ትራምፕ፤ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ተግባራዊ ሆንዋል
ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2017የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያወጁት የተኩስ አቁም ስምምነት በመካከለኛዉ ምስራቅ ተደቅኖ የነበረዉን ዉጥረት ወደ መረጋጋት ያመራ ነዉ ሲሉ በርካታ የአረብ ሀገራት ስምምነቱን በደስታ ተቀበሉት። የጀርመን የዜና ወኪል (dpa) እንደዘገበዉ፤ ግብፅ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በደስታ ተቀብላለች ፤ የክልሉን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ ቀውሶችን ዘላቂ እልባት ለመስጠት በቀጣይ ሁሉን አቀፍ ከሆኑ አካላት ጋር በመሆን ለሰላም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን እንደምትቀጥል ገልጻለች።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን በደስታ የተቀበለችዉ ሳዑዲ አረቢያ በበኩልዋ በመካከለኛዉ ምስራቅ ያለዉን ውጥረት ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ ከፍ አድርጋ እንደምትመለከተዉ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታዉቋል። በአማን የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለፀዉ ደግሞ በአካባቢው የሚታየዉ ቀዉስ ወደ አደገኛ መባባስ እንዳያመራ ስምምነቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። ሚኒስትር መስርያቤቱ መካከለኛዉ ምስራቅን በቀጣይ ከሚከሰት ቀዉስ እና መዘዝ ለመጠበቅ ስምምነቱን ማክበር አስፈላጊ ነዉ ሲልም አሳስቧል። የጀርመኑ መራሂተ መንግስት ፍሬድሪክ መርስ የዩኤስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት ደግፈዋል። ሩስያ በበኩልዋ የተኩስ አቁም ስምምነት በደስታ ተቀብላለች። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ እንዳሉት "ይህን ክስተት መቀበል ይቻላል" ሞስኮ የተኩስ አቁም ስምምነቱ "ዘላቂ" እንደሚሆን ተስፋ አታደርጋለች ሲሉ አክለዋል።
በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቆየት ብሎ እስራኤል እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሰዋል ሲሉ ወቅሰዋል። ትራምፕ ደስተኛ አልመሆናቸዉንም ተናግረዋል። በተለይም እስራኤል እንድትረጋጋ ትራምፕ ጠይቀዋል። ትራምፕ ኔዘርላንስ ሄግ ላይ በሚካሄደዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ሃገራት የኔቶ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ከማቅናታቸዉ በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱም ሃገራት ደስተኛ አይደለሁም ብለዋል። በተለይ በእስራኤል ደስተኛ አይደለሁም ያሉት ትራምፕ፤ የኢራን የኒኩሊየር አቅም ጠፍቷል ሲሉ ብለዋል። ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስራኤልም ሆነ ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱን መጣሳቸዉን ተናግረዉ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ ኢራን ተቋሞችዋን ለማደስ ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆንዋን አስታዉቃለች። የኢራን የአቶሚክ ኃይል ድርጅት ሃላፊ ዛሬ በኢራን መንግሥታዊ ቴሌቭዝን ባስተላለፉት መልክት ፤ አገራቸዉ ጥቃት የደረሰባቸዉን ተቋማት ሥራ ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ላይ ናት ብለዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በበኩላቸዉ ኢራን የኒኩሊየር ተቋሞችን ፈጽሞ መልሳ አትገነባም ሲሉ ቀደም ብለዉ ተናግረዉም ነበር። ዩናትድ ስቴትስ እሁድ ለሰኞ አጥብያ በኢራን ሦስት ግዙፍ የኩሊየር ኃይል ማበልፀግያ ቦታን በከፍተኛ ቦንብ መደምሰስዋ ይታወቃል።