ትኩረት በአፍሪቃ፤ ኤኮዋስ ለሕልዉናዉ እየታገለ ነዉ፤ የኬንያ ተቃዉሞ ሠልፈኞች ፅናት
ቅዳሜ፣ ሰኔ 21 2017እንደ መመሥረቻ ደንቡ ቢዘልቅ ኖሮ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራትን በምጣኔ ሐብት ማስተሳሰር ነበር-አላማዉ።ሥሙም።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) ነዉ።በጊዜ ሒደ,ት አካባቢዉን በገጠመዉ ቀዉስና ምናልባት እንዳዶች እንደሚሉት በምዕራባዉያን ግፊትም ከምጣኔ ሐብታዊነቱ ይልቅ ፖለቲካ የሚጫጫነዉ ማሕበር ሆኗል።
የተከፋፈለዉ አካባቢና ማሕበር
ባለፉት ሁለት ዓመታት አባላቱን አቃቅሮ፣የትብብር አቅሙን ሰርስሮ፣ ያዳከመዉም ፖለቲካዊ መሆኑ ነዉ።ኤኮዋስ እስከ 2023 ድረስ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) 15 አባል ሐገራትን ያስተናብር ነበር።በተከታታይ በተደረጉ መፈንቅለ መንግሥታት ሥልጣን የያዙት የቡርኪና ፋሶ፣የማሊና የኒዤር ወታደራዊ ገዢዎች ከተቀሩት አባል መንግስታት የተቃጣባቸዉን ጫና በመቃወም በ2023 ራሳቸዉን ከማሕበሩ አባልነት አግልለዋል።
ሶስቱ ሐገራት የሳሕል መንግሥታትትብብር (AES) ያሉትን ማሕበር መስርተዋል።የሥልታዊ ጥናት ተቋም አጥኚ ቤቬርልይ ኦቺንግ እንደሚሉት ኤኮዋስ እየተሰነጣጠቀ፣ የሚያስተናብራቸዉ አብዛኞቹ ሐገራት በቀዉስ እየተናጡ ነዉ።
«ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥታት ተደርገዋል።ማሕበራዊና ሲቢላዊ አመረጋጋት ተከስቷል።በጣም የከፋዉ ደግሞ አካባቢዉ መሰነጣጠቁ ነዉ።ሶስት ሐገራት ከኤኮዋስ አባልነት ወጥተዋል።ጊኒ በአባልነት መቀጠል አለመቀጠሏም ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ አአይታወቅም። እንዲያዉ ሰፋ አድርገን ስናየዉ ኤኮዋስ የገጠሙትን ፈተናዋች በጋራ ለመወጣት አንድነቱን ለመጠበቅ እየታገለ ነዉ።»
ኤኮዋስ ልክ እንደ ምዕራባዉያን መንግሥታት ሁሉ አሸባሪ የሚላቸዉ በየአባል ሐገራት የሸመቁ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃትም የማሕበሩ ከፍተኛ ፈተና ነዉ።የኤኮዋስ አባል መንግስታት የየአመፀኞቹን ጥያቄ ለማድመጥ፣ሠላማዊ መፍትሔ ለመፈለግ ይሁን ሌላ የብልሆች ሥልት ለመቀየስ ከመሞከር ይልቅ አመፅን በኃይል ለመደፍለቅ ያደረጉት ጥረትም አልተሳካለትም።ሶስቱ ሐገራት ከአባልነት በወጡ ሰሞን የECOWAS ተወርዋሪ ኃይል ለመመሥረት የጀመረዉ ጥረትም እስካሁን እንደተንጠለጠለ ነዉ።
የሊቀመንበር ለዉጥ ይጠቅም ይሆን?
