ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትራምፕ አስተያየትና ኢትዮጵያ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 9 2017የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳምንታት በፊት በማህበራዊ መገናኛ አውታር ባጋሩት ጽሑፍ አሜሪካ [የቀድሞው አስተዳደር] ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሞኝነት ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰው ነበር። ይህንን አቋም ከትናንት በስተያ ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም አንፀባርቀውታል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት ምላሽ ለመጠየቅ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ደጋግመን ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። ይሁንና ይህንን ጥያቄ በተመለከተ ባለፈው ሐሙስ በነበረ የተቋሙ መግለጫ የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሰጡት መልስ "ይህ ፕሮጀክት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት እና ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ታላቅ አፍሪካዊ ፕሮጀክት ነው" ብለው ነበር።
ዶቼ ቬለ ከሕዳሴ ግድብ የቀድሞ ተደራዳሪዎች አንደኛውንና አሁን በውኃ ኃብት አስተዳደር አማካሪ ሆነው ከሚሠሩት አቶ ፈቅ አሕመድ ሙያዊ ማብራሪያ ጠይቋቸዋል።"ግድቡን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ነው የሠሩት" በማለት ፕራምፕ "ግልጽ የወጣ አድሏዊ ንግግር እያደረጉ ነው"ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ፕራምፕ የሕዳሴ ግድብ ወደ ናይል የሚሄደውን ውኃ የሚዘጋ እንደሆነ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ጠቅሰዋል። ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያንም ሆነ የግድቡን ስም ባይጠቅሱም " ከግብጽ ወጣ ብሎ የሚገኝ" እና "በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉት አንዱ" ያሉት ግድብ "መፍትሔ ያገኛል" በሚል ሥራውን በችግርነት ጠቅሰውታል። "የዐባይ ውኃ የግብጽ የሕይወት ምንጭ ነው" ሲሉም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
የሕዳሴ ግድብ "የትብብር እንጂ የግጭት መንስኤ እንደማይሆን" የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ አቋሙን አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ጋር ትናንት ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም. "በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኘነትና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር መክረዋል" ሲል አስታውቋል። ዝርዝር የውይይቱ ጭብጥ ግን አልተገለፀም።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው "የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ብዙ ውጣ ውረዶችን" ማሳለፉን፣ ግንኙነታቸው በፀጥታ፣ በሰላም፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ጠንካራ የሚባልና በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ" መሆኑንም ጠቅሰው ነበር።
የግድብ የቀድሞ ተደራዳሪና አሁን በውኃ ኃብት አስተዳደር አማካሪ ሆነው የሚሠሩት አቶ ፈቅ አሕመድ በሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለግብጽ ያደላ አቋም የሚያራምዱት "አምባገነን መንግሥታትን ስለሚወዱ"፣ ግብጽ በመጀመርያው የፕሬዝዳንት ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት እሳቸው እዲመረጡ 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓንና ውለታው መኖሩን እንዲሁም አሜሪካ በግብጽ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያላት መሆኑ ብሎም አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ግብጻዊያን ከፍተኛ የማግባባት ሥራ የሚሠሩ መሆናቸውን ተጠቃሽ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ከሳምንታት በፊት ያስታወቁት ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ መጪው መስከረም ላይ እንደሚመረቅም ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