የቡና ባለሙያ (ባሬስታ) ታጁር ታምራየሁ
ዓርብ፣ ግንቦት 15 2017ታጁር ታምራየሁ ስለ ቡና ጥራት፤ ከአለቃቀሙ አንስቶ እስከ አፈላሉ ድረስ ያውቃል። ይህንንም እውቀቱን ለሌሎች በበጎ ፍቃደኝነት ያጋራል። ይህን ሲያደርግ አንዳንዶች አዲስ አበባ ጎዳና ላይ ወይም ኢንስታግራም ላይ አይተውት ሊሆን ይችላል። በአንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ታጁር ማህበረሰቡን ስለ ቡና ለማስተማር የሚያባክነው የምሳ ሰዓት እንኳን የለም። « ምሳ ሰዓቴን በደንብ እጠቀማለሁ። መንገድ ላይ ያገኘሁትን አንድም ሆነ ሁለት ሰው ጋር አብሬ ቡና ጠጥቼ ወደ ቢሮ እመለሳለሁ። ከሰኞ እስከ ሐሙስ ይኼ ነው ስራዬ። ከአርብ እስከ እሁድ ደግሞ ከሰዓት በኋላ ለሁለት ሰዓታት ያህል በየቀኑ ስልጠና እሰጣለሁ»
ጎዳና ላይ ቡና ለማፍላት የሚጠቀማቸው የቡና ማፍያዎች የቆዩና ከተመረቱ 60 እና 70 ዓመት የሆናቸው ናቸው ይላል። ታጁር ቡና አፍልቶ የሚያስቀምሳቸው በቡና ገበያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ብቻ አይደለም። « ማበረታታት የምፈልጋቸው ሰዎች ናቸው። የቀን ስራ የሚሰሩም ሆነ ፓርኪንግ፣ ሊስትሮ የሚሰሩ ላይ አተኩራለሁ። ራይድ የሚሰሩ አሉ። አንዳንዴ ደግሞ ቢሮ የሚሰሩ ይጋብዙኝ እና እሄዳለሁ»
የሰው አስተያየት እንደ ቡና ማፍያው የተለያየ ነው። «አሀ! ለካ ቡና እንደዚህም ሊፈላ ይችላል?» ከሚል አስተያየት አንስቶ እስከ «የጀበና ቡና ይግደለኝ» የሚሉ የተለያዩ አስተያየቶችን ታጁር እስካሁን ሰምቷል።
ከጀበና ቡና እና ከሌሎች ቡና ማፊያ መንገዶች የቱ ይሻላል?
«10 እጅ ጀበና ይሻላል። ለዛም ነው ራሴን the_jebena_guy ያልኩት።» ይላል ታጁር። « ምክንያቱም ባህል አለው፤ የራሱ የሆነ የአፈላል ስርዓት አለው። ለእኔ ደረጃውን ጠብቆ ቢሰራ ጀበናን እመርጣለሁ። »
እሱም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የጀበና ቡናን ስለመረጠ ይበልጥ ስለ ጀበና የማወቅ ፍላጎቱ አደረበት እና ጥናት ያደርግ ጀመር፤ « የራሴን ጥናቶች ማድረግ ጀመርኩ። ጀበና እንዴት እንደሚሰራ ተማርኩ። የሸክላ ሰሪዎች ማህበር ሄጄም ተማርኩ። ከዛ ከምዕራባዊያን የቡና ማፍያዎች ጋር ማነፃፀር ጀመርኩኝ።»
ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለማፍላት ምን ማወቅ ያስፈልጋል?