ኤኮዋስን ካናቱ ተቀምጠዉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቁል ቁል ሲያደረድሩት የነበሩት የናጄሪያ ፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ የሊቀመንበርነት ሥልጣናቸዉን ባለፈዉ ዕሁድ ለለሴራሊዮኑ ፕሬዝደንት አስረክበዋል።ቲኑቡ አቡጃ-ናጄሪያ ዉስጥ በተደረገዉ የኤኮዋስ ጉባኤ ላይ ሥልጣናቸዉን ሲያስረክቡ የማሕበሩ ተወርዋሪ ጦርን ለመመሥረት የሚደረገዉ ጥረት በጣም አዝጋሚ መሆኑ እንዳሰባቸዉ አስታዉቀዋል።
«የኤኮዋስ ተወርዋሪ ኃይልን አሸባሪነትን እንዲዋጋ፣ ለአካባቢያችን ሠላምና ደህንነት አስተማማኝ መሳሪያ እንዲሆን ለማድረግ አበክረን መጣር አለብን።»
የሴራሊዮኑ ፕሬዝደንት ጁሊየስ ማአዳ ቢዮ የኤኮዋስን የሊመንበርነት ሥልጣን ከናጄሪያዉ አቻቸዉ ሲረከቡ እንዳሉት ደግሞ በዘመነ ሥልጣናቸዉ አራት ጉዳዮችን ከግብ ለማድረሥ ቅድሚያ ይሰጣሉ።
«እንደ ሊቀመንበር ለ4 ጉዳዮች ቅድሚያ እሰጣለሁ።1ኛ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን መመለስና ዴሞክራሲን ማስረፅ።2ኛ የአካባቢዉን የፀጥታ ትብብር ማጠናከር።3ኛ የምጣኔ ሕብት ዉሕደትን ማፋጠን።4ኛ የተቋማትን ተዓማኒነት መገንባት።»
ቢዮ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊና ኒዤርን ወደ ማሕበሩ ለመመለስ እንደሚጥሩም ቃል ገብተዋል።የገቡትን ቃል ሙሉ በሙሉ ገቢር ያደርጉታል ተብሎ አይጠበቅም።እንዲያዉም ተሰናባቹ ሊቀመንበር ቲኑቡ «ወንድሞቻችን» ያሏቸዉን ሶስቱን ሐገራት ወደ ማሕበሩ ለመመለስ ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ተጥቅመን አልቻልንም ብለዋል።የፖለቲካ ተንታኝ ቤን ሤማንግ እንደሚሉት ግን ቢዮ የገቡት ቃል ተሳካም አልተሳከ ኤኮዋስ የመሪ ለዉጥ ማድረጉ ራሱ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ አሳድሯል።
«ብዙዎች፣ የመሪ ለዉጥ መደረጉ ፀጥታን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የአባል ሐገራትን አንድነትን ለማጠናከርም ይረዳል ብለዉ ያምናሉ።»
ተቃራኒ ማሕበራት ባንድ አካባቢ
ከኤኮዋስ አባልነት የወጡት ሶስቱ የሳሕል አካባቢ ሐገራት የመሠረቱት የጋራ ትብብር (AES) አዲስ፣ሶስት አባላት ብቻ ያሉትና የገንዘብ፣ የባለሙያና የአወቃቀር ችግር ያለበት ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ቤቨርሌይ ኦቺንግ እንደሚሉት ከዉጪ የሚያገኘዉ ዓለም አቀፍ ድጋፍም ትንሽ ወይም ምንም ነዉ።
«(ሶስቱ መንግስታት) ከሩሲያ፣ ምናልባት ከቱርክና ከቻይና ዉጪ ዓለም አቀፍ ድጋፍ አያገኙም።ምጣኔ ሐብታቸዉም ከፍተኛ ጫና አለበት።AESን ሙሉ በሙሉ ለማቋቋም፣ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማድረግ፣የተፈጥሮ ሐብትን ለመጠበቅ፣ እንደ ECOWAS፣COMESA ወይም እንደ EAC የተሟላ ማሕበር ለማድረግ ጠቀም ያለ ገንዘብ መመደብ አለባቸዉ።»
