሶ የመገንባት ስራዎች እየተከወነላቸው መሆኑ ለክልሉ መንግስት ቴሌቪዥን ጣብያ ተናግረዋል።
ኢንጅነር ቴድሮስ "284 ትምህርት ቤቶች፣ 98 የጤና ተቋማት እንዲሁም 558 የውሃ ማእከላት በሶስት ወር ጥገና ይደረግላቸዋል። ይህ ከዓለም ባንክ እና ሌሎች አጋዥ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ የሚደረግ ነው የመልሶ ግንባታ ስራ ነው። በድምር 1258 ፕሮጀክቶች ላይ ይህ የዳግም ግንባታ ሥራ የሚከወነው" ብለዋል።
በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት 80 በመቶ የሚሆኑ የትምህርት ቤቶች እንዲሁም 90 በመቶ የሚደርሱ የጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት እንደደረሳባቸው የክልሉ አስተዳደር ሲገልፅ ነበር ።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