ታጁር ሰዎች ስለ ቡና አፈላል ማወቅ ያለባቸው ነገሮችን በሶስት ለይቶ ያስቀምጣል። «ሳይቆላ፤ ከተቆላ በኋላ እና ሲፈላ። አብዛኛውን ጊዜ እኛ ጋር ቡና አሻሮ እስኪመስል ድረስ ይቆላል። ከዛ መለስ ማድረግ ያስፈልጋል። ሲፈላ የውኃው ሙቀት፤ የቡናው መጠን፤ አፈጫጭ ...። ሰዎች የፍጭት መጠኑን እና እሳት ላይ የሚቆይበትን ጊዜ ካመጣጠኑት የተሻለ ጣዕም ያለው ቡና መጠጣት ይችላሉ።»
ታጁር ከቡና ጋር የተዋወቀው ከልጅነቱ አንስቶ ነው። «እኔ የተወለድኩበት አካባቢ ጉጂ ነው።እዛ አካባቢ ቡና የሚበቅልበት አካባቢ ነው። ቢዝነሱ ላይ ዘመዶቼ ነበሩ። እዛ ሲሄዱ ቡና ማበጠሪያዎች ጋ እሄድ ነበር። ግን ስራውን ስራዬ ብዬ የጀመርኩት መጋዘን ውስጥ የጥራት ቁጥጥር ባለሙያ ሆኜ ስሰራ ነው። ከዛ የቡና ቀማሽ ሆኜ መስራት ጀመርኩ። ከዛ ነው የባሬስታ ትምህርት የወሰድኩት »
የባሬስታ ስራ ምንን ያጠቃልላል?
«ባሬስታ ማለት ለእኔ ስለ ቡና ዕውቀት የገበየ ባለሙያ ነው። ስለ ቡናው ቁሌት፣ ስለ አፈላሉ፣ ስለ የደንበኛ አገልግሎት ማወቅ አለበት።» የሚለው ታጁር ወደፊት ቡና እና ቡና ነክ ነገሮችን ማስተማር የሚችልበት ትምህርት ቤት ወይም ማዕከል መክፈት ይፈልጋል። ባገኘው አጋጣሚ አሁንም ያለውን የቡና እውቀት ለሌሎች እያጋራ የሚገኘው ይኼው ወጣት በቡና መገኛነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ይበልጥ በቡና ስሟ እንዲጠራ ከባለ ድርሻ አካላት እና ስራ ፈጣሪዎች ምን ይጠበቃል ይላል?
« ይህ እንደ ታሪክ ነው የሚወራው። አዎ ኢትዮጵያ መገኛ ሀገር ናት። ግን በስራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ወጥተን ስንወዳደር የመጀመሪያዎቹ ነን። አለም ርቆ ሄዷል። እኛ ግን አሁን ነው የባሬስታ ትምህርት መስጠት የጀመርነው። እና ጥሬ ቡና ከመላክ ውጪ ሌሎች ነገሮች ላይም መሰራት አለበት»
ታጁር ቡና ከሚያመርቱ ገበሬዎችም ጋር ሰርቶ ያውቃል። በተለይ ደግሞ የቡና መልቀሚያ ወራት በሆኑት « ጥቅምት፤ ህዳር እና ታህሳስ ወራት» ወደ ሲዳማ ፤ ይርጋጨፌ ፤ በየአመቱ ደግሞ ወደ ጉጂ እየሄደ ገበሬዎችንም እንደሚያሰለጥን ነግሮናል። « ደረጃ መለየት ላይ እናስረዳለን። አብረን እንለቅማለን።» ይላል።
ፎቶ አንሺም ነህ?
«አዎ! በፍላጎት ቡና ለቀማው ቦታ ጋር ስሄድ አነሳ ነበር። እና ጎን ለጎን ስራ ሆኖልኛል። ግን ሙሉ ትኩረቴ ቡናው ላይ ነው» ሲል ታጁር ታምራየሁን ስለራሱ አጋርቶናል። ወጣቱ ሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በተካሄዱ የባሬስታ ሻምፒዎንሺፕ ውድድሮችም ተካፍሎ ያውቃል። በሀገር ውስጥ በተካሄዱት የሶስተኝነት ቦታ ሲይዝ ታንዛንያ በተካሄደው ደግሞ ስድስተኛ ሆኗል።