ኤኮዋስ ባንፃሩ የ50 ዓመት ልምድ አለዉ።ባለፈዉ ሳምንት ከአዉሮጳ ሕብረት ብቻ 110 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ተሰጥቶታል።ማሕበሩ ያቀደዉን ተወርዋሪ ኃይል ለማደረጃት ከሚያስፈልገዉ የ2.26 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ጋር ሲነፃፀር በጣም ትንሽ ነዉ።ይሁና ከAES ጋር ሲወዳደር አሁንም በሁለንተናዊ አቅሙ የተሻለ ነዉ።
ሁለቱ ተቀናቃኝ ግን የአንድ አካባቢ ማሕበራት ከልዩነታቸዉ ጋር የጋራ ችግራቸዉ በተለይ «አሸባሪን መዋጋት» የሚለዉ መርሕና አላማቸዉ እንዲቀራረቡ አስገድዷቸዋል።በቅርቡ እንደተነገረዉ ሁለቱ ማሕበራት በአባላት መካከል የሚደረግ የሰዎችና የሸቀጦችን ዝዉዉር ደሕነትን በጋራ ለመጠበቅ ተስማምተዋል።
የሶስቱን ሐገራት ወታደራዊ ገዢዎች አጥብቀዉ የሚቃወሙት፣በተለይ ኒዤርን ለመዉረር እስከመዛት የደረሱት የናጄሪያ ፕሬዝደንት ቦላ ቲኒቡ የሊቀመንበርነቱን ሥልጣን መልቀቃቸዉ የተጀመረዉን ትብብር ሊያጠናክር፣የኤኮዋስን የቁልቁሊት ጉዞ ለመግታት ይጠቅም ይሆናል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
የኬንያ ተቃዉሞ ሰልፍ፣ የሩቶ አስተዳደር የጎን ዉጋት
ለምዕራብ አፍሪቃ የኤኮዋስ መከፋፈል፣ የየሐገራቱ ማሕበረ-ፖለቲካዊ ቀዉስ፣ ከሁሉም በላይ የሸማቂዎች መበራከትና ጥቃት እንደሚያሰጋ ሁሉ ምሥራቅ አፍሪቃም በኢጋድ መዳከም፣ በሶማሊያ አለመረጋጋት፣ በሱዳን ጦርነት፣ በኢትዮጵያ ግጭት፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ ዉዝግብ እየተመሰቃቀለዉ ነዉ።
የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ከሚያስተናብራቸዉ ሐገራት ሁሉ የሠላምና መረጋጋት አብነት ተደርጋ የምትቆጠረዉ ኬንያም ከአምና ጀምሮ በተቃዉሞ ሠልፍ እየተናወጠች ነዉ።እስከ አምና ድረስ የኢትዮጵያ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣የሩዋንዳ፣ የሱዳን አስታራቂ የነበረዉ አልፎ ተርፎ የሐይቲን ሠላም ለማስከበር ፖሊስ ያዘመተዉ የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት የወጣቶቹን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ተስኖት አምና በጎርፍ የታጠቡት ከተሞች ዘንድሮ በሰዉ ደም እየወሰኩ ነዉ።
የወገኖቹ ደም «ደመ ከልብ እንዳይሆን» የሚታገለዉ ሕዝብ
አምና በዚሕ ወር የኬንያ መንግሥት ተጨማሪ ግብር ለመጣል መወሰኑን በመቃወም አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ፕሬዝደንት ሩቶ የግብር ጭማሪዉን ሕግ እንዲሽሩ ማስገደዱ ለሰልፈኛዉ በርግጥ ታላቅ ድል ነበር።ድሉ የተገኘዉ ግን ሰልፈኛዉ ለፀጥታ አስከባሪዎች ጥይትና ዱላ የ60 ወገኖቹን ሕይወት፣ የ230ዉን አካልና ደም ገብሮ ነበር።20 ሰዎች እስካሁን የገቡበት አይታወቅም።
ሕዝቡም የወገኖቹ ደም «ደመ ከልብ» ሆኖ እንዲቀር አልፈቀደም።ገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ዓመቱን ሙሉ እያሰለሰ ሲሰለፍ ነበር።የናይሮቢዋ ወጣት እንደምትለዉ ደግሞ ለሟቾች ፍትሕ መጠየቅም ሆነ መሪዎችን መቃወም ለኬንያዉያን የማይሸረፍ መብት ነዉ።
«እዚሕ የመጣሁት መጀመሪያ ኬንያዊት በመሆኔ፣ሁለተኛ፣ መሰለፍ መብቴ በመሆኑ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ ይሕን ሥርዓት እቃወማለሁ።ፈላጭ ቆራጭ ነዉ።»
ሩቶና ሥርዓታቸዉን ለማዉገዝ፣ አምና የተገደሉትን ሠልፈኞች ለመዘከር፣ ገዳዮች ለፍርድ እንዲቀቡ ለመጠየቅ ብርዥ ጥርዥ ሲል የነበረዉ ሰልፍ ባለፈዉ ሮብ አብዛኛ ኬንያን አጥለቀለቀ።ርዕሰ ከተማ ናይሮቢን ጨምሮ ከ47ቱ የኬንያ አዉራጃዎች 23ቱ የተቃዉሞ ሰልፍ ተደርጎባቸዋል።
ረብሻ፣ ዘረፋ፣ ቃጠሎ ግድያና አመፅ
እስከ ቀትር ድረስ ሠላማዊ የነበረዉ ሠልፍ ቀትር ላይ በተለይ ናይሮቢ ዉስጥ ወደ ረብሻና ግጭት ተለወጠ።ግድያ፣ ዘረፋ፣ ቃጠሎዉ ቀጠለ።ከፖሊስ ጥይት፣ዱላና እስራት ያመለጠዉ የመብት ተሟጋች ጁሊየስ ካማዉ ተደጋጋሚዉ ግድያ ከማሳዘን አልፎ አበሳጭቶታል።
«ፖሊሶች ሰዉ ሲገድሉ ከዚሕ ቀደም አይተናል።ሥለጉዳዩ ተናጋግረናል።ግድያዉን ተቃዉመናል።መፍትሔ ለመፈለግ ሞክረናል።ግድያዉ ግን አሁንም ቀጥሏል።ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፈኛ መግደሉን ለመቃወም ስንሰለፍ፣ ሌላ ሰዉ ወይም ሰዎች በፖሊስ ይገዳሉ።»
የኬንያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ ሮብ አደባባይ በወጣዉ ሰልፈኛ ላይ ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት የኃይል ርምጃ 16 ሰዎች ተገድለዋል።ከ400 በላይ ቆስለዋል።83ቱ በጠና ተጎድተዋል።
በሰልፍና ግጭቱ መሐል በተቀሰቀሰ ረብሻ ሱቆች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና የሐገሪቱ ምክር ቤት እንፃ በእሳት ተቃጥለዋል ወይም ተዘርፈዋል።የኬንያ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ኪፕቹምባ ሙርኮሜን ሰልፈኛዉን አመፀኛ፣ አዋኪና ሥርዓተ አልበኛ በማለት አዉግዘዉታል
«ተቃዉሞ ሰልፍ እንዳልነበረ አሁን ግልፅ ሆኗል።ሁከትና ሥርዓተ አልበኝነት ነበር።ፓርላማዉና ቤተ-መንግሥቱ የጥቃት ኢላማ ሆነዋል።ይሕን ሁከት ያቀዱ ወገኖች አስቀድመዉ ተዘጋጅተዉበት ነበር።ዕቅዳቸዉን በኢንተርኔት ጭምር አጋርተዋል።ዕቅዳቸዉ የመንግሥትና የዴሞክራሲ አብነታችንን ለመቆጣጠር ነበር።የሪፐብልኪቱን የዴሞክራሲ ምልክት የሆነዉን ፓርላማና ቤተ,-መንግሥቱን በመቆጣጠር የሆነ የሥርዓት ለዉጥ ለማምጣት ነበር።»
ሐኪሞች በርካታ ሰዎች የተገደሉት በቀጥታ በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ መስክረዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኬንያ ፀጥታ አስከባሪዎች የወሰዱትን የኃይል ርምጃ አሳሳቢ ብሎታል።የሰልፈኞቹ ጥያቄም ሙታን ከመዘከር የዊሊያም ሩቶን መንግስት ከሥልጣን ወደ ማስወገድ ከፍ ብሏል።
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር